DiscoverDW | Amharic - Newsአብዛኛዎቹ ጀርመናውያን ጽንፈኝነትን ይቃወማሉ
አብዛኛዎቹ ጀርመናውያን ጽንፈኝነትን ይቃወማሉ

አብዛኛዎቹ ጀርመናውያን ጽንፈኝነትን ይቃወማሉ

Update: 2025-11-11
Share

Description

በጀርመን ብሔረተኝነት እያደገ መሄዱ አስጊ ቢሆንም፣ አንድ በቅርቡ የተካሄደ ጥናት ግን አብዛኛዎቹ ጀርመናውያን ዴሞክራሲን አብልጠው የሚደግፉ መሆናቸውን ደርሶበታል። የዶቼቬለው ሀንስ ፋይፈር እንደዘገበው፤ የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀኝ ጽንፈኝነት የፈረጀው አማራጭ ለጀርመን የተባለው ፓርቲ የሚያገኘው የህዝብ ድጋፍ እየጨመረ መሄዱ በሚገለጽበት በዚህ ወቅት ላይ የተካሄደው ይኽው ጥናት ፣ ቀኝ ጽንፈኝነት በጀርመን እየቀነሰ መምጣቱን ማመልከቱ ከተጠበቀው ተቃራኒው ሆኖ ተገኝቷል። እናም በዚሁ በአዲሱ ጥናት መሠረት በጀርመን ቀኝ ጽንፈኝነት አሳሳቢ ነው እንጂ እየተስፋፋ በመሄድ ላይ አይደለም ።



ጥናቱን ያካሄደው ለጀርመኑ የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ቅርበት ያለው ፍሪድሪሽ ኤበርት የተባለው የጥናት ተቋም፣ ፀረ-ዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎች ለመከላከል እንደ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት እንዲያገለግል ከጎርጎሮሳዊው 2006 ዓም አንስቶ መሰል ጥናቶችን ያካሂዳል። ብዙ ተመራማሪዎች በተሳተፉበት በአሁኑ ጥናት በጉዳዩ ላይ ለሁለት ሺህ ሰዎች ቃለ መጠይቅ ተደርጓል። የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ባካተተው የዚህ የዳሰሳ ጥናት ውጤት ከተጠበቀው ተቃራኒ ሆኖ ተገኝቷል። ከ80 በመቶ በላይ የጥናቱ ተሳታፊዎች ለዲሞክራሲ ፅኑ ቁርጠኝነት ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል።



የዚህ የዳሰሳ ጥናት ውጤትም ተቋሙ ከአራት ዓመት በፊት ባካሄደው ጥናት ከተገኘው ውጤት በ6 በመቶ ከፍ ያለ ነው። ምንም እንኳን የጀርመኑ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ አማራጭ ለጀርመን እያደገ ነው ቢባልም ጽንፈኝነት በሚመለከት ከሚጠበቀው በተቃራኒ በጀርመን በግልጽ ለቀኝ ጽንፈኝነት ያለው ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱን ጥናቱ ደርሶበታል። በጥናቱ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ሦስት በመቶ የሚሆኑት ጥብቅ የቀኝ ጽንፈኛ አመለካከት አላቸው ። ይህ አሀዝም ባለፈው ጥናት ከተገኘው ውጤት በእጅጉ ያነሰ ነው።



በጀርመኑ ቢሊፌልድ ዩኒቨርስቲ በግጭት እና ጥቃት ላይ ምርምሮችን የሚያካሂደው ተቋም ሃላፊ አንድሪያስ ዚክ የጥናቱን ውጤት እያሳዩ ለዶቼቬለ እንደተናገሩትየተወሰኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች ለጽንፈኝነት የተጋለጡ ናቸው። «በግራጫው አካባቢ ያሉትን ሰዎች ስንመለከት እና ከሌሎች ፀረ ዴሞክራሲ አቋም ካላቸው ጋር ስናነጻጽራቸው ለምሳሌ ዘረኝነትን የኑሮ ደረጃ ልዩነትን እና ጾታን መሠረት ያደረጉ አድሎዎችን በሚመለከት አዝማሚያቸው ዴሞክራሲን ከመደገፍ ይልቅ የሚቃወሙ ናቸው። ይህም ማለት በዚህ ስር ከተመደቡት አብዛኛዎቹ ከነዚህ ምርጡ ቢባሉ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አመለካከትን ይመርጣሉ። ለዚህም ነው ለሕዝበኝነትና ለጽንፈኝነት ይበልጥ የተጋለጡት።



ለጥናቱ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አብዛኛዎቹ ዴሞክራሲንና ብዝሀነትን በበጎ ነው የሚመለከቱት። የዳሰሳ ጥናቱ ካካተታቸው 70 በመቶው ምንም እንኳን በግለሰቦች ደረጃ ድርቅ ያለ የጽንፈኝነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም በጀርመን ቀኝ ጽንፈኝነት እያደገ መሄዱ እንደ አደጋ ነው የሚያዩት ። ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት መላሾች ቀኝ ጽንፈኝነትን የሚጻረር እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ናቸው።



በጀርመን ምዕራባዊ ክፍል ከሚኖሩት ይልቅ በምሥራቅ ጀርመን ውስጥ ካሉት፣ ብዙ ሰዎች ቀኝ ጽፅንፈኛአመለካከት እንዳላቸው ከሚገልጸው አጠቃላይ ግንዛቤ በተቃራኒ፣ በጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ምዕራባዊ ክፍል ነዋሪ የሆኑ በዳሰሳው ጥናት የተሳተፉ ሰዎች ተመራማሪዎቹ እንዳሉት በይፋ የማይታወቅ ቀኝ ጽንፈኛ አመለካከት አላቸው። እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት የሚገለጸው በግለሰብ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የተዛባ የዓለም እይታ አመለካከት ወይም በፀረ-ዴሞክራሲያዊ አመለካከቶች ላይ ነው።



ይሁንና የውጭ ዜጎች ጥላቻ ግን ከምዕራብ ጀርመን ይልቅ በምሥራቅ ጀርመን የተስፋፋ ነው።በአገር አቀፍ ደረጃ በጥናቱ ከተካተቱት 88 በመቶው በዴሞክራሲ ሁሉም መከበርና እኩል መታየቱን ከሁሉም ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። ሆኖም 25 በመቶው ለአናሳዎች ከሚገባው በላይ ትኩረት እየተሰጠ ነው ሲሉ ወደ 11 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አናሳዎች መሠረታዊ መብቶቻቸው ሊጠበቅላቸው ይገባል የሚለውን ሀሳብ ተቃውመዋል። በሌላ በኩል 30 በመቶው ለተገን ጠያቂዎች ያላቸው አመለካከት አሉታዊ መሆኑን አምነዋል፤ 36 በመቶው ደግሞ ለረዥም ጊዜ ስራ አጥ ሆነው ስለቆዩት አመለካከታችን አሉታዊ ነው ሲሉ መልሰዋል።



70% የሚሆኑት ተጠያቂዎች የቀኝ ጽንፈኝነት መስፋፋት ለጀርመን ስጋት አድርገው እንደሚመለከቱት ተናግረዋል። ተመሳሳይ ጥያቄ ከቀረበላቸው 22 በመቶው ችግሩ የተባባሰው በመገናኛ ብዙሀን አማክይነት ነው ብለው ያምናሉ። ብዙ ሰዎች በግልጽ ራሳቸውን ከቀኝ ጽንፈኛ አመለካከት አያርቁም ወይም አያስጠጉምም ። 20 በመቶ የሚሆኑት ተጠያቂዎች በቀኝ ጽንፈኝነት በግልጽ አልተስማሙም ወይም ቀኝ ጽንፈኝነትን አልተቃወሙም። በዳሰሳ ጥናቱ ከተካፈሉት 6 በመቶ ብቻ ፣ስለ ቀኝ ጽንፈኝነት የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች በሙሉ በግልጽ ተቃውመዋል። ይህ ቁጥርም በቀድሞ ጥናቶች ከታየው አነስተኛ ነው።



በጥናቱ መሠረት ቀኝ ጽንፈኝነት በእድሜ ከገፉት ይልቅ በወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ያመዝናል። የጥናቱ ተባባሪ አርታዒ እና በተለይ በወጣቶች ላይ የሚታዩ ጽንፈኛ አመለካከቶች አዋቂና ተመራማሪ ኒኮ ማርኮስ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት ምክንያቱን ከቀኝ ጽንፈኞች አስተሳሰቦች ጋር ያገናኙታል። «ግልጽ የቀኝ ክንፍ አክራሪዎች ሀሳቦች በተለይ ከናዚ ርዕዮተ ዓለም የተቀዱ መሆናቸውን በትክክል እናያለን ይኽውም አምባገነንትን መደገፍ ፣ፀረ-ሴማዊነት ወይም ለብሔራዊ ማንነት ያለ የጠንካራ ፍላጎት ስሜት ናቸው። »



ማርኩስ በዚህ ግኝት በተለይ ሊተኮርበት የሚገባው በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ ያለው ቡድን የአምባገነንነት አዝማሚያ ጠንካራ መሆኑ ነው ይላሉ። ከዚሁ ጋር ወጣቶች ሌሎች ስለነርሱ ውሳኔ ሰጭ በመሆናቸው ደስተኛ አለመሆናቸውም አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል። «በግል በጣም ትኩረት የሚስብ ሆኖ ያገኘሁት በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ፣ በእርግጥ የአምባገነናዊነት ጠንካራ ዝንባሌ መኖሩ ነው። ምናልባት በተወሰነ ደረጃ አስቸጋሪ ቃል ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይ ጊዜ፣ ጠበኝነት የሚፈጠረው እኔ ራሴ ውሳኔዎችን ማድረግ ስለማልችል እና ሌሎች ለእኔ ስለሚወስኑልኝ ነው የሚለውን ሃሳብ ያንጸባርቃሉ። ስለዚህ እነዚህ የአምባገነናዊነት ስሜቶች ሁልጊዜ በጣም አሻሚ ናቸው። እና ለምሳሌ ይህ ጠበኝነት ብዙውን ጊዜ የሚገለጸው ወጣቶች በተለይ የአናሳዎችን ዋጋ ዝቅ አድርገው በማየታቸው ነው።



ማርኩስ እንደገለጹት እነዚህ የተበሳጩ ወጣቶች በሕዝቡ ውስጥ ቀድሞውኑ የተገለለ ቡድን ይፈልጉና ጥቃታቸውን በነርሱ ላይ ያነጣጥራሉ ።ብዙ ሰዎች ብሔርተኝነትን እና የጀርመንን ጥቅሞች በኃይል እንዲጠበቁ የሚጠይቀውን አስተሳሰብ በግልጽ እየተቀበሉ ነው። ለምሳሌ፣ 23% የሚሆኑት “የጀርመን ፖለቲካ ዋና ዓላማ ጀርመን የሚገባትን ኃይል እና ክብር ማስጠበቅ መሆን አለበት።” በሚለውእንደሚስማሙ ተናግረዋል። ከስድስት ሰው አንዱ ወይም 15 በመቶው (15%) አምባገነንነትን ይደግፋል።



“ጀርመንን ለሁሉም ጥቅም በጠንካራ ክንድ የሚገዛ መሪ ሊኖረን ይገባል።” ሲሉ በዳሰሳው ጥናት ላይ ሀባቸውን አካፍለዋል። ሌላው ተመራማሪ አንድሪያስ ዚክ እዚህ ላይ በተቋማት ላይ ያለው እምነት መሸርሸሩ ያሰጋቸዋል። በርሳቸው አስተያየት ሰዎችየቀኝ ክንፍ ጽንፈኝነት ስጋት መሆኑን ለዚህም በቂ እርምጃ እየተወሰደ እንዳልሆነ ሲገነዘቡ፣ በዲሞክራሲያዊ አሠራር የማያምኑት ቁጥር ይጨምራል። ይህ ደግሞ ለአለመተማመንን በር ይከፍታል፣ እናም በዚህ ነጥብ ላይ ነው ጽንፈኞች እና ህዝበኞች የሚባሉት «መፍትሄው አለን» የሚሉት » ሲሉ ዚክ አስጠንቅቀዋል።



ኂሩት መለሰ



ታምራት ዲንሳ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

አብዛኛዎቹ ጀርመናውያን ጽንፈኝነትን ይቃወማሉ

አብዛኛዎቹ ጀርመናውያን ጽንፈኝነትን ይቃወማሉ