በዓለማችን እያደገ የሄደው የጦር መሣሪያ ምርት ፣ ንግድና ስጋቱ
Description
የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ጥናትና ምርምር ተቋም በምህጻሩSIPRIትናንት ሰኞ ባወጣው ዘገባ መሠረት የዓለማችን የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች በጎርጎሮሳዊው 2024 ዓ.ም. ከጦር መሣሪያ ሽያጭ ያገኙት ገቢ እስከአሁን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ነው። ተቋሙ በዓለማችን 100 ከፍተኛ የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች ላይ ባካሄደው ጥናት መሠረት በ2024 ከጦር መሣሪያዎች ሽያጭ እና ከወታደራዊ አገልግሎቶች ያገኙት ገቢ ወደ 679 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል። ይህም ከቀደመው ጎርጎሮሳዊው 2023 ዓ.ም. ጋር ሲነፃጸር የ5.9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በ2023 ዓ.ም. በዓለማችን ጂኦ ፖለቲካዊ ውጥረቶች ተባብሰው ነበር፤ የዩክሬን ጦርነት በዚሁ ጊዜ በመቀጠሉ የጦር መሣሪያ ግዥ ፍላጎት እንዲጨምር አድርጓል።
በ2024 ዓ.ም. ጦርነቶች እየተባባሱ በመሄዳቸው ፍላጎቱ ይበልጥ በማደጉ በዓለማችን ከጦር መሣሪያ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በእጅጉ ጨምሯል። ይህ ሊሆን የቻለውም በተለይ በዩክሬኑና በጋዛው ጦርነት የጦር መሣሪያ ግዥ ፍላጎት ይበልጥ እየጨመረ በመምጣቱ መሆኑን ተቋሙ ገልጿል። ከሽያጭ የሚገኘው ገቢ መጨመርና የግዥ ትዕዛዙም ከፍ እያለ መሄድ ኩባንያዎች የጦር መሣሪያ ምርት መስመሮችን እንዲያስፋፉ ፣ ማምረቻዎቻቸውንም እንዲያሳድጉ፣ መገልገያዎቻቸውንም እንዲያሰፉ፣ አዳዲስ ቅርንጫፎችን እንዲእንዲከፍቱ ግዥም እንዲፈጽሙ አነሳስቷቸዋል።
እናም የዩክሬንናየጋዛው ጦርነት ለአውሮጳውያኑም ሆነ ለሌሎች ተፈላጊ የጦር መሣሪያዎች ለሚያመርቱ በርካታ ሀገራት ጥሩ ንግድ ