ተደራራቢ ችግሮች የበረቱበት የትግራይ ኢኮኖሚ በድጎማ በጀት እና በጥሬ ገንዘብ እጥረት ፈተና ተጋርጦበታል
Description
ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ትላንት በመቐለ ሲከበር የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዝደንት ሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ ሌላ “ጦርነት ተነስቶ ሕዝብ ለዳግም ሰቆቃ እና እልቂት እንዳይዳረግ” የአስተዳደራቸው ጥረት የበረታ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ “የትግራይ ሕገ-መንግሥታዊ ወሰኖችን የማክበር፣ የማስከበር እንዲሁም በሞት እና በሥቃይ ውስጥ ስድስተኛ ዓመታት እያስቆጠሩ ያሉት ተፈናቃዮች ወገኖች ወደቀያቸው የመመለስ ጉዳይ” “ለሌላ ዙር ጦርነት ማገርሸት ዋና ምክንያት መሆን የሚችሉ” መሆናቸውን ገልጸዋል።
ጊዜያዊውን አስተዳደር የመምራት ኃላፊነት ከአቶ ጌታቸው ረዳ ከተረከቡ ስምንት ወራት ገደማ ያስቆጠሩት የጦር መኮንን “ቁልፍ የሰላም እና የጦርነት ጥያቄ” ያሏቸው ሁለቱ ጉዳዮች “በሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መንገድ ዕልባት ማግኘት የሚችል እና የሚገባው” መሆናቸውን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈረመው ግጭት የማቆም ሥምምነት “እንዳይፈርስ” ጊዜያዊው አስተዳደር የሚጠብቀው እንደሆነ ተናግረዋል። ይሁንና ባለፈው ሰኞ በአክሱም ከተማ ባደረጉት ንግግር “ሥምምነቱ በምሉዕነት ሳይተገበር፣ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም አደጋ ላይ እየወደቀ ከፍ እና ዝቅ የሚል ውጥረት እየተመለከትን እየኖርን ነው” ብለው ነበር።
“ይህን ሁኔታ የሚያባብሱ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች እና ክልከላዎች ደግሞ እንደጫና መፍጠሪያ መሣሪያ መጠቀም የተለመደ ሆኗል” ሲሉ ተደምጠዋል። “የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ድጎማ በጀት መላክ ከቆመ ሁለት ወር አልፎታል ያሉት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት እርምጃውን “ከነውርም የከፋ” በማለት ገልጸውታል።
“ባንኮቻችንም ካሽ አልባ ሆነው በትግራይ ኢኮኖሚ ሊጫወቱት የሚገባ አዎንታዊ ሚና ቀርቶ ሕዝብ የቆጠበው የራሱን ገንዘብ እንኳን እንዲጠቀም እያደረጉ አይደሉም” ሲሉ ተናግረዋል።
ዶይቼ ቬለ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ባነሱት የበጀት ድጎማ ጉዳይ ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ የጠቀሱት ከፌድራል መንግሥት ለትግራይ የተመደበው የበጀት ድጎማ ሳይላክ መቅረት እና በባንኮች የተፈጠረው የጥሬ ገንዘብ እጥረት “የከፋ ተጽዕኖ” ሊያሳድሩ እንደሚችሉ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሙኡዝ ሐዱሽ ይሰጋሉ።
ሕዝቡ የሚጋፈጠውን ችግር ከማባባስ በተጨማሪ የክልሉ “ኢኮኖሚ እንዲያገግም የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚያደናቅፉ እና ተጋላጭነቶችን እንደሚያባብሱ” ዶክተር ሙኡዝ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ጸጋዘአብ ገብረማርያም “ሠራተኞች ከፍተኛ ድሕነት ውስጥ የመግባት ዕድላቸው ይጨምራል” በማለት ዳፋው የበረታ እንደሚሆን ተናግረዋል።
“ትግራይ ገና ከጦርነቱ ያልወጣ ክልል ነው። በጦርነት በጣም የተጎዳ ስለሆነ በከፍተኛ መጠን የፍላጎት ችግር ያጋጥማል” የሚሉት ጸጋዘአብ በገበያው ላይ ጭምር ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ያስረዳሉ። የመንግሥት ሠራተኞች “ወደ ኪስ የሚገባ ነገር አላገኙም ማለት በቀጥታ ከገበያ ገዝተው መጠቀም የሚችሉት ነገር በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል” ሲሉ አስረድተዋል።
ከባንኮች ካዝና ይልቅ “የተወሰኑ ሰዎች ገንዘብ” እንዲይዙ ዕድል የሚፈጥረው ችግር ክልሉን ሲፈታተኑ የቆዩት የኑሮ ውድነት እና ሥራ አጥነት እንዲባባሱ የሚያደርግ ነው። ገንዘብ የሚፈልጉ የትግራይ ነዋሪዎች የሚከፍሉት ወለድ ከፍተኛ ቢሆን እንኳ “መደበኛ ወዳልሆኑ አበዳሪዎች” ፊታቸውን እንዲያዞሩ ይገደዳሉ። መዋዕለ-ንዋይ እና የንግድ እንቅስቃሴ ይዳማሉ።
ኢኮኖሚው እንዲያገግም “ትንሽ የተጀማመሩ የሚመስሉ ሒደቶች ወይም እንቅስቃሴዎች ወደ ኋላ የሚመልስ እና አጠቃላይ የክልሉን የማምረት አቅም የሚያዳክም” እንደሆነ ጸጋዘአብ አስረድተዋል።
ከ2013 እስከ 2015 የተካሔደው ጦርነት ባስከተለው ጉዳት ምክንያት “ምንም ዐይነት ተቋማዊ ሥርዓት አለ ለማለት ይከብዳል” የሚሉት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ለክልሉ መንግሥት ከፌድራል የሚላከው የበጀት ድጎማ ጉዳይ ባለው የሰው ኃይል በተወሰነ ለማስቀጠል የሚደረገውን ሙከራ እንደሚጎዳ ገልጸዋል።
“የመንግሥት ግብር የመሰብሰብ፣ የመንግሥት ወጪ የማውጣት ወይም ደግሞ ኢኮኖሚው ላይ ኢንቨስት የማድረግ” አቅም “አሁንም ቢሆን ያልተቀረፉ ችግሮች እንደሆኑ እና መንግሥትም በሁለት እግሩ መቆም ያልቻለበት አጋጣሚ እንደሆነ መረዳት ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።
የድጎማ በጀት ሳይላክ መቅረት “ትግራይን ለማግለል ሆን ተብሎ የተደረገ ሙከራ ተደርጎ ሊተረጎም” እንደሚችል ለዶይቼ ቬለ የገለጹት ዶክተር ሙኡዝ በበኩላቸው “የመገንጠል ስሜትን” የማባባስ አቅም እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የትግራይ ክልል ለፌድራል መንግሥት “ገቢ በሚያደርገው አስተዋጽዖ እና በሚያገኘው ጥቅማ ጥቅሞች መካከል አለ ተብሎ የሚታመን አለመመጣጠን ከፍ ያለ የራስ ገዝነት (autonomy) ወይም የነጻነት ጥሪዎች ጭምር ሊያስከትል እንደሚችል” ዶክተር ምኡዝ ለዶይቼ ቬለ በጽሁፍ በሰጡት ምላሽ አብራርተዋል። የኢኮኖሚ መምህሩ ከኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት ጋር “ግልጽ የሆነ ውይይት እና ድርድር ወሳኝ ናቸው” የሚል ዕምነት አላቸው።
አርታዒ አዜብ ታደሰ






















