DiscoverDW | Amharic - Newsየተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተፅዕናና መርሕ በአፍሪቃ
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተፅዕናና መርሕ በአፍሪቃ

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተፅዕናና መርሕ በአፍሪቃ

Update: 2025-11-12
Share

Description

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከለኛዉ ምሥራቅና አፍሪቃ ዉስጥ የምታሳርፈዉ ተፅዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ነዉ።በነዳጅ ዘይት የበለፀገችዉ ሐገር መከካለኛዉ ምሥራቅ ዉስጥ ከሶሪያ እስከ የመን፣ ከሊባኖስ እስከ ፍልስጤም ግዛቶች የምታደርገዉ ተሳትፎ በበጎም በመጥፎም ይጠቀሳል።ባለፉት ጥቂት ዓመታት ደግሞ አድማስዋን አስፍታ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ጅቡቲ ዉስጥም በሚደረጉ ግጭቶች፣የንግድና ወደብን የመሳሰሉ ሌሎች የምጣኔ ሐብት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳረፈች ነዉ።



የትንሺቱ ሐገር ትልቅ ሐብትና ጉልበት



ሰባት ትናንሽ ግዛቶችን (ኤሚሬቶችን) የምታስተባብር ትንሽ ሐገር ናት።የተባበሩት የዓረብ ኤሚሬቶቶች የመባሏ ምክንያትም ይኸዉ ነዉ።ትንሽ ናት። በቆዳ ሥፋት የኢትዮጵያን አንድ 13ኛ ወይም የኦሮሚያ ክልልን ብታክል ነዉ።83 ሺሕ ስኪየር ኪሎ ሜትር።አጠቃላይ ነዋሪዋ 12 ሚሊዮን ይገመታል።አንጡራ ሕዝቧ ግን 1.3 ሚሊዮን ቢሆን ነዉ።ሐብታም ናት።የነዳጅና የጋስ ምድር።



ታሕሳስ 1971 (እግአ) የብሪታንያ ገዢዎች አካባቢዉን ለቅቀዉ ሲወጡ፣ ሼኽ ዛይድ ቢን ሡልጣን አል ናሕያ እኒያን የአሸዋ ክምር፣ በረሐማ ግን የባህር ተዋሳኝ-ሥልታዊ፣ የነዳጅና ጋስ ሐብታም ትናንሽ ግዛቶችን አስተባብረዉ የአሸዋዉን ክምር በሕንፃዎች ቁልል፣ በረሐማ ሜዳዉን በከተሞች ድርድር ያንቆጠቆጡት ገቡ።



አልጋ ወራሾቻቸዉ ደግሞ ትንሺቱን ሐገር ከለንደን-ዋሽግተን፣ ከፓሪስ-ብራስልስ፣ ኋላ ከቴል አቪቭ ኃይለኞች ጋር አስተባብረዉ ከመካከለኛዉ ምሥራቅ አድራጊ ፈጣሪዎች አንዷ አደረጉት።የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተለይ ሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ ላይ የምታሳድረዉን ተፅኖ በተበለከተ በቅርቡ ጥናታዊ ፅሑፍ ያሰራጩት ዶክተር ሙከረም ሚፍታሕ እንደሚሉት የአቡዳቢ ገዢዎች አፍሪቃ የገቡት አሜሪካንን ተክተዉ ይመስላል።



«ቀደም ብሎ በነበረዉ የትራምፕ አስተዳደር ወቅት አሜሪካ ከአፍሪቃ እያፈገፈገች ወጥታለች።እና የእሷን ቦታ ተክተዉ ከሷ የዉጪ ጉዳይ ፖሊስ መሠረታዊ የሆነ ለዉጥ የሌላላቸዉ ተቀራራቢ የሆነ የኃይል አሰላለፍ የሚከተሉ ኃይላትን ተክታ ነዉ አሜሪካ የወጣችዉ።ከዚያ በኋላ እንግዲሕ አፍሪቃ ዉስጥ ከፍተኛ ሚና ሲጫዎቱ የነበሩት እንግዲሕ እንደነ እስራኤል፣የተባበሩት አረብ ኤምሬት በዋነኝነት፣ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት--ተጠቃሾች ናቸዉ።»



የአቡዳቢ ገዢዎች ተፅዕኖ አፍሪቃ ዉስጥ ብዙ ቦታ ይታያል



ከ2 ሺሕ አስራዎቹ ወዲሕ ከካይሮ መፍንቅለ መንግሥት እስከ ሶማሊያ ብጥብጥ፣ ከሶሪያ ጦርነት እስከ ሊቢያ መወረር፣ ከየመን ጣልቃ ገብነት እስከ እስራኤል-ፍልስጤሞች ዉዝግብ ፣ከሱዳን ጦርነት እስከ ኢትዮጵያ-ኤርትራ እርቅና ፍጥጫ፣ የጁቡቲ ወደብ፣ የበርበራ ወደብ፣ የሱዳን ወርቅ፣ የታንዛኒያ ማዕድን ሌላም ብቻ ሁሌም-ሁሉምጋ አቡዳቢዎች አሉበት።



የፖለቲካ ተንታኝ አብዱረሕማን ሰይድ እንደሚሉት የዘመኑ የተባበሩት አ,ረብ ኤምሬቶች ገዢዎች የሚከተሉት መርሕ ከአባቶቻቸዉ የሚቃረን፣ ለሕዝባቸዉ የማይጠቅም፣ አተራማሽ ነዉ።



«አቡዳቢዎች በሚያደርጉት የግጭቶችና የሐገሮች ማፍረስና የሰዎች ማጎሳቆል ምን ጥቅም ያገኛሉ ቢባል የሚጠቀስ ነገር ብዙ የለም።እንዲያዉም በተቃራኒዉ፣ በሼክ ዛይድ በመስራቹ ጊዜ የነበራቸዉ ፕሪቭሌጅ፣ በዚያን ጊዜ ነዉ እንግዲሕ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የደረሱበት የደረሱት፣ምክንያቱን የነበራቸዉ ፖሊሲ ለሕዝባቸዉና ላገራቸዉ የሚጠቅም፣ ከሌሎች ጋር በሰላም የሚያኖር ነበር።»



ልምድ፣ሥልት፣ ትዕግሥትና ዕዉቀት የለሹ መርሕ



በኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ መምሕርና የፖሊሲ ጉዳዮች አጥኚ ዶክተር ሙከረም እንደሚሉት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አፍሪቃ ዉስጥ የ60 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ነዋይ ሥራ ላይ አዉላለች።የአቡዳቢ ገዢዎች የፖለቲካ ይሁን የምጣኔ ሐብት መርሕ ግን በሶስት ጉዳዮች ላይ የተመሠረተ ነዉ።ጠንካራ ኃይል መሆን፣ ሙስሊም ወንድማማቾች፣ አል ሸባብና ሁቲን የመሳሰሉ ተቀናቃኞቻቸዉን መምታትና የምጣኔ ሐብት ጥቅምን ማስከበር።እነዚሕ ፍላጎታቸዉን ለማስከበር ግን ገንዘብና ገንዘብ የሚገዛዉ ጉልበት እንጂ ልምዱም፣ ትዕግስቱም፣ ዕዉቀቱም፣ ሥልቱም ያላቸዉ አይመስልም።



«በዓለም ፖለቲካ ዉስጥ ተፅዕኖ በማሳደር ዓላማን የማሳካት ትራክ ሪከርድ ብዙም የላቸዉም።ሥለዚሕ ኤክስፐርመታል ጂኦፖለቲካል ጌም ነዉ አፍሪቃ ዉስጥ የሚጫወቱት-የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ማለት ነዉ።ይኸ የፈጠራቸዉ አንድ ቦታ በር ይከፍታሉ፣በሌላ ቦታ በር ይዘጋሉ።አንዳድ ቦታ ሰላም የሚመስል ነገር (ያደርጋሉ) በሌላ በኩል ደግሞ ግጭት ሲፍጥሩ የምናይበት ነዉ።»



የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ገዢዎች በየመኑ ጦርነት ከሳዑዲ አረቢያና ከግብፅ ጋር ተባብረዉ ሁቲዎችን ሲወጉ ነበር።በሱዳኑ ጦርነት ግን የካይሮና የሪያድ ገዢዎች ተቃርነዉ የፈጥኖ ደራሹን ጦር ይረዳሉ።ታዛቢዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያና ኤርትራ ዉዝግብ ወደ ኢትዮጵያ ያዳላሉ።የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስትን ተቃርነዉ የፑንትላንድ ራስ-ገዝ አስተዳደርን ይደግፋሉ።



ነጋሽ መሐመድ



ታምራት ዲንሳ

Comments 
loading
In Channel
loading
00:00
00:00
1.0x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተፅዕናና መርሕ በአፍሪቃ

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተፅዕናና መርሕ በአፍሪቃ

ነጋሽ መሐመድ