በኢትዮጵያ ምርጫ ሲቃረብ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ወደ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እያደላ ነው
Description
ባለፈው ሣምንት በአዲስ አበባ በተካሔዱ የውይይት መድረኮች መንግሥት ያከናወናቸው እና ያቀዳቸው ሥራዎች ውዳሴ ቀርቦላቸዋል። “የጉባ ብሥራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ክፍለ-ከተሞች በተካሔዱት ውይይቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝን የመሳሰሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።
የተመረጡ የከተማዋ ነዋሪዎች የተሳተፉባቸው የክፍለ-ከተማ ውይይቶች ሚኒስትሮችን ጨምሮ በሦስት ባለሥልጣናት የተመሩ ናቸው። የኮሪደር ልማት፣ የመኖሪያ ቤት እና የመሠረተ-ልማቶች አቅርቦትን የመሳሰሉ ጉዳዮች በተነሱባቸው መድረኮች እንደ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ ያሉ ባለሥልጣናት መንግሥት አሳካ ያሏቸውን ሥራዎች እና ያቀዳቸውን ውጥኖች አብራርተው ነበር።
“ሕዳሴ በተመረቀበት ወቅት ከጉባ ላይ ሆነው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገና በቀጣይ እነዚህን እነዚህን እንሠራለን ብለው የተናገሯቸው ውጥኖች አሉ” ሲሉ ዶክተር ጌዲዮን ተናግረዋል። በሶማሌ ክልል ጎዴ አካባቢ ሊገነቡ የታቀዱ የአፈር ማዳበሪያ እና የጋዝ ማምረቻዎች፣ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ እና አስር ዓመታት ሊፈጅ ይችላል የተባለው የኑክሌር ኃይል ማመንጫ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በተካሔዱት ውይይቶች ባለሥልጣናቱ የዘረዘሯቸው ዕቅዶች ናቸው።
ባለሥልጣናቱ በሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ላይ ካጠሉት ተግዳሮቶች ይልቅ ኢኮኖሚያዊ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከፍ ያለ ትኩረት እንዲሰጣቸው የሚሹ ይመስላል። የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ “ኢኮኖሚያችን ቀና እያለ፤ ጠንካራ እየሆነ፣ ለኮሮና የማይበገር፣ ለግጭት የማይበገር፣ ለተፈጥሮ የማይበገር ለተለያዩ ችግሮች የማይበገር፣ ከውጭ እና ከውስጥ ለሚቃጣ የጠላት ሽኩቻ የማይበገር ኢኮኖሚ እየተገነባ እየመጣ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
በአንደኛው መድረክ በአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው ተጋብዘው ንግግር ያደረጉት የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ በመጪው ግንቦት የሚካሔደውን ሰባተኛ አጠቃላይ ምርጫ ከቀደሙት “የተሻለ” ማድረግ ከውይይቶቹ ዓላማ አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል።
ውይይቶቹ “የምረጡኝ ዘመቻ” ተብለው በይፋ ባይጠሩም ገዥው ፓርቲ የሚያደርገውን ዝግጅት እያጠናከረ እንደሚገኝ የሚጠቁሙ ናቸው። በኔዘርላንድስ በሚገኘው ክሊንገንዴል ኢንስቲትዩት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ተመራማሪው አማኑኤል ደሳለኝ ከምርጫ ጋር የሚያያዘውን ትርክት ገዥው ፓርቲ ለራሱ “በሚመች መልኩ መቃኘት” ሳይፈልግ እንዳልቀረ ታዝበዋል።
“በግልጽ የምርጫ ዝግጅት ነው ተብሎ ባይታወጅም ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳውን ከማሳወቁ አንጻር ካሁኑ ገዥው ፓርቲ ዝግጅቱን የጀመረ ነው የሚመስለኝ” ሲሉ አቶ አማኑኤል ተናግረዋል።
ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች እና የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ምርጫ ለማካሔድ የሚያስችሉ አይደሉም የሚል አቋም የሚያራምዱ ጥቂት አይደሉም። በፌድራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የበረታው ፖለቲካዊ ውጥረት እስካሁን መፍትሔ ስላልተበጀለት በትግራይ ክልል እንዴት ምርጫ እንደሚካሔድ የሚታወቅ ነገር የለም።
የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝደንት ዐቢይ አሕመድ ግን “ሰላም የለም” በሚል አመክንዮ ምርጫ ሳይካሔድ ሊቀር እንደማይችል የጸና አቋም አላቸው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የጸጥታ ችግሮች ቢኖሩም አቶ አማኑኤል “ኢኮኖሚው ትልቅ ቦታ የሚኖረው ይመስለኛል፤ ሊኖረውም ይገባል” ሲሉ ይናገራሉ።
“ከኢኮኖሚው አንጻር ሊነሱ የሚችሉ ብዙ ትልልቅ ጥያቄዎች አሉ” የሚሉት አቶ አማኑኤል የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት እና የድሕነት መስፋፋትን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። የዓለም ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሰነድ በጎርጎሮሳዊው 2025 በኢትዮጵያ የድሕነት ምጣኔ ወደ 43% ከፍ እንደሚል አሳይቶ ነበር። አቶ አማኑኤል እንደሚሉት “እነዚህ ክርክር ሊደረግባቸው የሚገቡ፤ አማራጮች ሊቀርቡባቸው የሚገቡ ትልልቅ ጉዳዮች ናቸው።”
