በተራዘመ ግጭት ካለፈው ይልቅ መጭው ጊዜ ያሳስበናል፤ የአማራ ክልል ነዋሪዎች
Description
በአማራ ክልል በኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መራዘሙ ህይወት አስከፊ እንዳ,ደረገባቸው ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናገሩ ። በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ነዋሪዎች እንደሚሉት ግጭት አስቸኳይ መፍትሔ ካልተበጀለት መጪው ጊዜ አሳሳቢ ነው።
«ያው ባለቤቴም አይኗ ጠፍቷል፣ በለቅሶ ምክንያት ፤ ምን አጠቃላይ ልጃችን ብቻኮ አይደለም እኛም ሁላችንም በቁመና ሞተናል። እና መን ባክህ እያየሐውም አይደል በጣም አስቸጋሪ ነው። »
ድምጻቸውን የሰማነው በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን ወገል ጤና ነዋሪ ናቸው ። ከአንድ አመት በፊት ነበርበመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች ግጭት መሃል ልጃቸው እንደተገደለባቸው የነገሩን። የግጭቱ መራዘም የቤተሰባቸውን ተስፋ ከማጨለም ባሻገር አሁንም ድረስ ማህበረሰቡ እንዳይረጋጋ አድርጎ መቀጠሉን ነው የሚገልጹት።
«ማህበረሰቡ አንደኛ አለመረጋጋት፤ ከትናንት ወዲያ እንኳ በዚህ በዳውንት አካባቢ ጦርነት ነበር ። እና እህል ነው የተቃጠለው ፤ እህል እየተቃጠለ ፣ አርሶ አደሩ እንደልቡ ወጥቶ እንደልቡ መግባት ካልቻለ ፣ ሌላው ቢቀር በፋኖ ስም እየተደራጀ መንገድ ላይኮ ወጥተህ መግባት አትችልምኮ፣ ኪስህ ያለህን ነገር ይዘህ መንቀሳቀስ አትችልም። በጣም ትልቅ ችግር ነው ያለው።»
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ምስራቅ ጎጃም ውስጥ በምትገኘው የደብረ ወርቅ ከተማ ነዋሪም ይህንኑ ሃሳብ የሚጠናክር አስተያየት ነው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት። የግጭቱ መራዘም በርካታ ሰዎች እንዲያጡ ከማድረግ ባሻገር ተማሪዎች ገና በለጋ ዕድሜያቸው እንዲዳሩ እስከማድረግም አድርሷል ይላሉ።
« በህይወትም በርካታ ሰዎች እያጣን ነው ። በኤኮኖሚም ጎድቶናል፤ ሌላው ቢቀር መማር ማስተማር እና አካባቢ ከተማዋ ላይ ብቻ ነው ተንጠልጥሎ ያለው፤ያንን ተከትሎ ተማሪዎች እየተዳሩ ነው ፤ ሴቶች በተለይ ከ2ና ክፍል 3ኛ ክፍል ጀምሮ ጋብቻ ነው ያለው ፤ ባማህበራዊም በኤኮኖሚም እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው።»
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን በደቡብ ወሎ የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪውም ቀደም ሲል የተገለጹ ሃሳቦችን ያጠናክራሉ ።የግጭቱ መራዘም ብርቱ ጫና አሳድሮብናል ይላሉ ።
«እውነት ለመናገር የግጭቱ መራዘም ሁላችንም ላይ ጫና እየፈጠረ ነው። የመንገዶች መዘጋት ፣ ያንን ተከትሎ የኑሮ ውድነቱ ተንቀሳቅሶ ለመስራት ሁሉንም ገድቦ ይዞታል ። አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ማንም ሰው ተንቀሳቅሶ ወጥቶ መግባት እየቻለ አይደለም። »
የአማራ ክልል መንግሥት እና የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት አፋህድ የዘላቂ ሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን የክልሉ እና ብሔራዊ የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የክሉን መንግስት ወክለው የክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና አፋህድን በመወከል ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ መፈራረማቸው ሲገለጽ ሁለቱን ወገኖች በማደራደር ሂደት የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ተሳታፊዎች እንደነበሩም ተገልጿል።
ይህ መረጃ ከመውጣቱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ እና ጥቂት ታጣቂዎች ለኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ኃይል እጃቸውን መስጠታቸውሲዘገብ ቆይቷል። የአፋህድ መሪ እንደሆኑ ሲነገርላቸው የነበሩት አቶ እስክንድር በዚህ ስምምነት የነበራቸው ሚና ተለይቶ አልተገለጸም። ዶቼ ቬለ አቶ እስክንድር ነጋን ለማነጋገር ይገኙበታል በተባለ የስልክ ቁጥር ላይ በመደወል ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ሁለት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱን "ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል" በሚል ማባረሩን የተመለከቱ መረጃዎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት ሲሲራጩ መቆየታቸው ይታወሳል።
የክልሉ ነዋሪዎች እንደሚሉት በመንግስት እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከልዘላቂነት ያለውና አጠቃላይ ድርድር ተደርጎ መፍትሄ ካልተበጀ መጭው ጊዜ በርግጥ በእጅጉ ያሳስባቸዋል።
«ካለፈው ይልቅ የሚመጣው ነው የሚያሳስበን እውነት ለመናገር። ቢያንስ እስካሁን አንጻራዊ የገበያ መረጋጋት ነበር ፤ አሁን ግን ገበያው ጣሪያ ነክቷል። አሁን እያንዳንዱ ሰው አፍኖ ነው እንጂ ያልቸገረው ሰው የለም።»
«እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው አሁን ተስፋ ሁሉ ማጣት መጥቷል በነገራችን ላይ ። ልክ የሚጠብቀው ነገር አለ። በተለይ የመንግስት ሰራተኛው አሁን ወደ ገጠር ያለው ደሞዝ እንደቆመ ነው ፤ እና ተስፋ ማጣት ቀጣይ የሚታየው ነገር ስለሌ ወደ ፊት በዚህ ከቀጠለ ከዚህ የከፋ ነገር ይመጣል»
ታምራት ዲንሳ
ፀሐይ ጫኔ























