በአሜሪካ ለሚወለዱ ህጻናት የገንዘብ ቁጠባ
Description
እንደ ጎርጎሮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር፣ ከሚቀጥለው ሐምሌ ወር 2026 የአሜሪካ የነጻነት ቀን ጀምሮ፣ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ህጻናት፣''ትራምፕ አካውንት" በተሰኘ የባንክ ሂሳብ፣አንድ ሺህ ዶላር ይበረከትላቸዋል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፊርማቸውን በማኖር ባስጀመሩት በዚህ መርሐ ግብር መሰረት፣ በመገባደድ ላይ ባለው የጎርጎሮሳዊው 2025 የተወለደች አንዲት ህጻን ልጅ በሚቀጥለው ሐምሌ ፣ አንድ ሺህ የአሜሪካ ዶላር የያዘ የባንክ ደብተር ይኖራታል።
በመርሐ ግብሩ መሰረት፣ለእዚች ልጅ፣ወላጆቿ፣ ቤተሰቦቿ ወይንም ሌሎች መስሪያ ቤቶች በባንክ ቁጥሯ፣በዓመት እስከ አምስት ሺህ ዶላር ድረስ ሊቆጥቡላት ይችላሉ። በዚህ ስሌት መሰረት፣ ይህች ልጅ 18 ዓመት ሲሆናት፣ 170 ሺህ ዶላር፣ልጅቱ ይህንኑ ቁጠባ እስከ 35 ዓመቷ ድረስ ከቀጠለችም፣ በባንክ ሂሳቧ ላይ 700 የአሜሪካ ዶላር ወይም በኢትዮጵያ የዛሬ አንድ የአሜሪካ ዶላር የብር ምንዛሬ ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ ትቆጥባለች ማለት ነው።
''ትራምፕ አካውንት''ምንድን ነው?
ስለ "ትራምፕ አካውንት'' ምንነት የጠየቅናቸው፣አትላንታ ጆርጂያ ውስጥ የታክስ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት፣ አቶ አስገዶም ተመልሶ እንደሚከተለው አስረድተዋል። ''ይሄ የትራምፕ አካውንት፣ከ18 አመት በታች ያሉ ህጻናትን ይመለከታል። አካውንቱ በገንዘብ ግምጃ ቤት የግብር ክፍል የሚከናወን ሆኖ በዚህ ዓመት 2025 ከጥር አንድ ቀን ጀምሮ፣ አሜሪካውስጥ ለተወለዱ ወይም የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው አንድ ሺ ዶላር የሚሰጥ ነው።ይህ አንድ ሺህ ዶላር በባንክ ሂሳብ ቁጥራቸው ላይ የሚገባ ነው።እስከ 2028 ድረስ የሚቀጥል ነው፤በትራምፕ ዘመን ማለት ነው።"
አቶ አስገዶም እንደሚሉት፣ልጆቹ 18 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ፣ይህንን ገንዘብ ከባንክ ሂሳባቸው ላይ ማውጣት አይችሉም።
''18 ዓመት እስኪሞላቸው፣አይነካም፤ማውጣት አይችሉም። እና እያደገ እያደገ ይሄዳል።18 ዓመት ሲሞላቸው፣በቂ ገንዘብ ይኖራቸዋል የሚል እሳቤ ነው።''
አሜሪካውስጥ ለልጆች የመጣላቸው መልካም ዕድል ይህ ብቻ አይደለም፣ ሌሎች ባለሀብቶችም የቀየሱላቸው የሀብት መንገድ አለ ይላሉ፣ ከፍተኛ የታክስ ባለሙያው፤
''ዐሥር ዓመትና ከእዛ በታች ላላቸው ልጆች፣ በጣም አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው፣እሰከ 150 ሺህ ዓመታዊ ሺህ ዓመታዊ ገቢ ላላቸው፣ለልጆች እስከ 250 ዶላር በአካውንታቸው ለመስጠት ቃል ገብተዋል።''
የመርሐ ገብሩ ጠቀሜታ
እነዚህ ለልጆች የተከፈቱ ዕድሎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አላችው ያሉት አቶ አሰገዶም፣ 18 ዓመት ሲሞላቸው፣ለከፍተኛ ትምህርት ክፍያ፣ቤት ለመግዛት ወይንም ንግድ ለመጀመር ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አብራርተዋል።ቁጠባው ከግብር ነጻ መሆኑ፣ ሌላው ጠቀሜታው መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ አሜሪካውያንና ኤርትራ አሜሪካውያን፣በዚህ ዕድል ለመጠቀም ምን ማድረግ አለባቸው ብለን የጠየቅናቸው ከፍተኛ የታክስ ባለሙያው፣እንደሚከተለው መልሰዋል።
የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን መመዝገብ ያስፈልጋል
"ፕሮግራሙ በራሱ የሚጀምር አይደለም፥መንግሥት የእከሌ ልጅ ብሎ የባንክ ሂሳብ ከፍቶ የሚሰጥ አይደለም።ወላጅ፣ቤተሰብ የባንክ ሂሳብ ይከፍታል።ይሄ የሚጀምረው በሐምሌ 2026 ነው።አንዳንድ የሚካሄዱ አሰራሮች አሉት።ይህን የሚያስተዳድረው፣የገንዘብ ግምጃ ቤት የግብር ክፍሉ ስለሆነ እነሱ የሚያዘጋጁ ቅጽ አለ።እዛ ቅጽ ላይ ተሞልቶ መላክ አለበት።ወላጆች ሞልተን ስንልክ የአሜሪካ ዜጋ የሆነና ሶሻል ሴኩሪቲ ቁጥር ያለው፣ይህን አካውንት ተከፍቶ፣የተከፈተውን ሂሳብ፣የታክስ አስተዳደሩ በሚሰጠው ቅጽ ላይ መረጃውን ስናስገባ አንድ ሺህ ዶላር ይላክልናል ማለት ነው።ይህ የልጆችና ገንዘብ የሚተዳደረው፣ በአሜሪካ የግል ድርጅቶች እና በአክሲዮን ገበያዎች ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
ታሪኩ ኃይሉ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ























