የፕሬዚዳንቱ ጉዞ መቀሌ እና አዲስ አበባን ያቀራርብ ይኾን?
Description
የጄነራል ታደሰ ወረደ ጉዞ እና አንድምታው
በመቀሌና በአዲስ አበባ መካከል ያለው ፖለቲካዊ ቁርቁስ ሊረግብ ወደሚችልበት አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረ መስሏል። የጄነራል ታደሰ ወረደ የአዲስ አበባ ጉዞ ፣ የሕወሓት ኤርትራ "ጽምዶ" ስልታዊ ጥምረት ክስ እና የትግራይ ፖለቲከኞች ስጋት ፤ የሰላም ስምምነቱን አደጋ ላይ የጣለው አዲሱ የጂኦ-ፖለቲካ ጨዋታ እና አንድምታው በዛሬው ማኅደራችን ከብዙ በጥቂቱ ይገለጥበታል።
ፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደ በይፋ ካልተገለጸው የአዲስ አበባ ጉዟቸው አስቀድሞ ፣ በመቀሌ ቤተ-መንግስት ሰማዩ የጠቆረበት ወቅት ነበር። ፕሬዚዳንቱ በይፋ ወዳልተገለጸው የአዲስ አበባ ጉዟቸው ከማምራታቸው በፊት፣ የክልሉን የጸጥታ ኃይሎች እስከ ቢሯቸው ድረስ ያመጣ፣ በውጥረት የተሞላ ጊዜ እንዳሳለፉ ይነገራል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርም ሆነ የፌዴራል መንግስቱ ፤ ፕሬዚደንት ታደሰ ወረደ ወደ አዲስ አበባ ስላደረጉት ጉዞም ኾነ ስለተደረጉ ንግግሮች አንድምታ እና ዉጤት ያሉት ነገር የለም።
በአዲስ አበባ እና በመቀሌ መካከል ተካሮ የቆየውእሰጥ አገባ ሌላ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ስጋት እስከ ማሳደር በደረሰበት ወቅት የፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደ ወደ መሃል ሀገር የመጓዝ አንድምታውን መጠየቃችን አይቀርም። ዶቼ ቬለ ከአንዳንድ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ጠይቆ እንደተረዳው የፕሬዚዳንቱ ጉዞ በነዋሪዎች ዘንድ በተወሰነ መልኩ መረጋጋትን የፈጠረ ፤ የነበረውን መካረረ እንዳለዘበ ነው።
በትግራይ የፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት አቶ ዳንኤል ብርሃነ እንደሚሉት ግን የፕሬዚዳንቱ ጉዞ የአዲስ አበባ እና የመቀሌ ግንኙነትን ለማደስ «ይጠቅማልም አይጠቅምም » ለማለት ያስቸግራቸዋል።
"...በመሰረታዊነት የመተማመን ችግር ነው... መተማመን በአንድ ቀን፣ በአንድ ጉዞ፣ በአንድ ንግግር አይደለም የሚፈጠረው። ሂደት ይጠይቃል።"
በሌላ በኩል፣ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጉዞው ላይ ያላቸው እምነት ዝቅተኛ ነው። የሳልሳይ ወያነ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃነ አጽብሃ፣ የፕሬዚዳንቱን ጉዞ በተለየ ተስፋ አይመለከቱትም።
"...እንደኛ አዲስ ነገር ይዞ ይመጣሉ ብለን አንጠብቅም። ምክንያቱም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሆነ ብዙ የተለየ ነገር ይዘው ይመጣሉ ብለን አናስብም..."
የፕሪቶሪያው ስምምነት ከሶስት ዓመታት በኋላ
የፕሪቶሪያው ስምምነት ሦስተኛ ዓመቱን ቢይዝም፣ ሰላሙም ጦርነትም የሌለበት "ግራ መጋባት" ሰፍኗል። የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ግንኙነት "የተቆራረጠ" መሆኑ በዘላቂ ሰላም ላይ ጥላ አጥልቶበታል። ፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደ ወደ መሃል ሀገር ማምራታቸው ይህንን የተበጣጠሰ ግንኙነት ለመቀጠል ይሁን ወይም ለሌላ ዙር ውጥረት "ጊዜ መግዣ" ፣በርግጥ ገና ግልጽ አይደለም።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት በተለያዩ ጊዜያት ባደረጓቸው ንግግሮች ግን “የትግራይ ሕገ-መንግሥታዊ ወሰኖችን የማክበር፣ የማስከበር » ጉዳዮችን ጨምሮ በክልሉ ለሌላ ዙር ጦርነት ማገርሸት ዋና ምክንያት መሆን የሚችሉ” ጉዳዮች መኖራቸውን ተናግረው ነበር።
በትግራይ ክልል ለተራዘመ ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ ጦርነቱ በቀጥታ ካስከተላቸው ችግሮች ባሻገር አሁንም ድረስ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር እየጋለ የሚቀዘቅዘው ግንኙነት ያልተገመቱ ሁኔታዎችን ማስከተሉን ነው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች የሚገልጹት። የክልሉ ፕሬዚደንት በቅርብ ጊዜ ንግግራቸው የነገሩንም ይህንኑ ነው። የፕሪቶሪያው ስምምነት ተሟልቶ ካለመተግበሩ ባሻገር ጫናዎች እንዳሉባቸውም አልሸሸጉም።
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ፕሪቶሪያ-ደቡብ አፍሪቃ ላይ ግጭትን የማቆም ስምምነት ከተፈራረሙ ባለፈዉ ጥቅምት 23 ቀን 2018 ዓ/ም ሶስተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። ሶስቱ ዓመታቱ ብዙዎች እንደሚሉት ሁለቱ ኃይላት በስምምነታቸው መሰረት ግዴታቸውን ያልተወጡበት ወይም ሊወጡ ያልፈለጉበት ሰላምም ግጭትም ያልነበረበት ሆኖ ነው ያለፈው። በሁለቱ ኃይላት መካከል የተፈጠረው ያለመተማመን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጫና ማምራቱ ደግሞ ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ ሳያደርገው እንዳልቀረ ነው ሲነገር የሰነበተው። ህወሓት የፌዴራል መንግስቱን "አዲስ ከበባ አድርጎብኛል" ሲል ይከሳል። ነዳጅና በጀት መስተጓጎሉ እንደ ማነቆ ያየዋል። በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ በጀቱ ለልማት ሳይሆን ለታጣቂዎች ስልጠና እየዋለ ነው የሚል የጽኑ ወቀሳ ክስ መሰንዘራቸውም የሚታወስ ነው።
የግንኙነቱ መቆራረጥ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ
በሁለቱ ኃይላት የሚቀርበው የቃላት ጦርነትና እሰጥ አገባ እንዱሁም ተፈጠረ የተባለው የኢኮኖሚ እገዳ፣ በጦርነት የደቀቀውን የትግራይ ህዝብ ዳግም ወደ ስጋት ማማ ውስጥ ማስገባቱን ነው ፖለቲከኞች የሚመለከቱት ። የሳልሳይ ወያነ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃነ አጽብሃ፣ የባንኮች መዘጋትና የንግዱ ማህበረሰብ ንብረት በሃራጅ መሸጥ በትግራይ ኢኮኖሚ ላይ "መጨረሻው የማይታወቅ አደጋ" ደቅኗል ይላሉ።
"…የንግድ ማህበረሰቡ ከባንኮች የወሰደው ብድር ነበር… የነበረውን ዕዳ እና ወለድ እንዲከፍሉ እና አሁን ይህን ካላደረጉ ያላቸውን ንብረት አጠቃላይ ባንኮች እንዲወርሱ በሃራጅ እንዲሸጡ ካልሆነም ወደ ራሳቸው እንዲያዘዋውሩ የሚል ተጨማሪ የንግዱ ማህብረሰቡን የሚያስጨንቅ እና የትግራይን ሃብት ለመውረስ በሚመስል መልኩ እየተኬደበት ነው …"
ከህወሓት ለቀረቡት ቅሬታዎችና ለፕሬዚዳንቱ ጉዞ አንድምታከፌዴራል መንግስት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት እስካሁን አልተሳካም። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይም ሆኑ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሯ ለቀረበላቸው የማብራሪያ ጥያቄ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ምላሽ አልሰጡም።
የክልሉን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ዳንኤል ብርሃነ እንደሚሉት ከፕሪቶሪያው የተኩስ አቁም ስምምነት ወዲህ የነበሩ ግንኙነቶች የተቆራረጡ መሆናቸው አንጻራዊ ሰላሙን በማጽናት ረገድ አጥልቷል ባይ ናቸው።
"…ያለፈው ሶስት ዓመት ትልቁ የባከነበት ከተኩስ አቁሙ ስምምነቱ ጠንካራ መሰረት ወዳለው ዘላቂ ወደ ሆነ ነገር እንዳይሄድ ካረጉ አንዱ ቁልፍ ምክንያቶች የተበጣጠሰ ናቸው ግንኙነቶቹ ፤ በመሃል ላይ ደግሞ በየአቅጣጫው የሚወረወሩ መግለጫዎች እና የሚዲያ ንግግሮች ናቸው ብዙ ነገሩን ቅርጽ የሚያስዩዙት ። "…
የትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ተጠሪነት እና ያሳደረው ስጋት
የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና ህወሓትን በአስገዳጅ የመሣሪያ ድምጽ ዝም ያሰኘው ግጭት የማቆም የፕሪቶሪያ ስምምነት ተሟልቶ አለመተግበር ለዘለቀው ሰላም እና ግጭት አልባ ግንኙነት ሁለቱንም ቢያካስስም በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ግን ከፍቶ ይታያል። የህወሓት መከፋፈል ብሎም አመጽ እስከ ማስነሳት የደረሰው የክልሉ የጸጥታ ኃይል ሁኔታ ተጠቃሽ ነው። አቶ ዳንኤል እንደሚሉት የክልሉ የጸጥታ ሃይል መጠቀሚያ መሆኑ ጎልቶ ታይቷል።
"…የሰራዊቱ አመራሮች እንደ ግለሰብ የራሳቸው ፍላጎት አላቸው ፤ ድሮ ህወሓት ስለነበሩ እኔ አሁንም ህወሃት ነን የሚሉ አሉ። ህወሃት ያኔ የሁሉም ትግራዋይ የጋራ ግንባር ነው የነበረው። ከዚያ በኋላ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሲመዘገብ እንደ ፓርቲ አባላት ነበሩት ። በዚያ ጊዜ እንዚያ ሰዎች ወደ መደበኛ ሰራዊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነው የገቡት ። ዞሮ ዞሮ ያንን የመላቀል ነገር ስላለከሰራዊቱ አመሮች መካከል ማለቴ ነው፤ ከህወሓት ጋር መቆራኘት የሚፈልጉ አሉ። "
የሳልሳይ ወያነ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ብርሃነም ይህንኑ የሚያጠናክር ሃሳብ ነው የሰጡት ።
"…ጥር 15 2017 ራሳቸውን ከኮር በላይ ብለው የሚጠሩ የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራር ሰዎች ባስተላለፉት ዉሳኔ በግልጽ ውሳኔ ጉባኤ ላደረገው ሕወሓት ነው የምንደግፈው ብለው ከገለጹ በኋላ ያው ሰራዊቱ ተከፋፍሏል። …"
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ያሳደረው ጠበሳ እና አዲሱ የ«ጽምዶ» እንቅስቃሴ
ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት፣ ኢትዮጵያ በቅርብ ታሪኳ ካየቻቸው እጅግ አውዳሚ ክስተቶች አንዱ ነበር። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት የቀጠፈው፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ያፈናቀለውና መሰረተ ልማቶችን አመድ ያደረገው ይህ ግጭት፤ በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ በሰላም ስምምነት የተቋጨ ቢመስልም ገና ነው።
ውስጥ ውስጡን ሲናፈስ ቆይቶ የአደባባይ ሚስጢር ወደ መሆን የተሸጋገረው የህወሓት ኤርትራ ጥምረት በአካባቢው አጠራር «ጽምዶ» የመፍጠር አዝማሚያ ትኩሳቱን እንደጋለ የሚያቆይ ወናፍ አስመስሎታል። የጥምረቱን ስልታዊ አስፈላጊነት በግላጭ የሚያስረዱ የቀድሞ ቱባ ባለስልጣናት ጭምር በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴ አውታሮች ሲደመጡ ቆይተዋል።
አቶ ብርሃ አጽብሃ ግን ይህንን ጥምረት የትግራይን ህዝብ ለሌላ መከራ የጋበዘ ሲሉ ነው የሚገልጹት ።
"…በመሰረቱ ከቃሉ ጀምሮ የትግራይ ህዝብ አይደለም ። በመሰረታዊነት ደግሞ ለትግራይ ህዝብ ሌላ መከራ ሌላ ዕዳ ይዞ ይመጣል የሚል ግምገማ ነው ያለን….``
የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዳንኤል ብርሃነም ይህንኑ ሃሳብ ባጠናከሩበት አስተያየታቸው የህወሓት ባለስልጣናት ራሳቸው በጉዳዩ ምን ያህል ዕምነት አላቸው ሲሉ ያጠይቃሉ ።
ዋዜማ ላይ እንዳይኾን ...
"… እዚያ ቦታ ይሰሩ የነበሩ ካድሬዎች ወደ ስራቸው አልተመለሱም እና የህወሓት ካድሬዎች ያላመኑትን የድንበር ግንኙነት ሌላ የትግራይ ህዝብ ሊያምነው አይችልም።…."
በፌዴራል መንግስቱ ላይ ለሚያቀርበው ክስም ኾነ በፓርቲው ላይ ለሚነሳ ስሞታ የህወሓት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ልክ እንደ ፌዴራል ባለስልጣናት ሁሉ አልተሳካልንም።
ነገር ግን የጄነራል ታደሰ ወረደ የአዲስ አበባ ጉዞ የሚያሳየው አንድ ትልቅ እውነት እንዳለ ነው፦ በትግራይና በፌዴራል መንግስቱመካከል ያለው ግንኙነት "ተቋማዊ መሰረት" ያልያዘ መሆኑን ነው። የበጀት፣ የጸጥታና የወሰን ጉዳዮች በሕግና በስምምነቱ መነጽር ከመፈታት ይልቅ፣ በፖለቲካዊ ፍላጎት የሚመሩ መሆናቸው፣ ሰላሙን ጽኑ እንዳይሆን ማድረጉን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ይናገራሉ።
የትግራይ ፖለቲካ ዛሬም በሦስት ኃይሎች መካከለኛ ስበት ውስጥ ይገኛል፦ በውስጣዊ መከፋፈልና በምርጫ ስጋት፣ በአዲስ አበባ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጫና፣ እንዲሁም በአስመራ የደህንነት ስጋት። በተንታኞች አስተያየት የጄነራል ታደሰ ወረደ ጉዞ ምናልባት ለጥቂት ቀናት የሚቆይ "የፖለቲካ ማስታገሻ" ሊሆን ይችላል፤ ዘላቂው ፈውስ ግን የሚገኘው ህወሓት ከራሱ ጋር፣ ትግራይ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን የታሪክና የዲፕሎማሲ ቁስል በግልጽ ጠረጴዛ ላይ ሲታክም ብቻ ነው።
ያ ካልሆነ ግን፣ አሁን የሚታየው "ሰላም" ዳግም ወደማያባራ ግጭት የሚወስድ " ዋዜማ" ላይ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው።
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ






















