የትራምፕ አስተዳደር አዳዲስ የስደተኞች ፖሊሲዎችና አንደምታቸው
Description
ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣በቅርብ ጊዜ ከወሰዳቸው ጥብቅ የስደተኞች ፖሊሲዎች መኻከል፣ ወደ አሜሪካ በየዓመቱ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ለመገደብ የወሰደው እርምጃ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው።
አሜሪካስደተኞችን መቀበል ከጀመረች ከ45 ዓመታት ወዲህ አነስተኛ ቁጥር በተባለው የስተዳደርሩ ዕቅድ መስረት፣በሚቀጥለው ዓመት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ሰባት ሺ 500 ብቻ ይሆናል።
ከዚህ ውስጥም፣አብዛኛው ድርሻ ለነጭ ደቡብ አፍሪቃውያን ቅድሚያ እንደሚሰጥአስተዳደሩ አስታውቋል። የትራምፕ አስተዳደር ቅነሳው በሰብዓዊ ጉዳዮች ወይም ለሃገር ጥቅም የሚውል ነው ብሏል።
የህግ ባለሙያው እይታ
በቨርጂኒያ ግዛት የህግ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ፍጹም አቻምየለህ፣በአስተዳደሩ እየተወሰዱ ያሉ ዋና ዋና የፖሊሲ እርምጃዎችን በተመለከተ ተከታዩን ማብራሪያ ለዶቼ ቬለ ሰጥተዋል።
''ጊዜያዊ የመቆያ ፈቃድ የተሰጣቸው አገሮች ነበሩ፣ እሱም እየቆመ ነው። የኤይቲ፣የሱዳን፣የዩክሬንና የአፍጋኒስታን፣ እንግዲህ በዚህ ከቀጠለ ለኢትዮጵያውያንም የተፈቀደው ጊዜያዊ የመቆያ ፈቃድ ይቆማል የሚል ስጋት አለ። ''የአሜሪካ አስተዳደር፣ለደቡብ ሱዳን ዜጎች ተሰጥቶ የነበረውን፣ ጊዜያዊ የመቆያ ፈቃድን በቅርቡ እንዳቆመው ይታወቃል። በዚህ ምክንያት፣በሺህዎች የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ዜጎች፣በጦርነት ምክንያት ከሀገራቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊነት በአሜሪካ እንዲኖሩ ያስችላቸው የነበረ ፈቃዳቸው ይሰረዛል።
በጠበቆች ላይ የተፈጠው ጫና
ሌሎች፣ በአስተዳደሩ የተወሰዱ የስደተኞች ጉዳይ ፖሊሲዎችእና አንደምታቸውን በተመለከተ፣የህግ ባለሙያው ያስረዳሉ። ''ጥገኝነት ያመለከቱ ሰዎች፣እያንዳንዱ አመልካች የቤተሰብ አባል ጭምር፣በየዓመቱ መቶ ዶላር መክፈል አለበት። በ ትንሽ የስርቆትም ሆነ የድብደባ ወንጀል የተከሰሰ ሰው፣ በሌከን ራይሊ ህግ መሰረት፣ከዚህ አገር እንዲባረር ወይም ደግሞ ታስሮ እንዲቆይና እንዲባረር የሚያደርግ ህግ ወጥቷል። ሃገራቸው አልቀበል ያላቸውን ሰዎች ወደ ሦስተኛ ሀገር መላክ፤ለምሳሌ ደቡብ ሱዳን፣ሩዋንዳ መላክ። ወደ ሰባ የሚሆኑ የኢሚግሬሽን ዳኞችን በተለይ፣ ከጥብቅና ሙያ ተመርጠው እዚያ የገቡ ዳኞችን ለስደተኞች ይረዳሉ በሚል ዳኞችን አባሮ ከጦር ፍርድ ቤት ዳኛ እና አቃቤ ህግ የነበሩ ሰዎችን አምጥቶ ሾሟል። የዜግነት ማመልከቻዎችን በተመለከተ መስፈርቱ እንዲጠብቅ፣ እንዲሁም አሁን እንደሰማሁት፣የአመልካቾች ሰፈርና ቤት እየሄዱ መጠየቅ ሊጀመር እንደሆነ ሰምተናል። '' ብለዋል።ከዚህ አኳያ አሁን በአሜሪካ የሚታየው አሰራር፣ለስደኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ብቻ ሳይሆን፣ለህግ ባለሙያዎች ጭምር ፈታኝ ሁኔታ ይዞ መምጣቱን ዶክተር ፍጹም አመልክተዋል።
''ለጠበቃ የሚመች ሁኔታ አይደለም ያለው። ጠበቆች ለደንበኞቻቸው ውጤት ማምጣት ይፈልጋሉ፤ ደንበኞች ውጤት ይጠብቃሉ፣ግን ያለው የኢምግሬሽን ሁኔታ፣ ውጤት ተኮር ስለሆነ ስራችን ደምበኛ የፈለገውን ነገር ማግኘት ያስቸግራል። እዚህ አገር ብቻ የሚያመለክተው ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡን ለማምጣት የሚጠብቀው ሁሉ፣ በተለያየ ምክንያት እንዲዘገይ እየተደረገ ነው። በተለይ እዚህ አገር ሆኖ፣እነዚህን ማመልከቻዎች አመልክቶ በፊት የምታቀርበው መረጃ እና ማስረጃ በቂ አይሆንም ማለት ነው። በእዛ ላይ፣ቶሎ በጊዜ ለቃለ መጠይቅ አትጠራም። በተለይ የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ያሉት ዳኞች ተቀባይ የሚሆኑ፣ለአመልካቹ መልካም የሚሆኑ አይደሉም።፣አሁን አሁን እየተሾሙ ያሉት ዳኞች። ሰባ የሚሆኑ መልካም ዳኞች ተባረዋል እና ለጠበቃ በጣም መጥፎ የሆነበት ደረጃ ላይ ነው ያለነው። የጠበቆችንናም ስራ ከባድ የሆነበት እንደውም ብዙ የሚሟገቱ ጠበቆችን ሁሉ ማስፈራሪያ ከዋይት ሐውስ ድረስ የሚደርሳቸው ሁኔታ ላይ ነው ያለነው። ''ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣እንደገና ተመርጠው ወደ ነጩ ቤተመንግሥት ከገቡባት ዕለት ጀምሮ፣የተለያዩ ስደተኞችን የተመለከቱ ፕሬዚዳንታዊ ትህዛዞችንና ፓሊሲዎችን እየተገበረ መሆኑ መሆኑ ይታወቃል።
ታሪኩ ሀይሉ
ታምራት ዲንሳ
ፀሀይ ጫኔ























