በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ላይ ፓርቲዎች የሰጡት አስተያየት
Description
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ማክሰኞ ይፋ ባደረገው የምርጫ የጊዜ ሠሌዳ መሠረት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚከናወን ዐሳውቋል ። ቦርዱ ከድምፅ መስጫው ዕለት አስቀድሞ የዕጩዎች ምዝገባ ከጥር አንድ እስከ የካቲት አንድ ቀን ለአንድ ወር፣ የመራጮች ምዝገባ ደግሞ ከየካቲት 7 እስከ መጋቢት 7 ባለው አንድ ወር ውስጥ እንደሚከናወን ይፋ አድርጓል። ከስድስት ወራት በኋላ የሚደረገው ምርጫ የመጨረሻው ይፋዊ ውጤት ደግሞ ሰኔ 4 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ይገለፃል ተብሏል። ይህንን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በሚመለከት ጥቂት የፖለቲካ ድርጅቶች አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ ሰጥተዋል ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከስድስት ወራት በኋላ የሚደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሥራዎች ከጥር 1 ቀን፣ እስከ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚከናወን ከግንቦት 20 እስከ ግንቦት 23 ድረስ ደግሞ የጥሞና ጊዜ እንደሚሆን ይፋ ያደረገው ሰነድ ላይ ተጠቅሷል።
«ከሞላ ጎደል [የምርጫ የጊዜ ሰሌዳው] አሠሪ ነው» - ኢዜማ
በዚህ የቦርዱ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ አስተያየት ከጠየቅናቸው የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የሆነው ኢዜማ ፓርቲዎች በጊዜያዊ የምርጫ ሰሌዳው ላይ ጥቅምት 10 ተወያይተው እንደነበር የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
የምርጫ ወረዳን መሠረት ያደረገ አደረጃጀት ያለው ኢዜማ "የምርጫ ማኔጅመንት ኮሚቴ" የሚባል መዋቅር ዘርግተው እየሠሩ መሆኑን ዋና ፀሐፊው ተናግረዋል። ፓርቲው በምን ያህል ቦታ እና በምን ያህል የዕጩ ብዛት ለውድድር እንደሚቀርብ በሂደት የሚገለጽ እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢዜማ ምርጫ ወረዳዎቹ ዕጩዎቻቸውን በጉባኤ መርጠው ለዋናው መሥሪያ ቤት እንዲያሳውቁ መስፈርት አዘጋጅቶ ለወረዳዎቹ መላኩንም አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ነግረውናል።
የድምፅ መስጫው ዕለት ሰኞ ስለሚሆን «መሥሪያ ቤቶች ዝግ ሊሆኑ ይገባል» - ኢሕአፖ
ለባለፈው ሳምንት ሕዝባዊ ስብሰባ በሆቴል ውስጥ ለማድረግ ጠርቶ መከልከሉን ያስታወቀው ኢሕአፓ ለምርጫው "ያለው ጊዜ ውስን ነው" ሲል ሕዝባዊ ስብሰባ እነዳያደርግ ከመከልከሉ ባለፈ ዛቻ እንደሚደርስበት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አብርሃም ሃይማኖት ተናግረዋል። "እነዚህን ኹኔታዎች ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ ቀላል ሊያያቸው አይገባም" በማለት ስለ ጊዜ ሰሌዳው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
«የዘንድሮ ምርጫ ምርጫ አይሆንም» - ኦፌኮ
የፖለቲካ ፓርቲው ስብስብ የሆነው - ኮከስ ሰብሳቢ እና የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ፓርቲያቸው የምርጫ ሕጉን ለማሟላት ብቻ ዐሥር ሰዎችን ለፓርላማ ለውድድር አቅርበው በምርጫው ውስኝ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው ነግረውናል። ስለምርጫ የጊዜ ሰሌዳም ሆነ በጥቅሉ ስለ ምርጫው በሰጡት አስተያየት በሁለት ምክንያቶች የዘንድሮው ምርጫ ምርጫ አይሆንም" ይላሉ።
እንደ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ገዢው ብልጽግና ፓርቲም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥ የፓርቲውን አንድ የሥራ ኃላፊ በስልክ ለማግኘት ያደረግኩት ጥረት አልተሳካም።
የፖለቲካ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶችን ቅድሚያ በመንግሥት ፖለቲካዊ ርምጃ መፍትሔ እንዲሰጣቸው በመጥቀስ ለምርጫው አስቻይ ኹኔታ የግድ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ























