የዩክሬን እና አውሮጳ ዕቅድን ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ይቀበሉት ይሆን?
Description
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም በሚል ያቀረቡት ባለ 28 ነጥብ የሰላም ምክረ-ሐሳብዕቅድ ውጤት ያስገኘ አይመስልም ። የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ስለእቅዱ ከአውሮጳ ኅብረት መሪዎች ጋር ለንደን እና ብራስልስ ውስጥ ተነጋግረዋል ። ሮምንም በዚሁ ጉዳይ ጎብኝተዋል ። ዩክሬን እና የአውሮጳ አገራት መሪዎች ዩናይትድ ስቴትስ ያቀረበችው የሰላም እቅድን ከልሰው በቅርቡ «የተጣራ» ያሉትን ሠነድ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን ትናንት ይፋ አድርገዋል ። በሌላ ጎኑ ደግሞ ለፖለቲኮ ቃለ ምልልስ የሰጡትፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪን እና የአውሮጳ ኅብረትን ሥራቸውን በሚገባ አልከወኑም ሲሉ በብርቱ ወቅሰዋል ።
የብራስልስ ወኪላችን ገበያው ንጉሤ፦ «ለመሆኑ የዩክሬን እና አውሮጳ መሪዎች ፍላጎት በዋናነት ምንድን ነው?» በሚል ለቀረበልት ጥያቄ ስያብራራ ዩክሬን እና አውሮጳውያን በሰላም ሐሳቡ ላይ እንድንወያይ አልተደረግንም እኛን ያካተተ አይደለም በሚል በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያሰሙ እንደነበር ገልጧል ።
ተከለሱ የተባሉት ሠነዶች ጦርነቱን ለማቆም በሚል የተዘጋጁ መሆናቸውን የጠቀሱት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ «ሁሉም ነገር» ጦርነቱን ለማስቆም ሩሲያ ካላት ፍላጎት ጋር የተመሰረተ ነው ብለዋል ። አዲስ «ተከለሰ» የተባለው ሠነድ ሦስት ዋና ጉዳዮችን ማካተቱን ገበያው ጠቅሷል ። አንደኛው የሰላም ሐሳቡ የዩክሬንን ፍላጎት እንዲሁም የአውሮጳን ጥቅም ባስጠበበቀ መልኩ በዓለም አቀፍ ሕግ ማእ ቀፍ እንዲዘጋጅ ይገባል መባሉን ገበያው ጠቅሷል ። ሁለተኛው ደግሞ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ዩክሬን ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከአውሮጳውያን በኩል ስለምታገኘው ዋስትና ይመለከታል ። ሦስተኛው ደግሞ የግዛት ጥያቄን የሚመለከት ነው ። እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የዩክሬን የግዛት ጥያቄ መነካት እንደሌለበት ይጠይቃል ።
። ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ፦ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በመሆን ነገሮች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉበትን መንገድ ለማቀላጠፍ መዘጋጀታቸውን ትናንት በይፋዊ የኤክስ ማኅበራዊ መገናኛ አውታራቸው ዐሳውቀዋል ። ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በዩክሬንም ሆነ በአውሮጳ እንዳልተደሰቱ በመግለጥ ወርፈዋቸዋል ። ዩክሬን እና አውሮጳ ከፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ምን ሊጠብቃቸው ይችላል? ድጋፍ ያስገኛቸዋል ወይ? ገበያው ንጉሤ ይህን እና ሌሎች ጉዳዮችንም ያብራራል ።
ሙሉ ቃለ መጠይቁን በማገናኛው በኩል ማድመጥ ይቻላል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ገበያው ንጉሤ
ታምራት ዲንሳ























