DiscoverDW | Amharic - Newsየዓይን ብርሃንን ይመልሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አዲሱ ቴክኖሎጂ
የዓይን ብርሃንን ይመልሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አዲሱ ቴክኖሎጂ

የዓይን ብርሃንን ይመልሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አዲሱ ቴክኖሎጂ

Update: 2025-11-12
Share

Description

በዓለማችን 300 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የማየት ችግር እንዳለባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።ምስጋና ለቴክኖሎጂ ይግባው እና የማየት ችግር የገጠማቸውን ሰዎች የዕለት ተዕለት ህይወት ለማቃለል የሚረዱ ቴክኖሎጂዎች ከጊዜ ጊዜ እየተሻሻላ መጥተዋል። የዓይን ብርሃንን ለመመለስ የሚደረጉ ተስፋ ሰጪ ምርምሮችም በዚያው ልክ እየጨመሩ ናቸው። በቅርቡ በተካሄደ ምርምርም ፤ትንሽ ነጥብ የምታህል በጣም አነስተኛ ቁስ (ቺፕ) እና ልዩ የዓይን መነጽሮች አማካኝነት እይታን ወደነበረበት ለመመለስ እና ለማሻሻል ያስችላል የተባለ ተስፋ ሰጪ ሙከራ ተደርጓል።



ከዕድሜ ጋር ተዛማጅነት ላላው የዓይን ችግር የሚያገለግል ነው



ይህ አነስተኛ ቁስ ወይም ችፕ የሚያገለግለው ከዕድሜ ጋር ተዛማጅነት ላላው እና «ማኩላር ዲኔሬሽን» በመባል ለሚታወቀው የዓይን ሕመም ሲሆን፤ይህ በሽታ «ሬቲና» የተባለውን የዓይን ክፍል የሚጎዳ ነው።እንደ ተመራማሪዎቹ ገለፃ በዩናይትድ ስቴትስ፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያ፣ ኔዘርላንድስ እና ጣሊያን በሚገኙ የሙከራ ጣቢያዎች ከ80% በላይ የሚሆኑ ታካሚዎች ከአንድ አመት ክትትል በኋላ ከፍተኛ የእይታ መሻሻል አሳይተዋል ተብሏል።የዓይን ሀኪም እና የሬቲና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ትልቅ ሰው ተሾመ ጥናቱ ተስፋ ሰጪ ነው መባሉን ይገልፃሉ።ተመራማሪዎቹ አያይዘውም፤ ይህን በጣም አነስተኛ ቁስ በቀዶ ጥገና ዐይናቸው ውስጥ ከተቀበረላቸው ወዲህ ፣የማየት እክል የገጠማቸው ሰዎች በቤት ውስጥ ቁጥሮችን እና ቃላትን ማንበብ ችለዋል።በመደበኛ የዓይን ምርመራ ላይ ይህ የንባብ አቅማቸውን ወደ 25 ፊደሎች ወይም ወደ አምስት መስመሮች ማሻሻል ይችላሉ ተብሏል።



የማየት ዕድልን በ50 በመቶ ያሻሽላል



ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ዕይታቸው 20/20 ከሚባለው መደበኛ የማየት ችሎታ በግማሽ በቀረበ መልኩ ወይም 50 በመቶ ተሻሽሏል ተብሏል።«ለዕለት ተዕለት ኑሮ ጠቃሚ በሆነው ዓይነ ስውነትን ሬቲና በሚባለው የዓይን ክፍል ውስጥ ዕይታን ወደነበረበት መመለስ እንደሚቻል የታየው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው» ሲሉ ፤የጥናቱ መሪ እና የቦን ዩኒቨርሲቲ የዓይን ህክምና ሀላፊ ፍራንክ ሆልዝ ለDW ተናግረዋል።ያም ሆኖ ውስኑነቶች እንዳሉት ዶክተር ትልቅ ሰው ገልፀዋል።ባለሙያዎች እንደሚሉት አንዳንድ ሰዎች በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ፣ ለማዕከላዊ እይታ የሚያገለግለው «ማኩላ» የተሰኘው የሬቲና ክፍል እየተጎዳ ሊሄድ ይችላል፣ ይህም በመጀመሪያ የእይታ ብዥታ ከዚያም ወደ ቋሚ ጉዳት ሊያመራ ይችላል።



የዓይን ብርሃንን ወደነበረበት ለመመለስ ይረዳል





አንድ ጤነኛ አይን ስራውን የሚያከናውነው ብርሃንን ከውጭ በመቀበል ወደ ኤሌክትሪካዊ ምልክቶች ወይም ሲግናሎች ይቀይራል። ከዚያም ይህንን ምልክት ወይም «ሲግናል» በኦፕቲክ ነርቭ አማካኝነት ወደ አንጎላችን ለትርጉም እንዲላክ በማድረግ ማየት እንድንችል ያደርጋል። ማኩላር ዲግሬሽን ግን ይህንን የተለመደ የዓይን ተግባር በማደናቀፍ የማየት አቅምን ይቀንሳል።ይህ ችግር፤ በአረጋውያን ላይ የዓይን ብርሃን ማጣት ዋነኛ መንስኤ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢያንስ አምስት ሚሊዮን ሰዎች በዚህ በሽታ ተጠቅተዋል።

በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዩኤስ የአይን ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዳንኤል ፓላንከርን የአንዲት እስፒል ራስ መጠን ያለው ቺፕ ሬቲና ውስጥ በመቅበር ይህንን ጉዳት ለመመለስ እና መፍትሄ ለማምጣት የአሁኑን ምርምር አካሂደዋል።ቴክኖሎጂውን ለማዳበር ከፒትስበርግ የህክምና ትምህርት ቤት ከፈረንሳዊው የአይን ባለሙያ ጆሴ-አሊን ሳሄል ጋር ተባብረዋል። ባለሙያው ዶክተር ትልቅሰው ምርምሩ ከተሳካ አዲሱ ህክምና በዋጋ ደረጃ ውድ ነው ይላሉ።ያ መሆኑ መሆኑ ደግሞ፤ በችግሩ ሰለባ ለሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው የሚል ስጋት አላቸው። እሳቸው እንደሚሉት ዋጋው ሀብታም ለሚባሉት ሀገራትም ጭምር ከፈተኛ ነው።



የሚቀበረው ችፕ ያልሞቱ የዓይን ህዋሳትን ይፈልጋል



ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ሬቲና ውስጥ የሚቀበረው አነስተኛ ቺፕ የህዝብ ስጋት አስተዳደር ማህበር (PRIMA) ከሚያስቀምጠው መስፈርት ግማሽ ያህል ብቻ የሚይዝ ነው።ሌላኛውን ግማሽ የሚይዘው ልዩ የዓይን መነፅር ነው። ይህ መነፅር ምስላዊ መረጃን የሚያስተላልፍ ካሜራ የተገጠመለት ሲሆን፤ ለመጠቀም በእጅ የሚያዝ ፕሮሰሰርንም ይጨመራል። በዚህ ሁኔታ ከፍተኛ ጥራት ያለው ምስል እና መረጃውን ወደ አንጎል እንዲደርስ ይደረጋል።ለዚህም የታካሚውን ያልተጎዱ የሬቲና የሚባለውን የዓይን ክፍል ህዋሳት ይጠቀማሉ። ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ሬቲና ውስጥ ያሉት ሁሉም ህዋሶች ከሞቱ ግን የሚቀበረው ችፕ የመስራት ዕድል የለውም።

ተመራማሪዎቹ ሳሄል እና የስታንፎርዱ ፓላንከር በጎርጎሪያኑ በ2012 ዓ/ም በአንድ ስብሰባ ላይ ሲገናኙ ተመሳሳይ ችግር ለመፍታት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመስራት ላይ ነበሩ።ያኔ ከበርካታ ታካሚዎች ጋር ትንንሽ



ጥናቶችን በተናጠል ያካሂዱ ነበር። በኋላ ግን ከ ሀብታቸውን እና ስራዎቻቸውን በማዋሃድ ከ30 በላይ በሆነ ጊዜ ትልልቅ ሙከራዎችን አካሂደዋል።ነገር ግን ጥናቱ PRIMA የተባለው ኩባንያ በ2024 ዓ/ም ከንግድ ስራ ሲወጣ ውድቅ ሊሆን ተቃርቦ እንደነበርም ገልፀዋል።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምርቱን የአሜሪካው ኩባንያ ሳይንስ ኮርፖሬሽን ተረክቦታል። አሁን ተመራማሪዎቹ ከምግብ እና መድሀኒት አስተዳደር (ኤፍዲኤ) መድሃኒቱን በአሜሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ ለማዋል ፈቃድ በመጠየቅ ላይ ናቸው።በአውሮፓ ጥቅም ላይ ለማዋል ደግሞ የ CE የተባለውን የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለማግኘት እየጣሩ ነው።በምርምሩ የመጣው ውጤት እንደ ትልቅ ግኝት የሚቆጠር ነው የሚሉት ዶክተር ትልቅሰው፤ የቀሩትን ጉድለቶችንም በቀጣይ የምርምሩ ሂደቶች ሂደቶች ማሻሻል ይቻላል ብለዋል።ነገር ግን ከሌሎች አንፃር አዲሱ ምርምሩ ጠባብ እና ገና ነው የሚል እምነት አላቸው።ከዚህ አንፃር አሁን በመሰጠት ላይ ያሉ ህክምናዎች የበለጠ ጠቃሚ ናቸው ብለዋል።



ሙከራውን በበርካታ ሀገራት እና ጣቢያዎች የማካሄድ ዕቅድ



ሙከራውን በበርካታ ሀገራት እና ጣቢያዎች በማካሄድ፣ በሁሉም ቦታዎች ተቀባይነት እንደሚኖረው የሙከራ ቡድኑ ተስፋ አድርጓል።ቴክኖሎጂውን በአንድ ወይም በሁለት ችሎታ ባላቸው የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ብቻ የተገደበ እንዳይሆን ማድረግ ያስፈልጋል፤ የሚሉት ተመራማሪዎቹ፤በዚህም በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ታካሚዎች ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ገልፀዋል።እናም ተመራማሪዎች እንደዚህ ያሉ አስቸጋሪ ስራዎች በአይን ቀዶ ጥገና ሐኪሞች በተሳካ ሁኔታ ሊከናወኑ እንደሚችሉ ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በአንዳንድ ታካሚዎች ላይአንዳንድ አሉታዊ ተጽእኖዎች ሪፖርት የተደረጉ ቢሆንም እነዚህ በ 12- ወራት የጥናት ጊዜ መጨረሻ ላይ መፍትሄ ማግኘታቸውን አመልክተዋል።በ13 የተለያዩ ጣቢያዎች እና የተለያዩ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ተሞክሮ ውጤቱ ወጥነት እንዳለው ታይቷልም ብለዋል። ይህም በተጨማሪ ማዕከላት እና ታካሚዎች መሞከር እንዳለበት የሚያመለክት መሆኑንም ገልፀዋል።



ቀዶ ጥገናው፡ቀላል አይደለም.



ዶክተር ትልቅ ሰው ከጠቀሷቸው ባሻገር የጥናቱ ባለቤቶች ሳሄል እና ሆልዝም በአዲሱ ቴክኖሎጂ ላይ ተግዳሮቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።ከነዚህም መካከል ቺፑን ለመትከል የተደረገው ቀዶ ጥገና በአለም ዙሪያ በበርካታ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ ቢሆንም፣ ቀዶ ጥገናው ቀላል እንዳልሆነ ለDW ተናግረዋል። ቀዶ ጥገናው ጥሩ ችሎታ የሚያስፈልገው እና በጣም ውስብስብ መሆኑን ገልፀዋል።ሌላው ተግዳሮት ታካሚው ላይ ሲሆን፤ ከቀዶ ጥገና በኋላ ለማገገም ወደ ክሊኒክ በተደጋጋሚ መመላለስ እና በቤት ውስጥም ድጋፍ የሚያስፈልገው በመሆኑ በታካሚ ምቾት ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል።



ሆልዝ እንደተናገሩት ህክምናው የተደረገለት ሰው ከቀዶ ጥገና በኋላ ቀጣይነት ያለው ክትትል ለማድረግ ፍቃደኛ መሆን አለበት።ህክምናውን በተሳካ ሁኔታ ለመጠቀምም ካሜራውን እና ፕሮሰሰሩን እንዴት እንደሚሰራ መሰልጠንአለበት።ይህ የህክምና ሂደት በአሁኑ ጊዜ 12 ወራት አካባቢ ይወስዳል ሲሉም ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል።ዶክተር ትልቅ ሰው ግን በአሁኑ ወቅት የማየት ችግር ያለባቸውን ሰዎች በሚያግዙ ተመጣጣኝ ዋጋ ባላቸው ቴክኖሎጂዎች ላይ ማተኮር ለጊዜው የተሻለ መፍትሄ መሆኑን አስረድተዋል።



ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።



ፀሐይ ጫኔ

ታምራት ዲንሳ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የዓይን ብርሃንን ይመልሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አዲሱ ቴክኖሎጂ

የዓይን ብርሃንን ይመልሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አዲሱ ቴክኖሎጂ