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ተግባራዊ የሚያደርገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በምርጫው ከፍተኛ ትኩረት ሊያገኙ ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ ነው። የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት እና የወጪ ንግድን ለማበረታታት ተግባራዊ የተደረገው ማሻሻያ ብር ዶላርን ከመሳሰሉ የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለውን የምንዛሪ ተመን በከፍተኛ መጠን አዳክሟል።
የብር መዳከም በፊናው ነዳጅን ጨምሮ ሀገሪቱ ከውጭ የምትሸምታቸው ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ መጠን እንዲንር አድርጎታል። የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ዛሬ ይፋ ባደረገው የነዳጅ ማሻሻያ የአንድ ሊትር ቤንዚን፣ ኬሮሲን እና ነጭ ናፍጣ የመሸጫ ዋጋ በሊትር 129 ብር ገብቷል። ይህ በሌሎች የኢኮኖሚው ዘርፎች ላይ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው።
በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት በገዥው ፓርቲ እና በተቃዋሚዎች መካከል ሊደረግ የሚችል ክርክር የኑሮ ውድነትን የተመለከቱ ርዕሰ-ጉዳዮች ውይይት እንዲደረግባቸው ዕድል ሊፈጥር ይችላል። “በተወሰነ ደረጃ ተቃዋሚዎች ሐሳባቸውን በግልጽ የሚያራምዱበት፤ ሚዲያ ላይ ወጥተው ሐሳቦቻቸውን ለመራጩ ሕዝብ የሚገልጹበት ዕድል የሚመቻች ከሆነ ኢኮኖሚው ውስጥ ያሉ ችግሮችን በማንሳት በገዥው መንግሥት ላይ የትርክት የበላይነት ለማግኘት” እንደሚረዳቸው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተመራማሪው አቶ አማኑኤል ያምናሉ።
ይህ የሚሆነው ግን የፖለቲካ ምኅዳሩ በአንጻራዊነት የመከፈት አዝማሚያ ካሳየ ብቻ ነው። አቶ አማኑኤል “ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕድል የማያገኙ ከሆነ የገዥው ፓርቲ ሐሳብ እና የገዥው ፓርቲ ትርክት ብቻ ነው ለሕብረተሰቡ የሚቀርበው” ሲሉ ተናግረዋል።
የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ በመንግሥት ተቋማት ገለልተኝነት ላይ እምነት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል። አስር የፖለቲካ ፓርቲዎች መከላከያ ሠራዊት፣ የፖሊስ፣ የደሕንነት ተቋማት እና የፍትኅ አካላትን “ገለልተኝነት የሚያረጋግጥ” አስገዳጅ “የጋራ ስምምነት” ሊኖር እንደሚገባ ባለፈው ወር ጥሪ አቅርበው ነበር።
የነጻ እና ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን መገፋት ከገዥው ፓርቲ ውጪ ያሉ ሐሳቦች በምርጫው ሒደት እንዳይሰሙ እንቅፋት ሊፈጥር የሚችል ሌላ ደንቃራ ነው። ምርጫው ገና ስድስት ገደማ ወራት የሚቀሩት ቢሆንም ፍትኃዊ፣ ነጻ እና ተዓማኒ እንዲሆን የሚያስችሉ እርምጃዎች መንግሥት ለመውሰዱ በርካቶች ጥርጣሬ አላቸው።
“የኢኮኖሚውም የሌሎቹም ጉዳዮች በግልጽነት ውይይት ሊደረግባቸው የሚችለው የምርጫው ሒደት አሳታፊ እና ተወዳዳሪ የሚሆን ከሆነ ነው” የሚሉት የክሊንገንዴል ኢንስቲትዩት ተመራማሪ “አሁን ፍትኃዊ ፉክክር የሚኖርበት ምርጫ ይኖራል” ብለው ለመናገር ያዳግታቸዋል። “በሚቀጥሉት ወራት ምን እንደሚከሰት አናውቅም” ሲሉ አስረድተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ አልጋ አውራሽ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በ4ኛው አጠቃላይ ምርጫ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫዎች መካከል 545 አሸንፎ ነበር። ኢሕአዴግ 52 የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ዘጠኝ የግል እጩዎች በተወዳደሩበት አምስተኛው አጠቃላይ ምርጫ 100% ቢያሸንፍም በተቃውሞ እና በውስጡ በገጠመው ፖለቲካዊ ቀውስ ህወሓትን ጥሎ ለመዋሀድ ተገድዷል።
የቀድሞውን ኢሕአዴግ ያዋሀዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ በተካሔደው ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ 96.8% አሸንፏል። የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት እና የፕሬስ ነጻነትን ማጠናከርን ጨምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥልጣን ሲይዙ ከገቧቸው ቃል ኪዳኖች መንግሥታቸው አፈግፍጓል። ዐቢይ “ተፎካካሪ” ይሏቸው የነበሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተከፋፍለው ተዳክመዋል።
በሀገሪቱ የሚካሔዱ ግጭቶች የጋረጡት ፈተና፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መዳከም እና የምኅዳሩ መጥበብ የግንቦቱ ምርጫ የይስሙላ እንዳይሆን የሚያሰጋ ነው። በመጪዎቹ ወራት መንግሥት “የፖለቲካ ምኅዳሩን ከፍቶ የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች” እንዲሳተፉ እና “ሐሳቦቻቸውን እንዲያራምዱ የሚያደርግ ከሆነ የይስሙላ ምርጫ ከመሆን ሊድን ይችላል። ነገር ግን ያ ይሆናል ወይ ብሎ ለማሰብ በጣም እቸገራለሁ” ሲሉ አቶ አማኑኤል አስረድተዋል።
አርታዒ ታምራት ዲንሳ























