‹‹የሰላም ተመላሽ›› በወርቅና ግብርና ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች
Description
‹‹የሰላም ተመላሽ›› የተባሉ ወጣቶች በወርቅና ግብርና ስራ ላይ ተሰማርተዋል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ‹‹የሰላም ተመላሽ›› የተባሉ ከ9ሺ በላይ ከትጥቅ ትግል የተመለሱ ወጣቶችን ወደ ስራ መግባታቸውን የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ አመለከተ፡፡ ታቂዎቹን ወደ ስራ ለማስገባት 3 መቶ 25 ሚሊዩን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልሰላም ሸንግል አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ዓመታት ታጠቆ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላምም ስምምነት ከተደረገ ወዲህ በመረጡት የተለያዩ የስራ ዘርፎች መስራታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከመንግስት ጋር በጥቅምት 2015 ዓ.ም የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙት መካከል አንዱ የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ መሪ የሆኑት አቶ ግራኝ ጉዴታ አንዱ ናቸው፡፡ በድርጅታቸው ስም ከ7 ሺ በላይ የታጠቁ ወጣቶች ወደ መደበኛ ኑሮአቸው መመለሳቸውን ገልጸው ወደ ስራ ከገቡት መካከል በወርቅ ምርት ላይ የተሰማሩት ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ፓርቲ አመራሮች ውዝግብ
‹‹ከ9ሺ በላይ ታጣቂዎች ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ወደ ስራ ገብተዋል››
በ2013 ዓ.ም ታጣቂዎች በስፋት ይንቀሳቀሱበት የነበረው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት የሰላም ስምምነት ላይ ከተደረሰ ወዲህ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ መንገድ መመለሳቸውን የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡ በክልሉ በጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉ.ህ.ዴ.ን) እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤ.ህ.ነ.ን) ስም ይንቀሳቀሴ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ከመንግስት ጋር ስምምነት ላይ የደረሱት ከጥቅት 2015 ዓ.ም ጀምሮ ነበር፡፡
የክልሉ የስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልሰላም ሸንግል በአሁኑ ወቅት በክልሉ ካማሺ ዞን፣መተከል እና አሶሳ ዞን በማዕድን፣በግብርና ሌሎች የስራ ዘርፎች መሰማራታቸውን አመልክተዋል፡፡ በሱዳን እና በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ይንቀሳቀሱ የነበሩት ታጣቂዎቹ በመረጡት የስራ ዘርፍ ላይ ለረጅም ጊዜ ስልጠናዎች መሰጠቱን የገለጹት አቶ አብዱል ሰላም ሸንግል ከታጣቂዎቹ 80 በመቶ የሚሆኑት በጉህዴን ስም ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡ በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች “በፖለቲካዊ እና የብሔር ልዩነት የተቀሰቀሰ ግጭት” ተባብሷል ተባለ
ከመንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ከደረሱት መካከል የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ግራኝ ጉዴታ ስምምነት በተደረሰበት ወቅት በጉህዴን ስም ከ7ሺ በላይ ታጣቂዎች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ በጥቅምት 9 /2015 ዓ.ም ከክልሉ መንግስት ጋር ስምምት ላይ ከተደረሰ ወዲህ በድርጅቱ ስም ታጥቅ የሚንቀሳቀሱ ቡድን አለመኖሩን በመግለጽ አብዛኛው የተመለሱ ታጣቂዎች በመተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች እና በካማሺ ዞን በወርቅ ቁፋሮና እና በእርሻ ስራ መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ሁለት ዞኖች ታጥቆ ይንቀሳቀሱ የነበሩት የጉህዴን ታጣቂ ቡድን ወደ ሰላማዊ መንገድ ከተመለሱ ወዲህም ድርጅቱ በክልሉ በምርጫ ላይ በመሳተፍ 8 የክልል ምክር ቤት እና አንድ የህዝብ ተወካዮችን ወንበር ማግኘቱን አቶ ግራኝ ጉዴታ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ከ2ቱም የታጣቂ ቡድን ጋር የሰላም ስምምነት የተደረሰው በ2015 ዓ.ም ነበር
የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ላይ በደረሰበት በወቅቱ ድርጅቱ ፍትሐዊ የፖለቲካ ውክልና እና የመሰረተ ልማት ጥያቄ ማንሳቱን አመልክተዋል፡፡ በሌላ በኩል በሱዳንና ኢትዮጵያ ድምበር መነሻውን በማድርግ በአሶሳ ዞን በስፋት ይንቀሳቀስ የነበረው የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ደግሞ በታህሳስ ወር 2015 ዓ.ም ነበር በሱዳን ካርቱም ውስጥ በተደረሰው ስምምነት የሰላም አማራጭን በመቀበል ወደ ክልሉ መግባቱን በወቅቱ ተዘግበዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሁኑ ወቅት ጉህዴንን ጨምሮ ከስድስት በላይ ድርጅቶች ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና አግኝቶ በሰላማዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ























