ውይይት፦ ምን ያስተሳስረው ይሆን? ግጭት ኢትዮጵያ እና ጎረቤት አገራት
Description
ምሥራቅ አፍሪቃን ጦርነት እና ውጥረት ሰቅዞ ከያዘ ሰነባብቷል ። ሰሜን ኢትዮጵያ የትግራዩ ጦርነት በሚል የሚታወቀው ውጊያ ትግራይ፤ አማራ እና አፋር ክልሎችን አድቅቆ፤ የበርካቶችን ሕይወት ገብሮ አልፏል ። በዚያ ግን አላባቃም ። የፕሪቶሪያው የተኩስ ማቆም ስምምነት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል ከተደረገ በኋላ በስምምነቱ እንድንሳተፍ አልተደረግንም የሚሉ ቅሬታዎች ከየአቅጣጫው አስተጋብተዋል ።
የኢትዮጵያ መንግሥትን ደግፎ በትግራይ ክልል ጦር ያዘመተው የኤርትራ መንግሥት ያኔ ከደገፈው ኃይል ጋር አሁን ዐይን እና ናጫ ከመሆንም አልፈው መፋጠጣቸው ይዘገባል ።
በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች ከመንግሥት ጦር እና ተባባሪዎቹ ጋር መፋለም መጀመራቸው ከተነገረ ዓመታት ተቆጥሯል ። አማራ ክልልን በስፋት በምትዋሰነው ሱዳን የጦር ኃይሏ እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ውጊያ ከገቡ እዚያም ዓመታት ተቋጥሯል ። የሱዳን ጦርን እና ዋነኛ ባላናንጣው የፈጥኖ ደራሹን ኃይል የሚደግፉ የባሕረ ሠላጤው አገራት የኢትዮጵያ መንግሥትን እና የኤርትራ መንግሥትን በየፊናቸው እንደሚደግፉ ይነገራል ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰተው ግጭት ሱዳን ውስጥ፥ የሱዳኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ነጸብራቁ በጉልኅ ይታያል ። ከፍ ሲል ግብጽ ከወደታች ደግሞ ሶማሊያም በግጭት ውጥረቱ ስማቸው በተደጋጋሚ ይነሳል ። የምሥራቅ አፍሪቃው ግጭት እና ውጥረት በአገራቱ ላይ ያስከተለውን ሰብአዊ ቀውስ፣ ፖለቲካዊ ውጥረት እና ኤኮኖሚያዊ ተግዳሮት በዛሬው ውይይት ለመዳሰስ እንሞክራለን ።
በውይይቱ 4 እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፦
አቶ ባይሳ ዋቅ ወያ፤ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሞያ እና የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲፕሎማት
አቶ አብድራህማን ሠይድ፤ የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኝ
አቶ መስፍን አማን የፖለቲካ ተንታኝ ብሎም ተማሪ
አቶ ያሬድ ኃይለማሪያም፤ የህግ ባለሞያ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች በአሁኑ ወቅት አማካሪ ናቸው ።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ እና በጎረቤት አገራት መካከል ስላለው ወቅታዊ ግጭት እና የፖለቲካ ውጥረት በማብራራት ይጀምራሉ ። ኢትዮጵያን ጨምሮ በጎረቤት አገራቱ መካከል ያለውን ግጭት እና ፖለቲካዊ ውጥረት የሚያያይዘው ነገር የሚሉትንም ይተነትናሉ ። በምሥራቅ አፍሪቃ ፖለቲካዊ ውጥረት እና ግጭት ረዣዥም እጆቻቸውን ስለዘረጉ አገራት በማንሳት በዋናነት እነማን እንደሆኑም ይጠቅሳሉ ። የባለረዣዥሞቹ አገራት ተጽእኖ ጥልቀት እና ስፋቱ ይዳሰሳል ። በስተመጨረሻም በቀጣናው የቀጠለው ጦርነት ተባብሶ መልኩን በመቀየር ተጨማሪ እልቂት ብሎም ብርቱ ሰብአዊ ቀውስ እንዳያስከትል መደረግ አለበት የሚሉትንም ተወያዮች ያካፍላሉ ።
ሙሉውን ውይይት በድምፅ ማእቀፉ በኩል ማድመጥ ይቻላል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ























