ያንዣበበው የጦርነት ስጋት እንዲገታ ...
Description
ያንዣበበው የጦርነት ስጋት መፍትሔ ይኖረው ይኾን?
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ፕሪቶሪያ-ደቡብ አፍሪቃ ላይ ግጭትን የማቆም ስምምነት ከተፈራረሙ ባለፈዉ ጥቅምት 23 ሶስኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። ሶስቱ ዓመታቱ ብዙዎች እንደሚሉት ሁለቱ ኃይላት በስምምነታቸው መሰረት ግዴታቸውን ያልተወጡበት ወይም ሊወጡ ያልፈለጉበት ሰላምም ግጭት ያልነበረበት ሆኖ ነው ያለፈው።
በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት የበላው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በዘመናዊው ዓለም አስከፊ ከሚባሉ ጦርነቶች እንደ አንዱ ተመዝግቦ ቢያልፍምላይመለስ ያከተመግን አልመሰለም ። ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 26፣2018 የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የህወሓት ታጣቂዎች ድንበር አልፈው በርካታ ቀበሌዎችን ወረሩብኝ፤ ብሎ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መረጃውን ለመቀባበል አፍታም አልወሰደባቸውም። የክልሉ መንግስት በመግለጫውየህወሓት ታጣቂዎች «በሰላማዊ ሰዎች ላይ «የተለመደ የሽብር ተግባሩን በግልፅ ጀምሯል» ብሏል።
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ባወጣዉ የአፀፋ መግለጫ በሁለቱ መግለጫዎች ደረሱ የተባሉትን ጥቃቶች ውድቅ አድርጓል። የጊዚያዊ አስተዳደሩ መግለጫ «ትግራይን ለማወክና እርስበርስ ለማዳማት ሆን ተብሎ በአፋር ክልል፣ ታጣቂዎች እንዲደራጁናእንዲታጠቁ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ በመደገፍና ተልዕኮ በመስጠት በትግራይ ላይ ተደጋጋሚ የጠብ አጫሪነት ተግባር ሲፈፅም ቆይቷል።አሁንም እያካሔደ ነዉ።» ይላል።
በአካባቢው አዲስ ጦርነት ይቀሰቀስ ይሆን የሚል በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ባጠላበት በአሁኑ ወቅት ህወሓት ታጣቂዎቹን ከአፋር ክልል ማስወጣቱን የሚገልጽ ዜና ቢነገርም የድሮን ጥቃት መፈጸሙ ከወደ ትግራይ ተሰምቷል። ሕወሓት በመግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይ ክልል በሚገኝ አንድ አካባቢ በሰዉ አዉልባ አዉሮፕላን (ድሮን) ደብድቧል፤ ብላል። ድብደባዉ የፕሪቶሪያዉን ግጭት የማቆም ሥምምነትን የጣሰ ነዉ በማለትም የፌደራሉን መንግስት ወንጅሏል።
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ከተደራጁ ታጣቂዎች ጋር የሚያደርጉት ዉጊያከመርገብ ይልቅ ተባብሶ በቀጠለበት በትግራይ እና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው ውጥረት ሊደገም ወደማይገባው አስከፊ ጦርነት ያመራ ይኾን ወይስ ሃይ ባይ አግኝቶ ከአጥፊ መንገዱ የመመለስ ዕድል አለው?
ተወያዮች
አቶ አበበ አካሉ ከአዲስ አበባ
አቶ ዳንኤል ብርሃነ ከትግራይ ክልል
አቶ ኑኡማን ሙሳ ከጀርመን ኮሎኝ
አቶ ባይሳ ዋቅወያ ከሲዊዲን
አወያይ ጋዜጠኛ ታምራት ዲንሳ























