DiscoverDW | Amharic - News«ለሕጉ ብለን ላለመሰረዝ በምርጫው እንወዳደራለን» ኦነግ
«ለሕጉ ብለን ላለመሰረዝ በምርጫው እንወዳደራለን» ኦነግ

«ለሕጉ ብለን ላለመሰረዝ በምርጫው እንወዳደራለን» ኦነግ

Update: 2025-12-10
Share

Description

የኢትዮጵያ ሰባተኛ ብሔራዊ ምርጫ በተያዘው ዓመት ሚያዚያ 24 ቀን እንደሚካሄድ ምርጫን የሚያስፈጽመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ሰኞ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ ቦርዱ ይካሄዳል ወይስ አይካሄድም በሚል በርካቶች ሲወዛገቡበት የነበረው የዘንድሮ ምርጫን ለማካሄድ ቀኑን ከመቁረጥ ጀምሮ የክንውኖች የጊዜ ሰለዳውንም ይፋ በማድረግ አስተያየቱን ሰጥቶበታል፡፡



«ምርጫውን በማድረግ እና ባለማድግ መካከል ያለው አጣብቂኝ»



በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባለው የፀጥታ ችግር እና አስቻይ የምርጫ አውድ አለመኖሩን በመጥቀስ ከአምስት ዓመታት በፊት ከተካሄደው ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ እራሳቸውን ካገለሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በዘንድሮ ብሔራዊ ምርጫ ግን ተሳትፎውን እንደሚያደርግ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡



የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዓለማየሁ ድሮ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት ኦነግ በምርጫው ላይ ለመሳተፍ አስቻይ ሁኔታዎቹ ላይ ኮሚቴ አዋቅሮ እየሠራበት ይገኛል፡፡ "የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አሁን በሥራ ላይ ያለው ቢሮው አዲስ አበባ ያለው ዋና ቢሮው ብቻ ነው” ያሉት አቶ ዓለማየሁ በአገሪቱ በርካታ ቦታዎች ባለው ግጭት ምክንያት ለምርጫ የተሟላ ሁኔታ ባይኖርም "ምርጫውን አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ከሁለት ጊዜ በላይ ማቋረጥ አይችልም በሚለው የኢትዮጵያ ሕግ ስላለ ሕጉን ለማክበር ሲባል የምንሳተፍ ይሆናል” ብለዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ እስካሁን እጩዎችን አለማስመዝገቡን የገለጸው ኦነግ ወደፊት ምን ያህል እጩዎችን እንደሚያስመዘግብም አሳውቃለሁ ብሏል፡፡



የምርጫው ተሳትፎና አስቻይ ሁኔታው ላይ ያለው ተግዳሮት



በሰባተኛው ብሔራዊ ምርጫ ላይ የመሳተፍ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን የገለጸው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እውነተኛ የምርጫ ተፎካካሪነቱን በአቅሙ ልክ የሚገልጽበት የምርጫ አውድ አለመኖሩንም በአስተያየታቸው ያብራሩት የኦነግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ዓለማየሁ ድሮ፤ አስቻይ የፍትሃዊ ምርጫ ሂደትን የሚፈትኑ ያሏቸውንም ተግዳሮቶች ዘርዝረዋል፡፡ "አሁን የገጠመን ዋናው የፍትሃዊ ምርጫ ተግዳሮቱ በኦሮሚያ ባለፉት ስድስት ዓመታት እየተስተዋለ ያለው የጸጥታ ሁኔታው ነው” በማለትም ይህም በህዝብ መሃል በመጓጓዝ የምርጫው እንቅስቃሴ ማድረግን ፈታኝ እንደሚያደርግ አንስተዋል፡፡



"ኦነግ ለአምስት ዓመታት ያህል ሁሉም ቢሮዎቹ ተዘግተው አመራርና አባላቱም በእስር ላይ ቆይተዋል” ያሉት የኦነግ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አሁንም ባለው ሁኔታ የተሻለው በአዲስ አበባ ያለው ዋና ቢሮው ተከፍቶ እንቅስቃሴ መጀመሩ ብቻ ነው ብለዋል፡፡ በመላው ኦሮሚያ በየዞንና ወረዳዎች ያሉ ከ300 የላነሱ ጽሕፈት ቤቶቹ አሁንም እንደተዘጉ ነው ያለው ኦነግ በዚህ አውድ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ የሚታሰብ ባይሆንም ፓርቲው ባለው አቅም ለምርጫው ዝግጁነት የሚያስፈልጉት ተግባራትን እየከወነ መሆኑን አመልክቷል፡፡



ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር ሊደረግ የታሰበው ምክክር ከምን ደርሷል?



የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከዚህ በፊት ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ጋር በኦሮሚያ ክልል ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ለመወያየት በሚል ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የቀረበው ጥያቄ ከምን ደርሶ ይሆን በሚልም የተጠየቁት የኦነግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ዓለማየሁ ድሮ፤ "የእኛ ፍላጎት በኦሮሚያ ያለው የፀጥታ ጉዳይ መረጋገጥ አለበት የሚለው ነው” ብለዋል፡፡ የጦርነት ምዕራፍ አብቅቶ በእጅጉ የሚፈለገው ሰላም መስፈን አለበት በማለትም "ሰላም በሌለበት አይደለም ምርጫ ተራ የህይወት ስራዎችንም መስራት አዳጃች ሆኖ ታይቷልም” ያሉ ሲሆን፤ ከመንግስት ጋር ለምርጫ ተስማሚ የሆነ መሰረት የሚጥሉ ጉዳዮች ላይ የመመካከር ውጥን የነበረ ቢሆንም እስካሁን ያገኘው ምላሽ ግን አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡



በኦነግ አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባትና የምርጫ ቦርድ ጥያቄ



የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ ኦነግ በአመራሮቹ መካከል ተፈጥሮ የቆየውን ውዝግብ በማንሳት ፓርቲው ሁሉንም አመራሮች ያላገለለ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሄድ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ይህ ለፓርቲው የምርጫ ተሳትፎ እንቅፋት ይፈጥር ይሆን የተባሉት አቶ ዓለማየሁ፤ "በኦነግ ውስጥ የተፈጠረ ክፍፍል የለም፤ የሆነው ነገር ከኦነግ ወጥተው የራሳቸውን ኦነግ እንመሰርታለን ያሉ ወገኖች ከምርጫ ቦርድ ጋር ስካሰሱ ነበር፡፡ ስለዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ከምርጫ ቦርድ ጋር እየተነጋገርን ነው ያለነው፤ ቦርዱ ምላሽ ስሰጠን ወይም ጉባኤውን አሁን አድርጉ ስለን ማድረግ ነው” በማለትም ይህ የጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ አለማድረግ በምርጫው ተሳትፎ ላይ እንቅፋት ይሆናል የሚል ስጋት አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡



ሥዩም ጌቱ



ማንተጋፍቶት ስለሺ



ታምራት ዲንሳ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

«ለሕጉ ብለን ላለመሰረዝ በምርጫው እንወዳደራለን» ኦነግ

«ለሕጉ ብለን ላለመሰረዝ በምርጫው እንወዳደራለን» ኦነግ

ሥዩም ጌቱ