በሰኔ ይጠናቀቃል የተባለው የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ወጪ ስንት ነው?
Description
ለረዥም ዓመታት የተጓተተው የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ በመጪዎቹ ስምንት ገደማ ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ተናግረዋል። በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የሚከናወነው የግድቡ ግንባታ በሰኔ ወር እንደሚጠናቀቅ የተገለጸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቦታው ተገኝተው ካደረጉት ጉብኝት በኋላ ነው።
ዐቢይ “የፕሮጀክቱ ቁልፍ የሆነው የወንዝ ቅልበሳ ሥራ በተሳካ መልኩ ተጠናቋል። የቀሩት ሥራዎችም በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እየተካሄዱ ይገኛሉ” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የመገጭ ግድብ በሚጠናቀቅበት ወቅት የአካባቢውን የግብርና ምርታማነት የሚያሳድግ ይሆናል” የሚል ተስፋ ሰጥተዋል።
“የመገጭ ግድብ ለመስኖ ይደርስልናል ብሎ ሕብረተሰቡ በጉጉት የሚጠብቀው” አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የምኅንድስና ባለሙያ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ግንባታውን በአካል የተመለከቱት የምኅንድስና ባለሙያ “የአካባቢው ማሕብረሰብ ብቻ ሳይሆን ከገበሬው አልፎ ራቅ ብሎ ከተማውም ለመጠጥ ውኃነት በተስፋ ይጠብቀዋል” ሲሉ አስረድተዋል።
የጣና ሐይቅ ተፋሰስ አካል በሆነው የመገጭ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ ሁለት ዓላማዎች ያሉት ነው። ማዕከላዊ ጎንደር፣ ምዕራብ ደምቢያ እና ምሥራቅ ደምቢያ ወረዳዎችን የሚያካልለው ዕቅድ አንዱ ዓላማ “በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ” ይሆናል።
ግንባታው ሲጠናቀቅ በመንግሥት መረጃ መሠረት “እስከ 17,000 ሔክታር የመስኖ እርሻ የማልማት አቅም” አለው። ሁለተኛው ዓላማ በጎንደር እና በጎንደር ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ለሚኖረው ሕብረተሰብ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ማቅረብ ይሆናል። ዕቅዱ ግን እስካሁን ድረስ በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ እና በጀት መሠረት አልተከናወነም። “የሆነ ነገር አስበህ ካልጨረስክ መገጭ ነው የምትባለው” ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት መኀንዲስ ተናግረዋል።
የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ውል በቀድሞው ውሃ ሀብት ሚኒስቴር እና በውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት መካከል የተፈረመው በመስከረም 2001 እንደነበር የፌድራል ሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ይፋ ያደረገው ሰነድ አሳይቷል። ሰነዱ በሰኔ 2017 እንደተዘጋጀ በመጀመሪያው ገጽ ላይ የሰፈረ ሲሆን በኮሚሽኑ ድረ-ገጽ የታተመው ጥቅምት 12 ቀን 2018 ነው።
የኮሚሽኑ “የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ዘርፍ የመስኖ ፕሮጀክቶች ውል አስተዳደር ግልጽነት እና ተጠያቂነት ሪፖርት” እንደሚለው በውሉ መሠረት የግድቡ ግንባታ “በ36 ወራት እንዲጠናቀቅ” ታስቦ ነበር። በሰነዱ መሠረት “የመጀመሪያው የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ በዓለም አቀፍ የጨረታ ውድድር ግዥው የተፈፀመ ነው።” “በበጀት እጥረት ምክንያት ሥራው ሳይጀመር ለ4 ዓመት በመዘግየቱ” ግንባታ የተጀመረው የመጀመሪያው የውል ማሻሻያ ተደርጎ በመጋቢት 2005 ነበር።
መገጭ ስንት እስካሁን ስንት ብር ፈጀ?
የዕቅዱ “የመነሻ የኢንቨስትመንት ዋጋ” 2 ቢሊዮን 451 ሚሊዮን 953 ሺሕ 789 ብር ነበር። ግድቡን የመገንባት ኃላፊነት የወሰደው ኮንትራክተር “የነጠላ ዋጋ እንዲሻሻልለት” ጠይቆ ሁለተኛ የውል ማሻሻያ በየካቲት 2007 ሲደረግ የፕሮጀክቱ ጠቅላላ የመነሻ ዋጋ ወደ 5.7 ቢሊዮን ብር ገደማ ከፍ አለ። በአጠቃላይ በአሰሪው እና በኮንትራክተሩ መካከል የተፈረመው ውል ስድስት ጊዜ እንደተሻሻለ የፌድራል ሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ሰነድ ላይ በዝርዝር ሰፍሯል።
የመገጭ ግድብ እና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ውል ከተፈረመ 17 ዓመታት፤ ግንባታው ከተጀመረ 12 ዓመታት ገደማ አስቆጥሯል። በፌድራል ሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ሰነድ መሠረት “የኢንቨስትመንቱ ዋጋው” ከ18.2 ቢሊዮን ብር በላይ “ተጨማሪ ወጪ የጠየቀ ነው።” አጠቃላይ ለሥራው የተመደበው በጀት 20.7 ቢሊዮን ብር ገደማ ደርሷል።
በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት የ2018 በጀት ከፍተኛ ገንዘብ ከተመደበላቸው የመስኖ እና የግድብ ግንባታ ሥራዎች መካከል መገጭ ቀዳሚው ነው። በበጀቱ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በአጠቃላይ 15.4 ቢሊዮን ብር ገደማ ተመድቦለታል። ከዚህ ውስጥ 14.5 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሆነው ለመስኖ ፕሮጄክቶች ግንባታ ፕሮግራም የተደለደለ ሲሆን የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ከ4.9 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦለታል።
መገጭ ምን ገጠመው?
ከጥቂት ወራት በፊት የመገጭ ግድብ ፕሮጀክትን የጎበኙት የጎበኙት የምኅንድስና ባለሙያ ግንባታው የዘገየው “ትኩረት በማጣት” እንደሆነ ያምናሉ። ለዚህም በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ግንባታው የተጠናቀቀውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንደ ማሳያ ይጠቅሳሉ። “ግድቡ ከአፈር ነው የሚሰራው። ግብዓቶቹ እዚያው አካባቢ የሚገኙ ናቸው። ሩቅ አይደለም” የሚሉት የምኅንድስና ባለሙያው ሥራው ለረዥም ዓመታት የተጓተተው “ውስብስብ ሆኖ አይደለም” የሚል አቋም አላቸው።
የግንባታው ውል ከተፈረመ በኋላ ባሉት ዓመታት የፕሮጀክቱ ባለቤት እና ግንባታውን የማከናወን ውል የተሰጠው የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት አወቃቀራቸውን ቀይረዋል። በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ ባለቤት የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ነው።
ዶይቼ ቬለ ከመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሀም በላይ እና ከአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክትን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግንባታውን ስድስተኛ የውል ማሻሻያ በሰኔ 2014 ተፈራርመው ነበር። ይሁንና በአሰሪ እና በተቋራጩ መካከል የነበረው ውል በግንቦት 2016 ተቋርጧል።
ውሉ ከመቋረጡ በፊት በ2013 ግንባታው ከ75 በመቶ በላይ ደርሶ እንደነበር የፌድራል ሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ሰነድ አትቷል። በ2013 “የግድቡ ማዕከላዊ ክፍል የመሰንጠቅ አደጋ” ቢደርስበትም ሳይጠገን ቀርቷል። የተሰነጠቀው “የግድቡ ማዕከላዊ ክፍል የመፍረስ አደጋ” በ2015 ከገጠመው በኋላ በመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር እና በኮንትራክተሩ መካከል የነበረው ውል እንዲቋረጥ ተደርጓል።
“የሥራው ቅደም ተከተል አለመጠበቅ እና የስልት ችግር” ለግድቡ ማዕከላዊ ክፍል መፍረስ ምክንያት እንደሆነ የሚገልጸው የፌድራል ሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ሰነድ “በተቋራጩ ግድየለሽነት” እንደተከሰተ አትቷል። አደጋው 75 በመቶ ደርሷል የተባለውን የግንባታ ሒደት ወደ 66 በመቶ ዝቅ አድርጎታል። ይሁንና ውሉ ሲቋረጥ መንግሥት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን “ያለምንም ቅጣት” እንዲሰናበት ተደርጓል።
ከግንባታ ጥራት ጉድለት በተጨማሪ ከማሳቸው ለሚነሱ ገበሬዎች የሚከፈል ካሳ ጉዳይ፣ የተቋራጩ የፋይናንስ አቅም መድከም፣ እና የአማካሪው የአቅም ድክመት ሌሎች በፌድራል ሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ሰነድ የተዘረዘሩ የመገጭ ግድብ ፕሮጀክትን የገጠሙ ችግሮች ናቸው።
በእርግጥ መገጭ በሰኔ ይጠናቀቃል?
ከፍተኛ ባለሥልጣናት የግንባታውን ሒደት ከጎበኙ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ “ሕዝቡ በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ቅሬታ ሲያሰማበት” እንደቆየ የተናገሩት የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሀም በላይ መንግሥት “በተከታታይ ችግሩን ለመቅረፍ ሙከራዎች” ሲያደርግ መቆየቱን አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ዓመት ካስተላለፉት “የተለየ ውሳኔ” በኋላ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽንን “በማስወጣት አዲስ ኮንትራክተር ገብቶ” እንዲሰራ መደረጉን ተናግረዋል። “ከውጭ አማካሪዎች አምጥተን ጥናት አድርገን፤ ሲሠራ የነበረበት ቴክኒካል ችግር ከሥር መሠረቱ መፍትሔ እንዲያገኝ ካደረግን በኋላ ፕሮጀክቱ አሁን በጤናማ የፕሮጀክት አመራር ሥርዓት እየሔደ ያለ ፕሮጀክት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
በአሁኑ ወቅት ግንባታውን በማከናወን ላይ የሚገኘው ቤ.አ.ኤ.ካ ጠቅላላ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለ ኩባንያ ነው። መንግሥት ሥራውን ለኩባንያው የሰጠው “በቀጥታ የግዥ ዘዴ” ሲሆን በሰኔ 2016 ውሉ ሲፈረም ግንባታው በሁለት ዓመታት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ታቅዷል።
የተቋራጭ ለውጥ ከተደረገ በኋላ ያለውን የግንባታ ሒደት በአካል ለመመልከት የቻሉት የምኅንድስና ባለሙያ “አካሔዳቸው አሪፍ ነው። ባየሁበት ሰዓት በጣም ጥሩ ነው። ቀንም ማታም ይሰራሉ” ሲሉ ተናግረዋል። “ለፖለቲካ ሳይሆን እንስራ ከተባለ ይሰራል” የሚሉት ባለሙያው “ሁል ጊዜ ሔዶ ፎቶ እየተነሱ መመለስ ከሆነ አያልቅም። አሁንም ሌላ አስራ አምስት አመት ሊጨምር ይችላል” የሚል ሥጋት አላቸው።
ባለፈው ሣምንት የመገጭ ወንዝ አቅጣጫ በመቀየሩ “ከጫፍ እስከ ጫፍ ግድቡን መስራት የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል” ያሉት ዶክተር አብርሀም ቆሞ የነበረው መዋቅራዊ ሥራ “100% ተጠናቋል” ሲሉ ተደምጠዋል። “ዋናው ግድቡ የአፈር ሙሌት ሥራው በስፋት እየተሠራ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ “በዚህ ሒደት ከሰኔ በፊት ፕሮጀክቱን ዋና ግድቡን ሙሉ በሙሉ ጨርሰን የምናከብረው ይሆናል” ሲሉ አብራርተዋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የምኅንድስና ባለሙያ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ግንባታውን ለማጠናቀቅ የያዘውን የጊዜ ሰሌዳ ሊከልስ እንደሚችል ያምናሉ። ባለሙያው ከጊዜ ሰሌዳው ባሻገር የተገደበውን ውኃ ወደ ገበሬው የእርሻ ማሳ የሚያከፋፍሉ ማስተላለፊያዎች መጠናቀቅ እንደሚኖርባቸው ይሞግታሉ። “ለመገጭ ግድብ ብቻ ሳይሆን የርብ ግድብ እኮ ተመረቀ ይባላል እንጂ ለሥራ እንዲውል የውኃ ማስተላለፊያ ቦይ አላለቀም” ሲሉ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገነባው የርብ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ለበርካታ ዓመታት ከዘገዩ የመንግሥት ተመሳሳይ ዕቅዶ መካከል ይገኝበታል። አርጆ ዴዴሳ፣ ወይቦ እና ካሌድ ጂጆ የተባሉት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ለረዥም ዓመታት የተጓተቱ እና ተጨማሪ ከፍተኛ ወጪ የጠየቁ ናቸው።
አርታዒ ታምራት ዲንሳ























