DiscoverDW | Amharic - Newsጋዜጠኛ ቦጋለ መኩርያ፤ የመጀመርያዉ የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ - ሲታወስ
ጋዜጠኛ ቦጋለ መኩርያ፤ የመጀመርያዉ የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ - ሲታወስ

ጋዜጠኛ ቦጋለ መኩርያ፤ የመጀመርያዉ የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ - ሲታወስ

Update: 2025-12-10
Share

Description

ጋዜጠኛ ቦጋለ መኩርያ፤ የመጀመርያዉ የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ ሲታወስ



«የዓለም ባንክ በዓለም ባንክ እየተባባሰ ስለሚሄደዉን ድህነት በማስመልከት ለዛሬ ያጠናከርነዉን ሃተታ እዚህ ላይ እናበቃለን፤ እስከሚቀጥለዉ የኢኮኖሚዉ ዓለም ዝግጅታችን በድህና ቆዩን»



ይህ ድምጽ በዶቼ ቬለ DW ከተደመጠ 20 ዓመታት ሆነዉ። በዶቼ ቬለ በአማርኛዉ ቋንቋ ክፍል አገልግሏል። ጋዜጠኛ ቦጋለ መኩርያ። ማክሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም በጀርመን ኮለኝ ከተማ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ጋዜጠና ቦጋለ መኩርያ ከአገሩ ከኢትዮጵያ፤ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ምዕራብ ጀርመንዋ ኮለኝ የመጣዉ በጎርጎረሳዉያኑ 1962 ነዉ። በኢኮኖሚ ትክህርት በኮለኝ ከሚሀኘዉ ዩንቨርስቲ የተመረቀዉ ደግሞ በጎርጎረሳዉያኑ 1970 ዓ.ም ነዉ። የዝያን ጊዜ ወጣት ቦጋለ መኩርያ በኮለኝ ከተማ በሚገኘዉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የኤኮኖሚ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳለ፤ የዛሬ 60 ዓመት የዶቹ ቬለ ድምፅ ራድዮ ዶቼ ቬለ DW ፤ ለ 15 ደቂቃ ዜና ዝግጅቶችን ለማሰራጨት ሲንደረደር፤ ዝግጅቶችን ከመቅረፅ፤ በተጨማሪ ሰራተኞችን አፈላልገዉ ፤ የጣብያዉን ስርችት ለማስጀመር ሥራ ላይ የነበሩት፤ የያኔዉ ጋዜጠኛ የአሁኑ ዲፕሎማት አምባሳደር ተፈራ ሻዉል፤ በትምህርት ጎበዙን እና ወጣቱን በቦጋለ መኩርያን፤ በኮሎኙ ዩንቨርስቲ ትምህርቱን ሲከታተል አግኝተዉ፤ ከትምህርቱ ትይዩ የጋዜጠኝነት ስልጠናን ሰጥተዉ፤ አብሮዋቸዉ የዶቼ ቬለ ሬድዮ ስርጭት ጅማሮን ተቀላቀለ።



«ለስራ እና ስልጠና በቬስት ዶቼ ሩንድ ፉንክ ጣብያ ስልጠናዬን ጨርሼ ፤ የአማርኛ ፕሮግራም እንዳቋቁም በተፈለገበት ጊዜ፤ እዛዉ በቬስት ዶቼ ሩንድ ፉንክ ዉስጥ እኔ ሰልጥኜ ስለነበር አቋቋምኩላቸዉ። እና ያን ሳቋቁም ቦጋለ የምጣኔ ኃብት /ኢኮኖሚክስ/ ተማሪ ነበር በኮለኙ ዩንቨርስቲ፤ ከሱ ጋር አብሮ ዶ/ር ጎይቶም ፤ በቀለ ደምሴ የሚባል ነበር / እነሱን አሰባስበን የአማርኛ ፕሮግራምን ማዘጋጀት ጀመርን። የአማርኛ ፕሮግራሙን የጀመርነዉ በጎርጎረሳዉያኑ ጥር 15 ቀን 1965 ነዉ።»



ጥሩ ግለሰብ፤ ጥሩ ኢትዮጵያዊ



«ቦጋለ በተፈጥሮዉ ትሁት ተጫዋች እና ጠለቅ ያለ ባህሪ ያለዉ ፣ እዉቀት ያለዉ የሚያነብ ወጣት ነበር፤ እኔ እስከማዉቀዉ። ለብዙ ዓመታት በዶቼ ቬለ አገልግሏል። በአገለገለበት ጊዜ የሱን አቀራረብ የሱን አስተያየት ይወዱለታል። ቦጋለን እንደዚህ ነዉ የማዉቀዉ። በግል ህይወት ደግሞ፤ እንደ አንድ ቤተሰብ ነበርን። በጣም ተጫዋች፤ ጥሩ ጥሩ ግለሰብ እና ጥሩ ኢትዮጵያዊ ነበር። በፀባዩ በባህሪዉ በአሰራሩ ደግሞ፤ ኢትዮጵያዉያን ምን አይነት ሰዎች ናቸዉ የሚለዉ ፤ በጀርመኖች ዘንድ አድናቆትን እንዲያተርፍ አድርጎታል። ለቦጋለ ቤተሰቦች ለጓደኞቹ፤ አብረዉት ለኖሩት ለሚያዉቁት ሁሉ፤ ሁላችንም እኔም ጭምር ከፍተና ጥልቅ ሐዘን ስለተሰማን ሁላችንንም እግዚአብሔር ያጽናን። እሱንም መልካም እረፍት በአፀደገነት ያሳርፍልን ፀሎት ነዉ የማደርገዉ አመሰግናለሁ።»



የጀርመን ሬድዮ ዶቼ ቬለ ስርጭት ከጀመረ በኋላ ትንሽ ቆየት ብሎ ነበር ጣብያዉን የተቀላቀልኩት ያለን፤ ከዶቼ ቬለ አንጋፋ ጋዜጠኞች መካከል ታዋቂዉ እና አንጋፋዉ ጋዜጠኛ ንጉዜ መንገሻ አንዱ ነዉ። ንጉሴ መንገሻ በአሜሪካ ድምፅ ቪኦኤ ሬድዮ ክፍል ኃላፊ፤ ቆየት ብሎ የቪኦኤ የ 17 ቋንቋዎች የአፍሪቃ ዲቪዥን ክፍል ዳይሬክተር ሆኖ አገልግሏል። ከዚህ ሁሉ በፊት ግን እንደ አምባሳደር ተፈራ ሁሉ ከብስራተ ወንጌል ራድዮ የነጻ ትምህርት እድል አግኝቶ በኮሎኙ ቬስት ዶቸ ሩንድፉንክ ጣቢያ ጋዜጠኝነት ተምሮ ሲጨርስ ነበር ዶቼቬለ መስራት የጀመረው። በዶቼ ቬለ ስራ እንደጀመረ ነበር ጋዜጠኛ ንጉሴ ቦጋለ መኩርያን የተዋወቀዉ።



የሥነ ጽሑፍ ችሎታዉም እጅግ አስገራሚ ከምገምተዉ በላይ ነበር



« ከቦጋለ ጋር በዶቼ ቬለ ለብዙ ዓመታት ሰርተናል። በመጀመርያ በኮለኝ ከተማ በሚገኘዉ ዩንቨርስቲ ኢኮኖሚክስ ተማሪ ነበረ። እየተማረ እንደ ፊሪላንስ በትርፍ ጊዜዉ ነበር ዶቼ ቬለ ዉስጥ የሚያገለግለዉ። የኢኮኖሚ ምሁር ነዉ ግን በጣም ጎበዝ ነበር። መጠነኛ ቁመት ነዉ ያለዉ ነገር ግን ድምፁ ከዚህ ተክለ አካል የሚወጣ አይመስልም። በጣም ጥሩ የሬድዮ ድምጽ ነበረዉ። የሥነ ጽሑፍ ችሎታዉም እጅግ አስገራሚ ከምገምተዉ በላይ ነበር። በጣም ጥሩ ፀሐፊ ነበር። ቦጋለ በዶቼ ቬለ ዉስጥ በጣም ታዋቂ ነበር። በተለይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1966 የየካቲት አብዮት ሲቀጣጠል እና የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሰት አጼ ኃይለሥላሴ፤ ከስልጣን እንደወረዱ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከዉጭ የብዙኃን ማሰራጫዎች ዶቼ ቬለ የመጀመርያዉን ደረጃ የያዘ ነበር። እና በዚያ ዉስጥ ቦጋለ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገ ሰዉ ነዉ። የጋዜጠኝነት ክህሎት በደንብ ያሳየሰዉ ነዉ። በዝያ ነዉ በደንብ አድርጌ የማዉቀዉ።»



ጋዜጠና ንጉሴ መንገሳ የሱን እና የጋዜጠና ቦጋለ መኩርያን የዝያን ጊዜ ባልደረቦች እንዲህ ያስታዉሳል።



ፍትህ የሚያዉቅ የሚሰብከዉን የኖረ ነበር



«የሚገርም ነገር ነዉ ቦጋለ፤ እኔ ብቻ ቀረሁ መሰለኝ። አማኑኤል በረከት ነበር በዶቼ ቬለ የሚሰራ ሄዷል። ጌታቸዉ ደስታ ሄዷል። ድራጎን ኃይለመለኮት ሄዷል።እነዚህ ሁሉ አልፈዋል። ተክሌ የኋላበቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፤ እነዚህ ሁሉ አልፈዋል። የሚገርም ነዉ እኔን ብቻ ነዉ መሰለኝ እግዜር የረሳኝ። እኔ ብቻ ነኝ መሰለኝ በህይወት ያለሁ ይመስለኛል። ትንሽ ያስፈራል። የሚገርመዉ ቦጋለ ከኢኮኖሚ ባለሞያነቱ እና ከጋዜጠኝነት ክህሎቱ ባሻገር ፤ ፀባዩ በጣም ጥሩ የነበረ ሰዉ ነዉ። ፍትህን በደንብ አድርጎ የሚያዉቅ ነበር። እኔ እንደሚመስለኝ ባሌ ነዉ ተወልዶ ያደገዉ ግን ደግሞ፤ በብሔር ደረጃ ከማንም ጋር ጠብ የለዉም። ከኤርትራዉ ከትግሬዉ ከአማራዉ ከሁሉም ጋር ሰም እና ወርቅ ነበር። ፀባዩም እሱ ፍትህ ያዉቃል ጥሩ ሰዉ ነዉ የሚባል እና የሚሰብከዉንም የኖረ ሰዉ ነበር። በዚህ ፀባዩ ቦጋለን በጣም የማከብረዉ ሰዉ ነበር። የሱ ማለፍ በጣም በጣም አድርጎ ነዉ የሚያሳዝነኝ። ለባለቤቱ ለሁለቱ ልጆቹ ለዘመድ ለጓደኞቹ ጽናቱን ይስጣቸዉእሱንም የሰላም እረፍት ያድርግለት።»



ሌላዋ የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ ኂሩት መለሰ ጥቂት ጊዜም ቢሆን ከጋዜጠኛ ቦጋለ መኩርያ ጋር አብራ ሰርታለች። ቦጋለ ከታታሪ ሰራተኝነቱ በተጨማሪ ሂሩት ዶቼ ቬለ ተቀጥራ ወደ ጀርመን ስትመጣ፣ ቦጋለ አገር ያላመዳት ቋንቋ ያስተጉምላት የነበረ ነዉ።



ሰዉን ለመርዳት ወደኃላ የማይል፤ ለአዳዲስ ሰራተኞች ጀርመንን የሚያስተዋዉቅ ነበር



«ቦጋለን የማዉቀዉ ለሥራ ወደ ጀርመን ዶቼ ቬለ ከመጣሁበት ጊዜ አንስቶ ነዉ። በዝያን ወቅት በዶቼ ቬለ ከነበሩ አንጋፋ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነዉ። ቦጋለ ለረጅም ዓመታት የኤኮኖሚ ፕሮግራም ሲያዘጋጅ እና ሲያቀርብ የነበረ ጋዜጠኛ ነዉ። ታታሪ ሰራተና እንደነበረ አዉቃለሁ። ለመጀመርያ ጊዜ የመጣሁበትን ጀርመንን ካላመዱኝ የስራ ባልደረቦች አንዱ ነዉ ቦጋለ። እሱ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቹም ጭምር፤ ትሁት ሰዉን ለመርዳት ወደኋላ የማይሉ ነበሩ። ሶቼ ቬለ ከመጣሁ በኃላ ስራ በጀመርኩበት በመጀመርያዉ ቀን ፤ በጀርመንኛ የተጻፈ የሥራ ኮንትራት እንድፈርም ስጠየቅ፤ ያኔ ጀርመንና ስለማላዉቅ በእንጊሊዘኛ የተጻፈ ካላችሁ ብዬ ስጠይቅ፤ እንደሌለ ተነግሮኝ፤ የስራ ባልደረችሽ ያስረዱሽ ተብዬ፤ ትርጉሙን ያስረዳኝ ቦጋለ ስለነበረ ምንጊዜም አልረሳዉም። ቦጋለ በባህሪዉ ሥራ ከጀመረ፤ ብዙም ድምፁ የሚሰማ አይደለም። ይልቁንም ትኩረቱን ሥራ ላይ የሚያደርግ ጋዜጠኛ ነበረ። ግን በትርፍ ጊዜዉ ጨዋታዉ የሚጠገብ አይደለም። ቦጋለ በብዙ ነገር ይታወሳል። እንግዲህ በጀርመን ህግ መሰረት እዚህ የሚሰራ ሰዉ መብቶችም ግዴታዎችም አሉት። እና ቦጋለ ለአዳዲስ ሰራተኞች ግር የሚሉ ነገሮችን በዝርዝር ለማስረዳት፤ ለመምከርም ወደኋላ የማይል ሰዉ ነበረ። ከሁሉም በላይ ቦጋለ ለዶቼ ቬለ ለሰጠዉ የ 40 ዓመታት አገልግሎት፤ ሁሌም የሚታወስ ነዉ። ለባለቤቱ ለልጆቹ እንዲሁም ለመላ ቤተሰቡ፤ መጽናናትን እመናለሁ። እግዚአብሔር ነፍሱን በገነት ያኑር።»



ብዙ የጋራ ዉይይቶች ነበሩን



በጋዜጠኛ ቦጋለ ምኞት መሰረት ሥርዓተ ቀብሩን ኢትዮጵያ ለማስፈፀም፤ ሐዘናቸዉን ይዘዉ ሕጋዊ የጉዞ ዝግጅትን ለማስጨረስ፤ ሥራ ላይ ሳሉ ያገኘናቸዉ የቦጋለ ባለቤት ወ/ሮ እመቤት ቦጋለ ናቸዉ።



«ባለቤቴ ቦጋለ በጣም ጥሩ ሰዉ ጥሩ አባት ጥሩ ባል ነበር። በጎርጎረሳዉያኑ 1994 ዓም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነዉ የተተዋወቅነዉ። በ 1995 ዓ.ም ወደ ጀርመን ይዞን መጣ። 30 ዓመት አብረን ኖረናል። በቃላት ሊገለጽ የማይችል በጣም ጥሩ ሰዉ እና ጥሩ አባት ነበር። ዘመድ የሚወድ ህይወቱን ሁሉ ለሰዉ ነዉ የኖረዉ። ለቤተሰቡ የሌ የኖረ ሰዉ ነዉ። ሁለታችንም ከአንድ አካባቢ ስለሆነ የመጣነዉ ፤ ብዙ የጋራ ነገሮች ነበሩን፤ በመካከላችን የእድሜ ልዩነት ቢኖርም። የመጣነዉ ከባሌ ነዉ ቦጋለ ከባሌጎባ ሮቤ አካባቢ ከምትገኝ ኢሱ ከሚባል ቦታ ነዉ። እኔ ደግሞ የረሮ ከሚባል አካባቢ ነዉ የመጣሁት። ሁለታችንም የምናቃቸዉ ሰዎች ስላሉ ብዙ የጋራ ዉይይት ነበረን።»



ከሁሉ በላይ ለቤተሰቡ ቅድሚያ ይሰጥ ነበር



የ20 ዓመቱ ጋዜጠኛ ቦጋለ የመጀመሪያ ልጅ ይኩኖ-ብርሃን ዘ-ሚካኤል ቦጋለ አባቱ ከምንም በላይ ለቤተሰቡ ቅድሚያ ይሰጥ እንደነበር እንዲህ ያስታዉሳል።



«አባቴ ለሌ ሰው ነበር ይኖር የነበረው ። ለልጆቹ፣ ለዘመድ፣ ለባለቤቱ፣ ለራሱ ምንም ነገር አላደረገም ። ለቤተሰብ ብቻ ነው የኖረው ። »



በዶቼቬለ በተለይ በሳምንታዊዉ ከኢኮኖሚዉ ዓለም ዝግጅቱ ይታወቅ የነበረዉ ቦጋለ መኩርያ፤ በጣብያዉ 40 ዓመታት አገልግሏል። ጡረታ ከወጣም 20 ዓመታት ሆኖታል። የአንዲት የ 26 ዓመት ሲት ልጅ እና የአንድ የ 29 ዓመት ወንድ ልጅ አባት ነዉ። ማክሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ዶቼቬለ ለዜተሰቦቹ ለዘመድ ወዳጆቹ መጽናናትን ይመኛል። ነፍስ ይማር!



አዜብ ታደሰ



ታምራት ዲንሳ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ጋዜጠኛ ቦጋለ መኩርያ፤ የመጀመርያዉ የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ - ሲታወስ

ጋዜጠኛ ቦጋለ መኩርያ፤ የመጀመርያዉ የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ - ሲታወስ

Azeb Tadesse Hahn