DiscoverDW | Amharic - Newsየካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች “እባካችሁ በተሰጣችሁ ፈቃዶች ላይ አትተኙባቸው”
የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች “እባካችሁ በተሰጣችሁ ፈቃዶች ላይ አትተኙባቸው”

የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች “እባካችሁ በተሰጣችሁ ፈቃዶች ላይ አትተኙባቸው”

Update: 2025-12-03
Share

Description

ባለወረቶች የግምዣ ቤት ሰነዶች በቀጥታ እንዲገዙ ለማመቻቸት በተዘረጋው “ጸጋ ካፒታል” በተካሔዱ ያለፉት አራት ጨረታዎች መንግሥት ከግለሰባዊ እና ተቋማዊ ኢንቨስተሮች ከ125 ቢሊዮን ብር በላይ እንደተበደረ የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ ተናግረዋል። ዶክተር እዮብ “በፍጥነት እያደገ እና እየተለወጠ ነው” ባሉት ሥርዓት በአጠቃላይ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ዝውውር መፈጸሙን በአዲስ አበባ በመካሔድ ላይ በሚገኘው የካፒታል ገበያ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል።



“ጸጋ ካፒታል” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሣምንት ሥራ ላይ ያዋለው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምዣ ቤት (Central Securities Depository) አካል ነው። ለረዥም ዓመታት በወረቀት ሲከናወን የቆየውን የአክሲዮን ግብይት ግዑዝ አልባ የሚያደርገው የሰነዶች ካዝና ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያዋን ከአምስት አስርት ዓመታት ገደማ በኋላ እንደገና መልሳ ሥራ ለማስጀመር በምታደርገው ጥረት ቁልፍ መሠረተ-ልማት ሆኗል።



የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ በሐምሌ 2017 በይፋ ሥራ ሲጀምር ለገበያ ካቀረባቸው መካከል የመንግሥት የግምዣ ቤት ሰነዶች ይገኙበታል። ግብይቱ ከዚህ ቀደም ባንኮች እና የጡረታ ፈንዶች ብቻ ይሳተፉበት የነበረውን የግምዣ ቤት ሰነድ ገበያ ፍላጎት ላላቸው ሌሎች ግለሰባዊ እና ተቋማዊ ባለወረቶች የከፈተ ነው።



የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ “የካፒታል ገበያ ልማት የረዥም ጊዜ የዕዳ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ፣ የመንግሥት እና የግል ዘርፍ አጋርነትን ለማጠናከር እና ዘላቂ ዕድገትን ለማራመድ” ጥሩ አማራጭ እንደሚሆን ተናግረዋል። አቶ አሕመድ ገበያው “በሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብ የሚወጡ የዕዳ ሰነዶችን በማስፋፋት” ኢትዮጵያ በሒደት የውጭ ብድር ጥገኝነቷን በመቀነስ ወደ ሀገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጭ ለመዞር እንድትችል ያደርጋል የሚል ተስፋ አላቸው።



ኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤቶች እና የኃይል ማመንጫዎችን ጨምሮ መሠረተ-ልማቶች ለመገንባት በመንግሥት በጀት ላይ ብቻ ጥገኛ ልትሆን እንደማትችል ያመኑት የገንዘብ ሚኒስትሩ ማዘጋጃ ቤቶች ወይም የከተማ አስተዳደሮች የሚያወጧቸውን ቦንዶች ጨምሮ አዳዲስ የዕዳ ሰነዶች በአማራጭነት ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።



ከገንዘብ ሚኒስቴር በተጨማሪ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን እና የአፍሪካ ልማት ባንክን የመሳሰሉ በርካታ ተቋማት የሚሳተፉበት ካፒታል ገበያ የማቋቋም ሒደት የመንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል ነው። ኩባንያዎች ሥራቸውን ለማከናወን ወይም ለማሳደግ የሚያስፈልጋቸውን ካፒታል ለማሰባሰብ የሚችሉበት አዲስ ሥርዓት የሚዘረጋው ገበያ የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከፍ ያለ ተስፋ የጣሉበት ሆኖ ይታያል።



ዶክተር እዮብ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ “መዋቅራዊ ሽግግር በሚያደርግበት ወቅት ካፒታል ገበያዎች ገንዘብ በማሰባሰብ፣ የገንዘብ አቅርቦትን በማሻሻል እና መዋዕለ-ንዋዮችን ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራን ወደሚፈጥሩ ዘርፎች በመምራት” ላቅ ያለ አስተዋጽዖ እንደሚኖራቸው አስረድተዋል። የመንግሥት የዕዳ ሰነዶች በኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ በኩል ተመዝግበው ለሽያጭ የቀረቡበትን ሥርዓት ዶክተር እዮብ “ታሪካዊ” ብለውታል።



ግብይቱ መንግሥት የበጀት ጉድለት ለመሙላት ለሚበደርበት ሥርዓት “ክፍት፣ ተወዳዳሪ እና በገበያ የተመሠረተ” መድረክ ፈጥሯል። የመንግሥት የዕዳ ሰነዶች እና አክሲዮኖች የሚወጡበት እና የሚሸጡበትን ሥርዓት የሚቀይረው ካፒታል ገበያ ሀገሪቱ ስትከተል የቆየችውን መንገድ ማስተካከል ይጠይቃል።



እስካሁን በነበረው አሠራር ኩባንያ ማቋቋም የሚፈልጉ አደራጆች ወይም መሥራቾች የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለመሰብሰብ የአክሲዮን ድርሻዎችን ሲሸጡ ቆይተዋል። ባንኮችን ጨምሮ በርከት ያሉ የአክሲዮን ማኅበራት የተመሠረቱት በዚሁ የአሠራር ስልት ነው።



በገበያው ውስጥ የሚገኙ የአክሲዮን ማኅበራትም ይሁኑ ወደፊት የሚቋቋሙ ኩባንያዎች ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል። ባለሥልጣኑ እስከ ኅዳር 16 ቀን 2018 ሙዓለ ንዋዮቻቸውን ያላስመዘገቡ “የአክሲዮን ማኅበራት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ጥብቅ” ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።



በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን መመሪያ መሠረት የአክሲዮን ማኅበራት በመጀመሪያ ደረጃም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ ገበያ ለመሳተፍ ከ50 በላይ ባለአክሲዮኖች ሊኖራቸው ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ የአክሲዮን ማኅበሩን ዓላማ፣ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚከተለውን ስልት እና እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል የሚያብራራ የደንበኛ ሳቢ መግለጫ አዘጋጅተው በተቆጣጣሪው ባለሥልጣን መጽደቅ አለበት። የደንበኛ ሳቢ መግለጫ የኩባንያውን የኦዲት ሪፖርትና ያለፉት ዓመታትን ትርፍ የመሳሰሉ ቁልፍ ጉዳዮችን ጭምር የሚይዝ ነው።



የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልቁ ባለፉት ዓመታት ተቋማቸው “የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት ለማዘመን፣ የቁጥጥር ማዕቀፍን ለማጠናከር እንዲሁም ለጠንካራ እና ተዓማኒ ካፒታል ገበያ መሠረት ለመጣል” የሚያስችሉ እርምጃዎች ሲወስድ እንደቆየ ተናግረዋል። “ንቁ፣ ተደራሽ፣ ከቀጠናዊ እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓቶች የተሳሰረ ገበያ” የማቆም የአንድ ወቅት ርዕይ “አሁን እውን ሆኗል” ሲሉ ተደምጠዋል።



ዋና ዳይሬክተሯ “አስራ ሦስት አካባቢ የሚሆኑ የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች ፈቃድ ተሰጥቷቸው በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የሚመራ ኢንዱስትሪ ተከፍቷል” ሲሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና በካፒታል ገበያ ምሥረታው ሒደት የተለያየ ሚና ያላቸው ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ጉባኤ አስረድተዋል።



በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድ ከተሰጣቸው መካከል አራቱ የኢንቨስትመንት ባንኮች ሲሆኑ ሦስቱ በሥራ ላይ የሚገኙ ባንኮች በተቀጥላ ኩባንያነት ወይም በሽርክና ያቋቋሟቸው ናቸው። አራቱ ተቋማት አዋሽ ካፒታል አክሲዮን ማህበር፣ ሲቢኢ ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ፈርስት አዲስ ኢንቨስትመንት ባንክ እና ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ናቸው።



ባለሥልጣኑ ከሰጣቸው ፈቃዶች መካከል የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ እና ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አከናዋኝ ጭምር ይገኙበታል። ፈቃድ የተሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች ቁጥር ቀስ በቀስ እያደገ ሲሔድ ገበያው ቅርጽ መያዝ ቢጀምርም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ ግን “እባካችሁ እባካችሁ በተሰጣችሁ ፈቃዶች ላይ አትተኙባቸው” ሲሉ ተደምጠዋል።



ብሩክ “አንዳንዱ ነገር በጣም አሳፋሪ ነው። ምክንያቱም እኛን ስለማገዝ እየተነጋገርን ነው። የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ደላላ እንፈልጋለን። አማካሪዎች እንፈልጋለን። ነገር ግን ፈቃድ ስለተሰጣችሁ ብቻ ሥራው አብቅቷል ማለት አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል። ፈቃድ የወሰዱ የካፒታል አገልግሎት አቅራቢዎች ሥራውን በሚገነዘቡ ብቁ ባለሙያዎች ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ፣ ስትራቴጂዎቻቸውን እንዲያዘጋጁ እና ሐሳብ እንዲያቀርቡ መክረዋል።



“እኔ ራሴ ችግሩ ምን እንደሆነ መለየት አልፈልግም። ችግሩን ለእኔ የምትፈልጉልኝ እናንተ ናችሁ። ለእኔ መፍትሔ የምታቀርቡት እናንተ ናችሁ። ከዚያ እኔ ካፒታሉን አቀርባለሁ” በማለት የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች ከደንበኞቻቸው ጋር ሊኖራቸው ስለሚችል የሥራ ግንኙነት ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሚናቸው ገበያ ማፈላለግ፣ ማስተዋወቅ እና ማስተማርን እንደሚጨምርም አስገንዝበዋል።



ከዶክተር ብሩክ አንደበት የተሰማው መሰላቸት ኢትዮጵያ ንቁ የካፒታል ገበያ ለማቆም በምታደርገው ጥረት ውስጥ ሥራቸውን በብቃት የሚያከናውኑ ተቋማት አለመኖር ሊያስከትል የሚችለውን ፈተና የጠቆመ ነው። ብሩክ ከኅዳር 2015 እስከ ነሐሴ 2016 የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል። ባለሥልጣኑ በዶክተር ብሩክ በተመራባቸው ጊዜያት “የቁጥጥር ማዕቀፎችን በማዘጋጀት እና የካፒታል ገበያ ተቋማዊ አቅምን በማሳደግ ላይ ያተኮሩ” ሥራዎች አከናውኗል።



ብሩክ ኃላፊነቱን ለሃና ተኸልቁ አስረክበው 41 የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ቢያመሩም የካፒታል አገልግሎት አቅራቢዎችን ሥራ ያስፈልጋቸዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በሥሩ ከሚገኙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ የተወሰኑ ኩባንያዎችን አክሲዮኖች በኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ በኩል ለሁለተኛ ገበያ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።



የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድ ሳይሰጣቸው የአክስዮን ማህበራት አክስዮኖችን “ለሽያጭ የማቅረብ፣ የማስተዋወቅ እና የማገበያየት” ሥራ ላይ ለተሰማሩ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ሕብረተሰቡ “ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ለማገበያየት የሚያስተዋውቁ እና የሚያገበያዩ እንዲሁም የተለያየ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና እድሎችን እናቀርባለን የሚሉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች” ጋር ከመዋዋሉ በፊት ፈቃድ የተሰጣቸው መሆናቸውን እንዲያረጋግጥ መክሯል።



አርታዒ ፀሐይ ጫኔ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች “እባካችሁ በተሰጣችሁ ፈቃዶች ላይ አትተኙባቸው”

የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች “እባካችሁ በተሰጣችሁ ፈቃዶች ላይ አትተኙባቸው”

Eshete Bekele