የኢራንና የዓለም የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት ዉዝግብ
Description
ባለፈዉ ሰኔ የእስራኤልና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይላት የደበደቧቸዉን የኢራንን የኑክሌር ተቋማት መፈተሽ አለመቻሉን የዓለም የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት (IAEA) አስታወቀ።መጀመሪያ የእስራኤል ኋላ የዩናይትድ ስቴትስ የጦር አዉሮፕላኖችን ኢራንን መደብደባቸዉ ምክንያት ዓለም አቀፉ ድርጅት የኢራንን የኑክሌር ተቋማት መፈተሹን አቋርጦ ነበር።የኢራንና የተቆጣጣሪዉ ድርጅት ባለሥልጣናት በቅርቡ ባደረጉት ሥምምነት ግን የድርጅቱ ባለሙያዎች አንዳድ የኑክሌር ተቋማትን መፈተሽ ችለዋል።የእስራኤልና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይላት የደበደቧቸዉን ተቋማት ግን መፈተሽ አልቻለም።
የእስራኤልና የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች የድል ብሥራት ማግሥት ዕዉነት
የእስራኤል ባለሥልጣናት«የኢራንን የኑክሌር ማብላያ ተቋማትን ለማጥፋት» ባሉት ወታደራዊ ዘመቻ ባለፈዉ ሰኔ ኢራንን መደብደባቸዉና ኋላ ዩናይትድ ስቴትስ በተሞጀረችበት የ12 ቀናት ጦርነት በርካታ የእስራኤልና የኢራን ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ጠፍቷል።የእስራኤል መሪዎች መጀመሪያ ላይ እንዳሉት የኢራንን ሥርዓት እስከማስወገድ ያለመዉ ወታደራዊ ዘመቻ ግቡን ቢስትም የኢራንን የኑክሌር መርሐ-ግብር ማዉደማቸዉን የእስራኤልም፣ የአሜሪካም መሪዎች አረጋግጠዉ ነበር።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ።ሰኔ 22፣ 2025 (እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር)
«ዛሬ ማታ ለዓለም መዘገብ እችላለሁ።የኢራን ዋና ዋና የኑክሌር ማብላያ ተቋማት ሁሉምና ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።»
የዓለም የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት (IAEA) ከሶስት ወር በኋላ ባለፈዉ መስከረም ባወጣዉ መግለጫ ግን ኢራን 440.9 ኪሎ ግራም የሚመዝን የተብላላ የዩራኒየም ክምች እንዳላት አስታወቀ።ድርጅቱ እንደሚለዉ የኢራን የዩራኒየም ክምችት 60 በመቶ የነጠረ ወይም የተብላላ ነዉ።ኑክሌር ቦምብ ለማምረት ዩራኒየሙ 90 በመቶ መንጠር ወይም መብላላት አለበት።
ከቴክኒካዊ ማብራሪያዉ ይልቅ እዉነቱ ያለበትአለመታወቁ ወይም ዋሾዎች አለመለየታቸዉ ግን በሐቅ ፈላጊዎች ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል።ትራምፕ ሰኔ ላይ፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ ደግሞ መስከረም ላይ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እንደተናገሩት የኢራን የኑክሌር ማብላያ ሁሉምና ሙሉ በሙሉ ከወደመ 60 በመቶ የተጣራዉ ዩራኒየም ከየት መጣ?
ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለማምረት አልሞከረችም-ግሮሲ
ኢራን በበኩሏ ከጦርነቱ በኋላ የኑክሌር ተቋማቷን አላስፈትሽም ሥትል ነበር።ለምን? ከብዙ ጫና፣ማስፈራራትና ማዕቀብ በኋላ ግን ለማስፈተሽ ፈቅዳለች።የዓለም የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት ዳግም ፍተሻ ከጀመረ በኋላ ባለፈዉ ጥቅምት ማብቂያ የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ እንዳሉት ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለመስራት እየሞከረች አይደለም።በፊትም አልሞከረችም።
«እነሱ (ኢራኖች) የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለማምረት እየሰሩ ሥለመሆናቸዉ ታዉቃላችሁ ወይ ነዉ ያልከዉ? አይደል? (እየሰሩ) አይደለም።እየሰሩም አልነበረም።በዚሕ ጉዳይ ላይ በጣም ግልፅ መሆን እፈልጋለሁ፣ ምክንያቱም ይሕን በተመለከተ ብዙ ጊዜ በሐሰት እንጠቀሳለን።ሰዎች ደግሞ ያላልነዉን ያልን ይመስላቸዋል።»
ግሮሲ የሚመሩት ድርጅት ትናንት እንዳለዉ ግን ባለሙያዎቹ እንዲፈትሹ ኢራን የፈቀደችዉ ሌሎች የኑክሌር ተቋማቷን እንጂ እስራኤልና የዩናይትድ የደበደቧቸዉን ተቋማት አይደለም።የዓለም የአቶሚክ ተቆጣጠሪ ድርጅት ትናንት ባሰራጨዉ ሰነድ እንደሚለዉ ኢራን ሁሉንም የኑክሌር ተቋማቷን ማስፈተሽ አለባት።
የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴርቃል አቀባይ ኢስማኢል ባጋሊ ባለፈዉ ሰኞ እንዳሉት ግን «ፅዮናዊት» ያሏት እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ የኑክሌር ተቋማቱን በመደብደባቸዉ የዓለም አቀፉ ተቆጣጣሪ ድርጅት ተቋማቱን ማየት የሚችሉት በኢራን ላዕላይ ብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት ባልደረቦች ታጅበዉ ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ























