የባህል አምባሳደርዋ ፍቅርተ ተድላ በግሪክ
Description
«የተሸለምኩት የባህል አምባሳደርነትን ነዉ። የኢትዮጵያን ቱሪዝምን እንዳስተዋዉቅ፤ ወደ ሃገር ቱሪስቶች እንዲገቡ ለማድረግ፤ ይሄን የመሰለዉን የበለጠ እንድሰራበት፤ እና በኢትዮጵያ እና በግሪክ መካከል ባህላዊ ድልድይ እንድዘረጋ ነዉ። ደሞም በደንብም እሰራበታለሁ።» ይህን የነገረችን፤ ፍቅርተ ተድላ ትባባለች፤ በግሪክ መዲና አቴንስ መኖር ከጀመረች ወደ 27 ዓመታት ሆንዋታል። በግሪክ አገር በምትሰራዉ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ በአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ በዶ/ር ሂሩት ካሳው የባህል አምባሳደር ተብላ ሽልማትን ተቀብላለች።
ኢትዮጵያ ሃገሪን ስለምወድ በግሪክ ስኖር የኢትዮጵያን ጥሩ ገጽታ አስተዋዉቃለሁ። ለሃገሬ መስራት የጀመርኩት እዚህ አገር ከመጣሁ ጀምሮ ነዉ ስትል ፍቅርተ ተድላ ነግራናለች። ፍቅርተ ተድላ የባህል አምባሳደር በመባል ሽልማትን የወሰደችዉ፤ በግሪክ ከተማ ዉስጥ የዛሬ መቶ ዓመት ግድም አቢሲያ ተብሎ የተሰየመዉ አደባባይ ስም ይቀየራል የሚል ወሬን ሰምታ ይህን ለማረጋገጥ እና ለማስቀረት ባደረገችዉ ጥረት ነበር። በግሪክ መዲና የሚገኘዉ አቢሲኒያ አደባባይ ተብሎ በኢትዮጵያ ስም የተሰየመዉ አደባባይ ከፍተኛ የንግድ የሚካሄድበት እና በአካባቢው በሚኖሩ ሰዎችና በጎብኚዎች በጣም ተወዳጅ እና መስህብ ያለዉ አደባባይ እንደሆን ይነገራል። አደባባዩ አቢሲኒያ የሚለዉን ስም የወሰደዉ በጎርጎረሳዉያኑ 1922 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ ለስደተኞች ምግብ መግዣ የሚሆን የገንዘብ እርዳታ ከሰጡ በኋላ እንደሆነ የታሪክ ማህደራት ያሳያሉ። ቀደም ባሉት ዓመታት በዚህ አደባባይ ላይ ለብዙ ዘመናት ነጋዴዎች ከእንስሳት እና ከምግብ አንስቶ እስከ ልብስና የመገልገያ መሣሪያዎችን ሁሉ ለመግዛት እና ለመሸጥ አዘዉትረዉ የሚሰበሰቡበት አደባባይ እንደነበር ይነገራል። ዛሬም ይህ አደባባይ በተለይ የጥንታዊ ቁሳቁሶች መሸጫ እንደሆን ይታወቃል። ከ 28 ዓመት ገደማ በፊት በሃገር ፍቅር የባህል ተወዛዋዥ የነበረችዉ እና በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የባህል አምባሳደር ተብላ የተሸለመችዉ ፍቅርተ ተድላ አሁንም ባህል ዉዝዋዜዉን፤ ሃገርን የማስጠራቱን ስራዋን፤ ቀጥላለች። ፍቅርተ ተድላ በአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ በዶ/ር ሂሩት ካሳው ሽልማትን ማግኘትዋ ያልጠበቀችዉ ግን እጅጉን ያስደሰታት እንደሆን ገልጻልናለች።
«በግሪክ መዲና የሚገኘዉ እና አቢሲኒያ አደባባይ ተብሎ የሚጠራዉ አደባባይ በሃገሪዉም ሆነ በዉጭ ጎብኝዎች የታወቀ ቦታ ነዉ። በአሁኑ ወቅት ብዙ የተለያዩ ጥንታዊ እቃዎች የሚሸጥበት ቦታ ሆንዋል። ቦታዉ አቢሲኒያ የተባለዉ የኢትዮጵያዉ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ፤ ለግሪካዉያን እርዳታ ከሰጡ በኃላ እንደተሰየመ ይነገራል። በግሪክ ረሃብ ነበር ለዝያ ነዉ ንጉሱ ግሪክን የረዱት። ይህ የኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ነዉ። ያኮራናል። እኛን ብቻ ሳይሆን፤ ዓለምንም ሳይቀር ነዉ የሚያኮራዉ።» ስትል ፍቅርተ ነግራናለች።
«በግሪክ የኢትዮጵያ ኤንባሲ ወይም ቆንስላ የለም። አንዲት ትዉልደ ግሪካዊት የሆነች የኢትዮጵያን ባህልና ቋንቋ የምትችል ዜጋ፤ ለብዙ ዓመት በግሏ እንደቆንስላ አገልግላ ነበር። ይህ ግን ከተዘጋ ስድስት ዓመት ይሆነዋል። ኢትዮጵያዉያን የኤንባሲ ጉዳይ ስንፈልግ የምንሄደዉ ጣልያን አገር ወዳለዉ የኢትዮጵያ ኤንባሲ ነዉ። እዝያ ነዉ ጉዳያችንን የምናስፈጽመዉ። በግሪክ ሃገር ወደ ሁለት ሽህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዉያን ይኖራሉ። በገጠርም የሚኖሩ አሉ። አብዛኞቹ የሚሰሩት በቤት ሰራተኝነት በምግብ ቤት፤ አልያም ወጣ ብለዉ በእርሻ ላይ ነዉ። እርሻ ላይ የደረሰ ድንች፤ ቲማቲም፤ ካሮት አልያም የወይራ ፍሬ ይለቀማል። በበጋ ሞቅ ሲል ስራ ይገኛል ይሁንና የስራ ፈቃድ ያስፈልጋል። ግሪክ አሁን ለስደተኞች የመኖርያ ፈቃድ መስጠት አቁማለች። እንደዉም እያስወጣች፤ እያባረረች ነዉ። የስደተኛዉ ኑሮ እጅግ ያሳዝናል። በእርግጥ በህክምና ሞያ፤ አልያም ሌሎች ትልልቅ ስራዎችን የሚሰሩ ኢትዮጵያዉያንም አሉ። እኔ አሁን የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብን እና እቃዎችን ከኢትዮጵያ አምጥቼ የምሸጥበት የራሴ ሱቅ አለኝ» ስትል የባህል አምባሳደርዋ ፍቅርተ ተናግራለች።
ግሪክ እንደሚታወቀዉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ናቸዉ። በሃገሪቱ ብዙ ገዳማት አሉ ገዳማት ዉስጥ ሲገባ ልክ ኢትዮጵያ እንዳሉ ሁሉ ይሰማል። ኢትዮጵያዉያንም ኪዳነምህረት የምትባል የራሳቸዉ ገዳም አላቸዉ በብዙ ኢትዮጵያዉያን ይጎበኛል።» በግሪክ መዲና አቴንስ ዉስጥ ነዋሪ የሆነችዉ ኢትዮጵያዊትዋ የባህል አምባሳደር ፍቅርተ ተድላ ይህን ቃለ ምልስ የሰጠችን በዓመቱ እንደምታደርገዉ ሁሉ የጎርጎረሳዉያኑ አዲስ ዓመት እና የገና በዓል ሊደርስ ሲል በግሪክ ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር በመሆን በዓለም ላይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸዉ ህጻናት የገንዘብ ማሰባሰብያ ዝግጅት ላይ ለመሳተፍ ስራ ላይ ሳለች ነበር። ፍቅርተ ተድላ ለሰጠችን ቃለ-ምልልስ እያመሰገንን ሙሉዉን ዝግጅት እንዲad,ምጡ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ























