የምሥራቅ እና የመካከለኛው አፍሪቃ እና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጫወታዎች
Description
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በቀጠለው የምስራቅ እና የመካከለኛው አፍሪቃ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ሻምፒዮና ዋሊያዎቹ የመጀመሪያ የምድብ ጫወታቸውን በድል ጀምረዋል። ኢትዮጵያዊቷ ልቅና አምባው የስፔይን ሶሪያ ከተማ የስምንት ሺ ሜትር የሀገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር አሸንፋለች። ብዙዎችን ቁጭ ብድግ እያደረገ የመጨረሻዎቹን ተሳታፊ ሃገራት መለየቱን የቀጠለው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ሰፊ ትኩረት ስቧል።
አትሌቲክስ
በስፔይኗ የሶሪእያ ከተማ ያስተናገደችው እና የወርቅ ደረጃ የተሰጠው እና ተዘዋዋሪው የሀገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር ትናንት እሁድ ተካሂዷል። ከጣልያናዊቷ ቫለንቲና ጌሜቶ እና ከኬኒያዊያኑ ሼሊያ ጃቤት እና ኖሺን ኪሙጌ ብርቱ ፉክክር የገጠማት ልቅና በመጨረሻም ነፋሻማውን የሶሪእያ የስምንት ሺ ሜትር የሀገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር በአሸናፊነት አጠናቃለች። የገባችበት ሰዓትም 27:25 , 30 ሆኖ ተመዝግቧል።
ኬንያዊያኑ ሼሊያ ጃቤት እና ኖሺን ኪሙጌ ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመሆን አጠናቅቀዋል። ልቅና በስፔይኗ ከተማ በተመሳሳይ ውድድሮች ስታሸንፍ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከውድድሩ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠችው ቃለ ምልልስም "ሶሪእያ የምወደው የሀገር አቋራጭ ውድድር ነው፤ በዚህም ሁለተኛ ድሌን እዚህ በማግኘቴ በጣም ተደስቻለሁ" ብላለች።
በወንዶች ምድብበተመሳሳይ ርቀት የተደረገውን ውድድር ኬንያዊው ማቲው ኪፕሳንግ አሸንፏል። ርቀቱን ለማጠናቀቅ 23:10 ሰከንድ የወሰደበት ኪፕሳንግ የሶሪእያ ሀገር አቋራጭ ውድድር ሲያሸንፍ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። በውድድሩ ሌላዉ ኬኒያዊ ኪፕሩቶ ሁለተኛ ሲወጣ ትውልደ ብሩንዲ ስፔናዊ ቲየሪ ንዲኩምዌናዮ ሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል።
ካለፈው ቅዳሜ ሕዳር 6 ቀን፣ 2018 ዓ/ም የጀመረው እና ለአንድ ሳምንት የሚቆየው የምስራቅ እና የመካከለኛው አፍሪቃ ሃገራት ሴካፋ ዋንጫ አዲስ አበባ ውስጥ ተጀምሯል። 10 የቀጣናውን ሃገራት እያሳተፈ በሚገኘው ውድድሩ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ብሔራዊ ቡድን በመክፈቻው የርዋንዳ አቻውን 2 ለ 0 በማሸነፍ አጀማመሩን አሳምሯል። ዋናውን ብሔራዊ ቡድን የመተካት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ቡድኑ ያለበትን ደረጃ ፣ የውድድር ዝግጅቱ እና የተሳታፊ ሃገራት የተወዳዳሪነት አቅም እንዴት ይታያል ስንል በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት መርኃ ግብር ዋና አዘጋጅ ምስጋናው ታደሰን በስልክ አነጋግረነዋል። (የቃለ ምልልሱ የድምጽ ማዕቀፍ በድምጽ ዘገባ ውስጥ ተካቷል።)
የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ
በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጫወታዎች ተደርገዋል። በማጣሪያ ጫወታው በተለይ በአፍሪቃ ጥሩ ሁለተኛ ሆኖ ለማለፍ ከአፍሪቃ በናይጄሪያ እና በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መካከል የደረገውን ጫወታ ጨምሮ በአውሮጳ በጣልያን እና ኖርዌይ እንዲሁም በሃንጋሪ እና አየርላንድ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የተደረጉትን ጫወታዎች ስሜት የገዛ ለየ ደጋፊዎቻቸው ነብስ ሰንቆ የያዘ ውድድር አለ ለማለት ይከብዳል።
ከአፍሪቃ ምድብ ሁለት እና ምድብ ሦስት 2ኛ ሆነው የመጀመሪያውን የምድብ ማጣሪያቸውን ያጠናቀቁት ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ናይጄሪያ ወደ ጥሎ ማለፍ ሃላፊ ሃገራትን ለመቀላቀል ትናንት እሁድ ምሽት ያደረጉት ጫወታ መደበኛው የጫወታ ጊዜ አንድ አቻ ነበር ያጠናቀቁት ። አሸናፊውን ለመለየት ወደ መለያ ምት ያመራው የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ትንቅንቅ አንዱን የግድ መለየት ነበረበት እና የማታ ማታ አቦሸማኔዎቹ ፧ ኮንጎዎች ንስሮቹን ከቀጣዩ አልም ዋንጫ አስቀርተው ወደ ቀጣዩ የጥሎ ማለፍ ውድድር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። በመለያ ምቱ ኮንጎ ናይጄሪያን 4 ለ 3 አጠቃላይ ውጤት አሸንፋ ወደ ዓለም ወደ የዓለም ዋንጫ መድረክ አንድ ርምጃ መጠጋቷን ስታረጋግጥ የንስሮቹ እና የቱርኩ ጋላተሰራይ የጎል አነፍናፊ ቪክቶር ኦስሜን በቀጣዩ የሰሜን አሜሪካው የዓለም ዋንጫ መድረክ ከማናያቸው ድንቅ አጥቂዎች መካከል አንዱ ሆኗል።
በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ከተስተናገዱ ድንቅየዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ቻወታዎች አንዱ የነበረው በጣልያን እና የኖርዌይ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል በሚላን ሳንሲሮ የተስተናገደው ግጥሚያ የብዙኃንኑን ቀልብ የገዛ ነበር ። በምሽቱ ጫወታ ግብ የማስቆጠሩን ቅድሚያ ሰማያዊዎቹ ማስቆጠር ቢችሉም ከዕረፍት መለስ የኖርዌያዊያኑ የጎል ቀበኞች የዘነባበቸውን የጎል ሙከራዎች መከላከል አልተቻላቸውም። በታሪኩ ካቴናው ተብሎ የሚታወቀው የጣልያን የተከላካይ ክፍል ታሪክ መሆኑን ባሳየበት ምሽት በሰሜን አውሮጳዊt። ሀገር 4 ለ 1 ለመሸነፍ ተገድዷል። ኖርዌይ ጣልያንን በደርሶ መልስ 7 ለ 1 በማሸነፍም በሁለቱ ሃገራት የግንኙነት መድረኮች አዲስ ታሪክ መጻፍም ችላለች። በአውሮጳ ምድብ 9 ውስጥ የተደለደለችው ኖርዌይ በማንችስተር ሲቲው ኤርሊንግ ሃላንድ ፊት አውራሪነት የምድብ ማጣሪያ ሁሉንም ጫወታዎች በማሸነፍ በ24 ነጥቦች ወደ ታላቁ የውድድር መድረክ በኩራት እና በክብር መቅረብ ችላለች።
በአንጻሩ በሩስያ እና የቃጣር የዓለም ዋንጫዎች መታደም የተሳናት ጣልያን ለሦስተኛ የውድድር ዘመን ከውድድር መድረኩ ላለመራቅ ያደረገችው ብርቱ ጥረት ፈተና ገጥሞታል። ከምድቡ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ጣልያን ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ሌላ የጥሎ ማለፍ ውድድር ይጠብቃታል።
በሌላ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ትናንት ምሽት በምድብ ስድስት ውስጥ የተደለደሉት ሃንጋሪ እና አየላንድ ሁለተኛ ሆኖ ለማጠናቀቅ ያደረጉት ብርቱ ፍልሚያ ለዋንጫ ከሚደረግ ትንቅንቅ የተለየ አልነበረም። ሃንጋሪ ያስተናገደችው የምሽቱ ጫወታ እስከ 96ኛው ደቂቃ ድረስ ሁለት አቻ የነበረ ሲሆን በዚህ ስሌት የሊቨርፑሉ የጎል አዳኝ ዶሚኒክ ሶቦስላይ የሚመራው የሃንጋሪ ብሔራዊ ቡድን 2ና ሆኖ በማጠናቀቅ ወደ ጥሎ ማለፍ የሚያመራውን ዉጤት እንደጨበጠ ነበር ። ነገር ግን የምሽቱ የጫወታው ኮከብ እና በአንድ ጫወታ ሃትሪክ መስራት የቻለው ትሮይ ፓሮት የሃንጋሪያውያንን ህልም ያጨለመች ለራሱ ሃትሪክ ያስገኘች እና ለሃገሩ ወደ ዓለም ዋንጫው መድረክ ያስጠጋችውን ጎል ሲያስቆጥር ስቴዲየሙ የተናጠ ነበር የመሰለው። የእግር ኳስ መወደድ አንዱ ማሳይ ሆኖም አልፏል።
የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሮች የበርካታ ሃገራትን የቀጥታ ተሳታፊነት አረጋግጧል። በዚህም ከአፍሪቃ አልጄሪያ ፣ ኬፕ ቨርዴ ፣ ግብጽ ፣ ጋና ፣ አይቮሪ ኮስት ፣ ሞሮኮ ፣ ሴኔጋል ፣ ደቡብ አፍሪቃ እና ቱኒዚያ በቀጥታ ኃላፊ ናቸው ። በአውሮጳ ምድብ ክሮሺያ ፣ እንግሊዝ ፣ ፈረንሳይ ፣ ኖርዌይ እና ፖርቹጋል ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ ከደቡብ አሜሪካ አርጀንቲና ፣ ብራዚል ፣ ኮሎምቢያ ፣ ኢኳዶር ፣ፓራጓይ ፣እና ዩራጋይ የቀጥታ ተሳታፊነት ትኬታቸውን በጊዜ ቆርጠዋል።
ከእስያ ምድብ አውስትራሊያ ፣ ኢራን ፣ ጃፓን ፣ ዮርዳኖስ ፤ ቃጣር ፣ ሳኡዲ አረቢያ ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ኡዝቤኪስታን በታላቁ የውድድር መድረኮች ተሳታፊነታቸውን ኣ,ረጋግጠ,ዋል። የውድድሩ የጥምር አዘጋጆች ካናዳ አሜሪካ እና ሜክሲኮን ጨምሮ የኦሺኒያ ተወካይዋ ኒውዚላንድ በ,ዚሁ የውድድር መድረክ የምንመለከታቸው ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው።
በቀሪ የማጣሪያ ውድድሮች በተለይ ከአውሮጳ ምድብ ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ትንቅንቅ የሚታይባቸው ውድድሮች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።
የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው መዘዝ
የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ሯጮች ከዚህ በኋላ የማራቶን ክብረወሰን የመስበር እድላቸውን እየቀነሰ ነው ሲል አንድ አዲስ የወጣ ጥናት አመልክቷል።
በአሜሪካ የሚገኘው እና ለትርፍ ያልተቋቋመ ክሊሜት ሴንትራል የተባለ የጥናት ተቋም ባወጣው ግኝቱ እንዳለው የአየር ሙቀት መጨመር “በአንዳንድ የሩጫ ውድድሮች ክብረ ወሰን መስበር ከማያስችል ደረጃ እያደረሰው ነው ” ብሏል።
በጎርጎርሳዉያኑ 2045 ከ221 የአለም ማራቶን ውድድሮች 86 በመቶው የሩጫ ውድድሮች ክብረ ወሰን የመስበር ዕድሉ ዝቅተኛ እንደሚሆን ተቋሙ ያወጣው ትንበያ ያመለክታል።
ተቋሙ በጥናቱ በዚህ ዓመት የተካሄደው የበርሊን ማራቶንን እንደምሳሌ ሲጠቅስ በርሊን ባልተለመለደ የአየር ሁኔታ በመስከረም ወር በ24 ዲግሪ ሴልሽየስ ውድድሩን ማስተናገዷን አስታውሷል። ከዓለም ታላላቅ የማራቶን የውድድር መድረኮች የሚጠቀሱት ለንደን እና ቶኪዮም ቢሆኑ ከበርሊን የተለዩ አልነበረም ያለው መግለቻው ከተሞቹ ባልተለመደ ሁኔታ ከ20 ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ ማስመዝገባቸውን በማሳየነት ጠቅሶ በአየርን ንብረት ለውጥ ላይ ሊወሰዱ የሚገባቸው ርምጃዎች አስገዳጅነትን አጽንዖት ሰጥቷል።
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ























