የአውሮፓ ሕብረት ውሳኔና በልጅየም ተቃውሞ
Description
ባለፉት አመታት የቀጠለውንየሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም ከአሜሪካ በቀረበ የሰላም እቅድ መነሻነት ሰሞኑን ጥረት ሲደረግ የቆየና አሁንም ጥረቱ እንዳለ ቢታወቅም ጦርነቱን ግን እስካሁን ማስቆም ቀርቶ ማብረድ አልተቻለም።
እንደውም በአሁኑ ወቅት ዩክሬን በጦርነቱ ብዙም እንዳልቀናት ብቻ ሳይሆን፤ በውስጧም በሙስና ምክንያት የፖለቲካ ቀውስ እንዳጋጠማትና ከሁሉም በላይ ግን በከፍተኛ የፋይንናስ ችግር ውስጥ እንደሆነች ነው የሚነገረው።
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ዩክሬንን ለመታደግና በተለይም ከሩስያ ጋር በሚደረገው ድርድር ጠንካራ ሆና እንድትቀርብ፤ በኢኮኖሚ፣ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እየገለጸ ነው። የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ኦርዙላ ፎንዴር ላየን ባለፈው እሮብ ዩክሬን እአአ በ2026/27 የበጅት አመት ከሚያስፈልጋት 140 ቢዮን ዩሮ ውስጥ ሶስት አራተኛውን ማለት 90 ቢዮን የሚሆነውን ለመሸፈን የሚያስችል ነው ያሉትን ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።
“ የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ እንዳይንቀሳቀስ ከታገደ ተቀማጭ ገንዘብ ወጭ የሚሆን ወይም በማያዣነት በመጠቀም ለዩክሬን የ90 ቢሊዮን ዩሮ የመቋቋሚያ ብድር (reparation loan) ይፋ ያደርጋል” በማለት ህብረቱ ለዩክሬይን የሚሰጠውን ድጋፍ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የመቋቋሚያ ብድር ( reparation loan ) ምንድን ነው?
የመቋቋሚያ በድር ወይም (reparation loan) የሚባለው ዩክሬይንን ለመርዳት በአውሮፓ ባንኮች ታግዶ የሚገኘውን የሩሲያ 210 ቢልዮን ዩሮ ለመጠቀም የሚያስችል የአውሮፓ ፕሮግራም ሲሆን ከዚህ ውስጥ 140 ቢልዮን ዩሮው በቤልጀየም ዩሮ ክሊር የገንዘብ ተቋም የሚገኝ መሆኑ ታውቋል። የቤልጀም መንግስት ግን ተቀምጦ ያለን የሌላ አገር ገንዘብ አሳልፎ መስጠት በህግ ያሚያስጠይቅና ባለዕዳም ሊያደርግ የሚችል ነው በማለት ዕቅዱን ተቃውሞታል።
የቤልጅየም ቃውሞ ምክንያትና ህጋዊ መሰረቱ
የቤልጅየም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ማክሲመ ፕሬቮት፤ ወይዘሮ ፎን ዴር ላየን እቅዱ ይፋ ማድረጋቸውን ተክትሎ በሰጡት መግለጫ የመግስታቸውን አቁም ግልጽ አድረገዋል፤ “ ይህ የመቋቋሚያ ብድር ወይም ሪፓሬሽን ሎን ፕሮግራም የህግ ክፍተት ያለበት፤ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ቀውስ ሊያስክተል የሚችል ነው” በማለት ከዚህ በፊት ተሞክሮ የማያውቅ ብዙ ችግር ያለበት ዕቅድ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህን የቤልጀየም ተቃውሞና ክርክር ህጋዊ መሰረት ያለው ስለመሆኑ እንዲያስረዱን በሉቨን የካቶሊክ ዩንቨርስቲ የፋይናንስ ህግ መምህት የሆኑትን ፕሮፌሰር ቬርለ ኮላርትን ዶይቼቨለ ጠይቆ ነበር፤ «በትክክል ህጋዊ መረት አለው። ሁለት ጭብጦችን ነው ያነሳው የቤልጅየም መንግስት፤ አንደኛው በመርህ ደረጃ ዩክሬይን ከጦርነቱ በኋላ ከሚከፈላት ካሳ ብድሩን መክፈል ያለባት መሆኑ ቢገለጽም፤ በተጨባጭ ግን ይህ ሊሆን እንደማይችልና ጦርነቶች ሲያበቁ ወይም ሲቆሙ በአንደኛው አለም ጦርነት ጀርመን ፈጽሞ ስትሸነፍ ከከፈለችው ካሳ ውጭ ለሌላ ተከፍሎ እንድማይውቅ፤ በዚህ መሰረትም ዩክሬይን ካሳ ማገኘቷ አስተማማኝ ባለመሆኑ ብድሩን የመክፈል ግዴታ ስለማይኖርባት የቤልጀይም መንግስት ዋስትና መጠየቁ ተገቢም ህጋዊም ነው» ብለዋል።
ሌሎች ዩክሬይንን ለመርዳት የሚያስችሉ አማራጮች
የዩክሬን ችግር ግን አጣዳፊና ይህ ገንዘብም መንግስታዊ ስርአቷን ለማሰቀጠል የሚያስፈልግና እያካሄደች ላላው ጦርነትም ወሳኝ ነው እየተባለ ነው።፡ ከዚህ ከህብረቱ እቅድ ውጭ ሌላ ህብረቱ ዩክሬይንን ሊደግፍ የሚችልበት አማራጭ ምን ሊሆን ይችላል የተባሉት ፕሮፌሰር ኮላርት፤ “ሁለት የመፍትሄ ሀሳቦች አሉ፤ አንደኛው አማራጭ አባል አገሮች የጋራ ብድር ወስደው ለዩክሬን ማቅረብ ነው። ይህ ግን ወለድ ያለውና መንግስታትን ብዙ ወጪ የሚያስወጣ በመሆኑ ላይፈልጉት ይችላሉ። ሁለተኛው አማራጭ ለቤልጅየም መንግስት ዋስትና መስጠት ቢሆንም ይህንንም አባል አገራቱ ላይቀበሉት ይችላሉ” በማለት ህብረቱ የገባበትንም አጣብቂኝ አውስተዋል።
በታገደውና ለዩክሬን መርጃ እንዲሆን በታሰበው የሩሲያ ገንዘብ ላይ የአሜሪካ አቋም
ቤልጅየም ይህን ዋናዎቹ የህብረቱ አገሮች እየገፉበት ያለውን እቅድ እንድትቀበል ግፊት እየተደረገባት ሲሆን፤ ምን ያህል እንደተሳካላቸው ባይታወቅም የጀርመኑ ቻንስለር ፌሬዴርሽ ሜርስ በትናንትናው እለት ብራስልስ በምመጣት ከጠቅላይ ሚኒስትር ባርት ዌቨር ጋር በዚሁ ጉዳይ መነጋገራቸው ታውቋል።አሜሪካ ግን በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ ታግዶ ያለውን የሩሲያን ገንዘብ ለዩክሬይን ማስተላለፍ የሰላም ጥረቱን ሊያደናቅፍ ይችላል በማለት አገሮች ዕቅዱን እንዳይደግፉት እያግባባች መሆኑን ጋዜጦች እየዘገቡ ነው። ይህ ከቤልጅየም ተቃውሞ የገጠመውና አሜሪካኖቹም ድጋፋቸውን ነስተውታል የተባለው የአውሮፓ የዩክሬይን መርጃ እቅድ፤ በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ዋና አጀንዳ ሆኖ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ገበያው ንጉሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር























