ዓመታዊው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ በብራዚል
Description
«የፓሪስ ስምምነትን ከፈረምንበር ከጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓም ጀምሮ፤ ሳይንሱ ግልፅ በሆነበት ጊዜ፤በ2050 የዓለም ኤኮኖሚ ከብክለት ነጻ መሆን እንዲችል፤ በ2030 ብክለቱ በግማሽ እንዲቀንስ ከ2020 አስቀድሞ ዓለም አቀፍ የብክለት መጠኑ በደንብ ዝቅ ማለት እንደሚኖርበት በፖሊሲው ዓለም ግልጽ ነበር። አሁን ከዚህ ወሳኝ ዓመት ላይ ለመድረስ የቀረን አምስት ዓመት ብቻ ነው። የብክለት መጠኑም እየጨመረ መሄዱን ቀጥሏል።» የአየር ንብረት ተጽዕኖንን የሚመረምረው በፖስትዳም ተቋም ዳይሬክተር ዮሀን ሮክሽትሮም፤
የብራዚሉ የአየር ንብረት ለወጥ ተመልካች ጉባኤ
የተመ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ ዛሬ በብራዚሏ ቤለም ከተማ ተጀምሯል። ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለሁለት ሳምንት የሚዘልቅ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥም 200 ከሚሆኑ ሃገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች የምድራችንን የሙቀት መጠን መቀነስ ላይ ላይ አተኩሮ እንደሚነጋገር ተጠቁሟል። የዓለምን የአየር ንብረት እንዳበላቸው የሚነገርለትን የበካይና ሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ለመቀነስ የዛሬ አስር ዓመት ነበር ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ ሃገራት ከብዙ ክርክርና ድርድር በኋላ ተስማምተው የተፈራረሙት። ከዚያ ወዲህ እንደታሰበው ከባቢ አየርን በካይ የሚባሉት በኢንዱስትሪው ያደጉት ሃገራት የልቀት መጠን ቀንሰዋል ወይ የሚለው አጠያያቂ ቢሆንም፤ለውጥ እየታየ መሆኑን የሚጠቁሙ ዘገባዎች ይወጣሉ። በተቃራኒው ብክለቱ እየባሰበት መሄዱን የሚያሳዩ ተመራማሪዎችም በየጉባኤው በይፋ መረጃዎችን በመጥቀስ ይሞግታሉ። በብራዚሉ ጉባኤ ዋዜማ የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት 10ኛ ዓመት በታሰበበት መድረክ የተገኙት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽን ይህንኑ ነው ያመላከቱት።
«የዛሬ አስር ዓመት የፓሪስ ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ በብሔራዊ ደረጃ የተረጋገጡ አስተዋጽኦዎች ማለትም NDC ሃገራት ከአየር ንብረት ጥበቃ አኳያ ያላቸው የምኞት መለኪያ ሆነው ቆይተዋል። በዚህ ረገድ በቅርቡ የተወሰነ መሻሻል ታይቷል። ሆኖም ግን በእውነታው ጉባኤ ሁላችንም ሀቀኞች መሆን አለብን። የቀረቡት እቅዶችና ፖሊሲዎች አሁንም በቂ አይደሉም።»
«የእውነት ጉባኤ» COP30 ቤለም ብራዚል
ቤለም ብራዚል ከተማ የሚካሄደውን COP30ን የእውነት ጉባኤ ብለው የሰየሙት የአስተናጋጇ ሀገር ፕሬዝደንት ሉላ ኢናሲዮ ደሲልቫ ናቸው። ሉላ ደሲልቫ በጉባኤው መክፈቻ ንግግራቸው ነገር እያሳመሩ መልካም የማውራትና በጎ ፍላጎት የማሳያው ዘመን አክትሟል አሁን የተግባር ጊዜ መሆን አለበት ማለታቸው የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ሉላ ይህ ጉባኤ እንደሌላው ጊዜ እንዳይሆን ሲያሳስቡም ሕዝብ በእኛ እምነት እንዲኖረው ይህን ስብሰባ የእውነት ጉባኤ እናድርገው በማለት ነው የጠየቁት። ይህን ያሉበትን ምክንያትም አስተድተዋል።
«COP30ን የእውነት COP ማድረግ ማለት ለሳይንስ እውቅና መስጠትና የተደረጉ ለውጦችንም አለመካድ ነው። በዚያም ላይ ደስ የማይለውን እውነት ሁሉ መቀበል ማለት ነው። ይህም ማለት አሁንም ዓለም ፓሪስ ላይ ከተደረሰው የስምምነት ግብ አሁንም ገና አልደረሰም።»
በእርግጥም የጉባኤው አስተናጋጅ ሀገር የብራዚል ፕሬዝደንት የተናገሩት እውነትነቱን የሚያሳዩ መረጃዎች በይፋ እየታዩ ነው። ለዚህም ነው አንቶኒዮ ጉተሬሽ የዛሬ አስር ዓመት ፓሪስ ላይ ጉባኤው ከታቀደለት ቀን በላይ ጊዜ ወስደው የተደራደሩት መንግሥታት እንደተስማሙት የዓለምን የሙቀት መጠን ከ1,5 ዲግሪ በታች ዝቅ እንዲል ማድረግ ተስኗቸዋል ያሉት።
«ከባዱ እውነት ከ1,5 ዲግሪ በታች እንዲወርድ ማድረግ ተስኖናል። ሳይንስ ከ2030 መጀመሪያ አንስቶ የሚቀቱ መጠን ከ1,5 ዲግሪ እንደሚበልጥ ነግሮናል። ይህን ከመጠን በላይ የሆነ ሂደት ለመገደብና በፍጥነት ወደታች ለማውረድ የአሠራር ለውጥ ያስፈልገናል። ሌላው ቀርቶ ጊዜያዊ ጭማሪ እንኳን ቢከሰት የሚያስከትለው መዘዝ አስከፊ ነው የሚሆነው። ስነምህዳሮቹ ከማይቀለበስ ጫፍ ይደርሳሉ፤ በቢሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ለኑሮ አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል፤ የሰላምና ደኅንነት ስጋት ሊያጋጥም ይችላል። ሌላው ቀርቶ መጠነኛ የዲግሪ ጭማሪ ቢከሰት ተጨማሪ በርካታ ርሀብ፤ መፈናቀል እና በተለይ እነዚያ ለብክለቱ ተጠያቂ ያልሆኑ ወገኖችን ለእልቂት መዳረግ ነው። ይህ ደግሞ የሞራል ውድቀትና አደገኛ መዘናጋት ነው።»
አነጋጋሪው የሙቀት አማቂና በካይ ጋዞች ቅነሳ
ከወዲሁ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ብራዚል ላይ የተሰባሰቡት ሃገራት የውይይታቸው ትኩረት የሚሆነው የዓለም የሙቀት መጠን እንዲቀንስ ሊወሰድ የሚገባው ወሳኝ እርምጃ ነው። አሁንም ግን ሙቀት አማቂና በካይ ጋዞችን የመቀነሱ እርምጃ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋቶቹ በርካታ ናቸው።
ሁኔታው ያሳሰባቸው የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ የዛሬ አስር ዓመት ሃገራት የብክለት መጠን ለመቀነስ ቃል የተገቡትን በአግባቡ ተግባራዊ እንዲያደርጉም አስቀድመው ጠይቀዋል።
«ሃገራት ቃል የገቡት የብክለት መጠንን የመቀነስ እቅድ እና ተግባራዊነቱ መካከል የተፈጠረው ክፍተት እንዲጠብ በፍጥነት መንቀሳቀስ ይኖርብናል። ያ ደግሞ እዚህ ቤለም ላይ መጀመር አለበት። በዚህ በCOP 30 ዓለም የዛሬ 10 ዓመት ፓሪስ ላይ የገባውን ቃል እናድስ፤ ይህን አዲስ አስር ዓመት ደግሞ የትግበራና የፍጥነት ጊዜ በማድረግ እንጀምር።»
በዚህ መሀል ታዲያ ሃገራት የየራሳቸውን የትግበራ እቅድ መገምገም ጀምረዋል። በአካባቢ ተፈጥሮ ክብካቤ ረገድ በአዎንታዊ እንቅስቃሴዎቿ የምትታወቀው ጀርመን የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ መቀጠል ካልቻለች በጎርጎሪዮሳዊው 2045 አሁን ካሰበችው የብክለት ቅነሳ ግብ እንደማትደርስ እየተነገረ ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሀገሪቱ መንግሥት ከቅሪተ አጽም ለሚገኘው ጋዝ መሠረተ ልማት ማስፋፋት መጀመሩ ለታዳሽ የኃይል ምንጮችን ለማስፋፋት የነበረውን ቁርጠኝነት አዳክሞታል በሚል ትችት አስከትሎበታል።
COP30ና የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች
በዚህ ጉባኤ ላይ ከተሳታፊና ተደራዳሪዎች በተጨማሪ በአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ ለችግር የተጋለጡ ሃገራት ነዋሪዎችም ድምፃቸውን ሊያሰሙ ተገኝተዋል። በተለይም የአማዞን አካባቢ ነዋሪዎች ለቀናት በባሕር ላይ ተጉዘው በስፍራው መገኘታቸው ትኩረት ስቧል።
በአማዞን ወንዝ ላይ ከሦስት ሳምንታት በላይ ተጉዘው ወደስብሰባው የመጡት የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዋ ሉቺያ ኤክስቺዩ እንደእነሱ ያሉ የየአካባቢው ነዋሪዎችና ተወላጆች ያልተሳተፉበት ማንኛውም የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከተ ውሳኔ ውጤት ሊያመጣ አይችልም ባይ ናቸው።
«ከኤኳዶር ወደ ቤለም ለመድረስ ከ25 ቀናት በላይ በአማዞን ወንዝ ላይ ተጉዘናል። ጥያቄያችን ግልጽ ነው፤ በድርድር ጠረጴዛው ላይ የአካባቢው ነባር ነዋሪዎች በአግባቡ መሳተፍ አለባቸው የሚል ነው። የየአካባቢው ነዋሪዎችና ተወላጆች፣ ሴቶች እንዲሁም ወጣቶች ያልተሳተፉበት የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ውሳኔ መኖር የለበትም።»
ሌላኛዋ ተሳታፊ የኤኳዶሯ የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋች ኤልሳ ኬርዳ በበኩላቸው በጉዟቸው ላይ አየሩ ብቻ ሳይሆን የውኃ አካላትም ምን ያህል እንደተበከሉ ማስተዋላቸውን ተናግረዋል።
«ከኤኳዶር ብራዚል ድረስ በጠጣር ነገሮች ውዳቂ የተበከለውን ባሕር አይተናል። እኛ ከተገኘንባት የውኃዎች እናት በሆነችው ያኩማማ ላይ በደረሰበው ጉዳት ምክንያት ልባችን በሀዘን የተሞላ ትልቅ ጉድጓድ አበጅቷል።»
የብራዚልን ከተማ የመታው የተፈጥሮ አደጋ
የተመድ በየዓመቱ የሚያዘጋጀውን የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ አስተናጋጇ ሀገር ብራዚል ይህን ዓለም አቀፍ ጉባኤ በምታካሂድበት ዋዜማ ከደመና እስከምድር በሚጥመለመል ከባድ አምደ ወጀብ ወይም ቶርኔዶ ተመትታለች። በዚህ የተፈጥሮ አደጋ ቢያንስ አምስት ሰዎች መሞታቸው ሲነገር፤ ከ400 በላይ የሚሆኑት ተጎድተዋል፤ አደጋው የደረሰባት የደቡባዊ ብራዚልዋ ከተማ ፓራና በከፊል ወድማለች። በሰዓት እስከ, 250 ኪሎ ሜትር ይወነጨፍ የነበረው ነጎድጓድ መብረቅ ብርቱ ዝናም እና ወጀብ ተከትሎ ወደ ምድር የሚዘረጋው ኃይለኛው ፈጣን አውሎ ነፋስ 14,000 ሰዎች የሚኖሩባትን ከተማ የጦርነት ቀጣና እንዳስመሰላት የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል። የብራዚል መገናኛ ብዙኀን ያሰራጩዋቸው ምስሎችም በከተማዋ ላይ የደረሰውን ውድመት በገሀድ ያሳያል።
በዚህ መሀል ነው ከ40 እስከ 50 ሺህ የሚገመቱት የCOP30 ተሳታፊዎች 200 ገደማ ከሚደርሱ ሃገራት ወደ ብራዚሏ ቤለም ከተማ መግባት የጀመሩት። የሃገራት መሪዎች በሚገኙበት የተመድ በሚያዘጋጀው 30ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ የወደሙ ደኖችን ለመተካት የተጀመሩ ጥረቶችን የሚያበረታቱ ንግግሮች ይጠበቃሉ።
ቤለም ከተማ ለጉባኤው የተመረጠችበት ዋነኛው ምክንያት በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ በሚገለጸው የአማዞን አካባቢ መገኘቷ ነው። አካባቢው ብራዚል ውስጥ ድኅንነት ከተንሰራፋባቸው ስፍራዎች አንዱ እንደሆነና በተደጋጋሚ ጽንፍ የወጡ የአየር ጠባይ ክስተቶች እንደሚያጋጥሙትም ተገልጿል።
ከተማዋ እንግዶቿን ለማስተናገድ ከፍተኛ ዝግጅት አድርጋለች። ሌላው ቀርቶ በብዙ ሺህዎች ከሚቆጠሩ እንግዶቿ የተወሰኑት አማዞን ወንዝ ላይ በሚንሳፈፉ ሁለት ክሩዝ መርከቦች ውስጥ እንዲያድሩ ልታደርግ ትችላለች ተብሏል።
የብራዚሉ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ እስከ ኅዳር 12 ይቀጥላል። ጉባኤው የአስተናጋጇ ሀገር ፕሬዝደንት ሉላ ደሲልቫም ሆኑ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ባሰቡት መንገድ ይከናወን ይሆን? ጉባኤው ሲጠናቀቅ መልሰን የምቃኘው ይሆናል።
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ























