ኢትዮጵያ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የማርበርግ ቫይረስ የሙከራ ክትባት መስጠት ልትጀምር ነው
Description
ኢትዮጵያ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የማርበርግ ቫይረስ የሙከራ ክትባት መስጠት ልትጀምር ነው። “የጤና ባለሙያዎች እና ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ቡድኖች ቅድሚያ” እንደሚሰጣቸው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ለተከሰተው “የማርበርግ ቫይረስ ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ 2,500 የማርበርግ ቫይረስ የሙከራ ክትባት ከአሜሪካ መንግሥት በድጋፍ” መገኘቱን መሥሪያ ቤቱ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ አስታውቆ ነበር።
“ክትባቱ በአርማወር ሃንሰን የምርምር ተቋም በሚመራ ፈጣን የደረጃ 2 ክሊኒካዊ ሙከራ ተደርጎለት ጥቅም ላይ እንደሚውል” የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለጹ መሥሪያ ቤታቸው ያሠራጨው መግለጫ ይጠቁማል።
ክትባቶቹን ለኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ያስረከቡት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ የማርበርግ በሽታን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት “አስቸጋሪ” መሆኑን ጠቁመው “ብዙ የሚቀር ነገር” እንዳለ ተናግረዋል።
አሜሪካ ለኢትዮጵያ ያቀረበቻቸው የሙከራ ክትባቶች የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር “ጠቃሚ የመጀመሪያ እርምጃ” እንደሚሆን ገልጸዋል።
የአሜሪካው ሳቢን የክትባት ኢንስቲትዩት ከ640 በላይ በሙከራ ላይ የሚገኘውን ሲኤዲስሪ የማርበርግ ክትባት (cAd3-Marburg Vaccine) ወደ ኢትዮጵያ እንደላከ አስታውቋል።
የማርበርግ ቫይረስ በሽታ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መገኘቱ እንደተረጋገጠ ከጤና ሚኒስቴር ጥያቄ እንደቀረበለት ሳቢን የክትባት ኢንስቲትዩት ገልጿል። ጥያቄውን የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እንዳጸደቀ ተቋሙ አስታውቋል።
ወጪውን የሚሸፍነው በአሜሪካ ጤና ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የባዮ ሜዲካል የላቀ ምርምር እና ልማት ባለሥልጣን (Biomedical Advanced Research and Development Authority) ነው።
ሳቢን የክትባት ኢንስቲትዩት እና ጤና ሚኒስቴር የክትባቱን “ደሕንነት፣ ውጤታማነት እና የመከላከል አቅም” የሚፈትሹ ሙከራዎች በሁለት ቡድኖች ለማከናወን ከሥምምነት መድረሳቸውን መግለጫ ይጠቁማል።
በሥምምነቱ መሠረት በመጀመሪያው ቡድን ክትባቱ የሚሰጣቸው በ21 ቀናት ውስጥ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ቀጥተኛ ንክኪ ለነበራቸው ከፍተኛ ተጋላጭ የሆኑ የጤና ባለሙያዎች፣ ሠራተኞች እና ግለሰቦች ብቻ ይሆናል።
ሌሎች የጤና ባለሙያዎች፣ የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት የሚሳተፉ ሠራተኞች እና ግለሰቦች በሁለተኛው ቡድን ይካተታሉ።
ሲኤዲስሪ የማርበርግ ክትባት (cAd3-Marburg Vaccine) በርዋንዳ፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በዩጋንዳ እና በኬንያ በተለያዩ ደረጃዎች በሙከራ ላይ የሚገኝ ነው።
ትላንት አርብ 104 የላብራቶሪ ምርመራዎች ተደርገው አንድም በማርበርግ ቫይረስ የተያዘ ሰው እንዳልተገኘ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጋራ ዕለታዊ መግለጫ አሳይቷል።
የማርበርግ ቫይረስ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከተረጋገጠ ወዲህ እስከ ትላንት ኅዳር 26 ቀን 2018 ድረስ 1,235 የላብራቶሪ ምርመራዎች የተደረጉ ሲሆን 13 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ስምንት ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ አራቱ አገግመዋል፤ አንድ ሰው ደግሞ በሕክምና ላይ ይገኛሉ።
አርታዒ ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር























