የአቢዬ ግዛት ዕጣ ፈንታን ያራዘመው የሁለቱ ሱዳኖች የጸጥታ ኹኔታ አሳስቧል
Description
የአብዬ ግዛት ዕጣ ፈንታ መፍትሔው ገና ነው
ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን በገጠማቸው የውስጥ ቀውስ በይገባኛል በሚወዛገቡባት እና በነዳጅ ዘይት በበለጸገችው የአቢዬ ግዛት ዕጣ ፈንታ ቁርጡ እንዳይታወቅ ተግዳሮት መፍጠሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመለከተ። የግዛቲቱን ዕጣ ፈንታ ለመመልከት ባለፈው ረቡዕ የተሰባሰበው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የተከፋፈለ አቋም መያዙ ተሰምቷል። አሜሪካ ቅድመ ሁኔታ ስታስቀምጥ የመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪቃ ህብረት ለሚመራው አሸማጋይ ቡድን ድጋፍ አደርጋለሁ ብሏል።
ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የሚወዛገቡባት እና እስካሁንም መፍትሄ ባጣችው የአብዬ ግዛት ሲደረጉ የነበሩ ንግግሮች መገታታቸው ውስብስቡ ችግር እንዲቀጥል ማድረጉ ነው የተገለጸው። ይህንኑ ተከትሎ በግዛቲቱ የተሰማራውን የሰላም አስከባሪ ኃይል ቆይታ ለማራዘም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የተያዘውን ዕቅድ አሜሪካ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጧ በዕቅዱ ተግባራዊነት ላይ ተጨማሪ ተግዳሮት ኾኗልም ነው የተባለው።
የመንግስታቱ ድርጅት ምልከታ
በተባበሩት መንግታት ድርጅት የአፍሪቃ ጉዳዮች ረዳት ዋና ጸሐፊ ማርታ ፓቤ ለጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በሱዳን ውስጥ ያለው ተለዋዋጭ ጦርነት እና በደቡብ ሱዳን ያለው ያልተረጋጋ ፖለቲካዊ ኹኔታ የአብዬ ግዛት ዕጣ ፈንታን ለመወሰን አዳጋች አድርጎታል።
"በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን መካከል በአቢዬ እና በድንበር ጉዳዮች ላይ የነበረው የፖለቲካ ሂደት በጎርጎርሳዊው ሚያዝያ 2023 የሱዳን የርስ በርስ ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በነበረበት እንደ ቆመ ነው። ነገር ግን ከዚያ በኋላ በግንቦት ወር ሁለቱም ወገኖች ከተባበሩት መንግስታት ጊዜያዊ የጸጥታ ሃይል ለአቢዬ (UNISFA) ስትራቴጂክ ግምገማ ቡድን እና ከተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረት ድጋፍ በአቢዬ ላይ ግንኙነታቸውን ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው አሳውቀዋል ።”
በተባበሩት መንግታት ድርጅት የአፍሪቃ ጉዳዮች ረዳት ዋና ጸሐፊ ማርታ አማ አክያ ፖቤ ይህን ያሉት ባለፈው ወር የደቡብ ሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወደ ፖርት ሱዳን ተጉዘው በሁለቱ ሃገራት የጸጥታ እና በኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የትብብር ስምምነቶችን ለማስቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው።
እንደዚያም ሆኖ ግን ሁለቱም ሃገራት አሁን በውስጣቸው በሚታመሱባቸው የርስ በርስ ግጭት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት የአቢዬን የመጨረሻ ዕድል ፈንታ ለመወሰን የሚያስችለውን ሂደት ለማስቀጠል እንዳላስቻለቸው ነው የተገለጸው ። ረዳት ዋና ጸሐፊዋ ለጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ያሳወቁትም ይህንኑ ነው።
«የአብዬ ጉዳይ ሂደቱን ከመጨረሻው ምዕራፍ ለማድረስ ብዙ ፈተናዎች አሉበት። እነዚህም በሱዳንእየተካሄደ ካለው ጦርነት እና በደቡብ ሱዳን ካለው ያልተረጋጋ ፖለቲካ ጋር የተያያዙ ጎዳዮች ይገኙበታል። ደቡብ ሱዳንም ሆነች ሱዳን ፍላጎታቸውን ከመግለጽ ባለፈ አሁን ያሉ ስምምነቶችን ተግባራዊ ማድረግ እንዲያፋጥኑ፣ እንዲሁም ተግዳሮቶችን ለመፍታት የተቀመጡ ስልቶችን እንዲጠቀሙ አሳስባለሁ።»
የሰላም አስከባሪ ኃይል ስምሪት ጊዜን ማራዘም
ሁለቱ ሃገራት የአብዬን የወደፊት እና ዘላቂ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ጊዜ በወሰደባቸው ቁጥር በግዛቲቱ የሰፈረውን የሰላም አስከባሪ ኃይል የቆይታ ጊዜ እንደማራዘሙ መጠን ምክር ቤቱ ጉዳዩን እንዲያጤነው አድርጓል። ይህ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ተግዳሮት ይዞ ሳይመጣ አልቀረም ።
አሜሪካ በምክር ቤቱ የቀረበውን የሰላም አስከባሪ ኃይል በግዛቲቱ የቆይታው ጊዜ እንዲራዘም ለቀረበ ምክረ ሃሳብ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች። አሜሪካ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ ቆይታ እንዲራዘም ሁለቱ ሃገራት በጎርጎርሳዊው 2011 የደረሱትን የሰላም ስምምነት ማጽናታቸውን ማረጋገጥ አለብኝ ብላለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጓንግ ኮንግ ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር በሱዳን የጦርነቱ መቀጠል በደቡብ ሱዳን ጸጥታ ላይ ብርቱ ተግዳሮት ደቅኗል። በሁለቱም ሃገራት በኩል የታጠቁ ኃይሎች ድንበር ዘለል እንቅስቃሴ ማድረጋቸው በአካባቢው የጸጥታው ሁኔታ እንዲባባስ አድርጎታል ። ልዑኩ እንዳሉት ሂደቱን ለማስቀጠል የአፍሪቃ ህብረት መራሹ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ እንደሚጠባበቁ ተናግረዋል።
"ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን የአቢይን የወደፊት ሁኔታ በተመለከተ የፖለቲካ ንግግራቸው ለማደስ ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ በ1108 የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ጉባኤ መሰረት የአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ሂደት ለመደገፍ እጠባበቃለሁ"
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ወደ ኋይት ሀውስ ከተመለሱ በኋላ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ላይ የሰላ ትችት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል። ፕሬዚዳንቱ ኣሜሪካ ለዓለም አቀፍ ተቋማት የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ እንድትቀንስ አልያም ሙሉ ለሙሉ እንድትሰርዝ በያዙት አቋምም አሜሪካ ለመንግስታቱ ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የምታደርገውን የበጀት አስተዋፅኦ በእጅጉ ቀንሷል። ይህም አሁን በአቢዬ ግዛት ጉዳይ ላይ ካስቀመጠችው ቅድመ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በሚደረጉ ንግግሮች ላይ ሳያጠላ እንደማይቀር ነው የተገለጸው።
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ























