ኮርዶፋን ሌላዋ ኤል ፋሺር የመሆን ሥጋት እንደተጋረጠባት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ፎልከር ቱርክ አስጠነቀቁ
Description
በአንድ ወቅት አጋር የነበሩት የሱዳን ብሔራዊ ጦር እና በመሐመድ ሐምዳን ደጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አሰቃቂ ጦርነት ከገጠሙ ከሁለት ዓመታት በላይ አስቆጠሩ። በሁለቱ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያ በአሁኑ ወቅት በነዳጅ ዘይት ወደ በለጸጉየሱዳን ግዛቶች ተስፋፍቷል።
ባለፈው ወር የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ታጣቂዎችለአንድ ዓመት ገደማ አፍነው ጥቃት ሲፈጽሙባት የቆየችውን የሰሜን ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ ኤል ፋሽርተቆጣጥረዋል። ኤል ፋሽርን ለመቆጣጠር የተደረገው ውጊያ ግድያ፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ ስቅየት እና ሌሎች ግፎች የተፈጸሙበት እንደነበር የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።
ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ከሁለት ሣምንት ገደማ በፊት የሰሜን ኮርዶፋን ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውን ባራ በእጁ አስገብቷል። ከጥቅምት 25 ወዲህ ባለው ጊዜ “ከአየር በተፈጸሙ ጥቃቶች፣ በከባድ መሣሪያ ድብደባዎች እና በዘፈቀደ ግድያ ቢያንስ የ269 የሲቪል ሰዎች ሞት” ቢሯቸው እንደመዘገበ መዝግቧል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ፎልከር ቱርክ ተናግረዋል።
“በመላው ኮርዶፋን ግዛት የሚደረገው ኃይለኛ ውጊያ በመጨመሩ ምክንያት በሱዳን ሌላ የግፍ ማዕበል እንደሚከሰት እፈራለሁ” ያሉት ፎልከር ቱርክ “ኮርዶፋን ሌላዋ ኤል ፋሽር እንድትሆን መፍቀድ የለብንም” የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በባራ እና አካባቢው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ሥጋት አለው። የበቀል ግድያዎች፣ የዘፈቀደ እስር፣ አፈና፣ ወሲባዊ ጥቃት እና ሕጻናትን ጨምሮ ሰዎችን በግዳጅ ለውትድርና መመልመል እንደተስፋፋ ተቋሙ ይፋ አድርጓል።
ከተቀናቃኝ ኃይሎች ጋር በመተባበር የተከሰሱ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ፎልከር ቱርክ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የጥላቻ እና ከፋፋይ ንግግሮች አጠቃቀም በመጨመሩ ፍርሀት ነግሷል።
ፎልከር ቱርክ በኤል ፋሺር የተከሰቱ አሰቃቂ ኩነቶች በኮርዶፋን ሲደገሙ ማየት አስደንጋጭ እንደሆነ ገልጸዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አረመኔያዊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እና ውድመቶችን በጋራ እንዲያወግዝ የጠየቁት ኮርዶፋን ሌላዋ ኤል ፋሺር እንድትሆን ልንፈቅድ አይገባም ብለዋል።
“በተፋላሚ ኃይሎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉ ሁሉም ሀገራት ውጊያውን ለማቆም እና ግጭቱን የሚያባብሰውን የጦር መሣሪያ አቅርቦት ለመግታት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ” አቅርበዋል።
“ካለፈው ምንም አልተማርንም ማለት ነው?” ሲሉ የጠየቁት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር “ሌሎች ተጨማሪ ሱዳናውያን የአሰቃቂ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሰለቦች ሲሆኑ እጃችንን አጣጥፈን በመቀመጥ ልንፈቅድ አንችልም። እርምጃ መውሰድ አለብን፤ ይኸ ጦርነት አሁኑኑ ሊቆም ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
በአካባቢው የተቀሰቀሰው ግጭት ከ45,000 በላይ ሰዎች ለደሕንነታቸው በመሥጋት በኮርዶፋን ውስጥ አሊያም ከግዛቲቱ ውጭ መሸሻቸውን የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል። ፎልከር ቱርክ ግጭቱ ምግብ፣ መድሐኒት እና ሌሎች አስፈላጊ አቅርቦቶች ለማግኘት ችግር እንደፈጠረ ገልጸዋል። ገበሬዎች ወደ እርሻ ማሳዎች እና ገበያዎች መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ዕክል በመፍጠሩ በኮርዶፋን ግዛቶች የከፋ ረሐብ ሊስፋፋ እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
በኮሚሽነሩ ማብራሪያ መሠረት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች በሰሜን ኮርዶፋን ኢል ኦቤይድ ከተማ 45 ሰዎች ተገድለዋል። በሱዳን ብሔራዊ ጦር ጥቃት በደቡብ ኮርዶፋን በምትገኘው ካውዳ አብዛኞቹ ሲቪል የሆኑ 48 ሰዎች ተገድለዋል።
አርታዒ ጸሀይ ጫኔ























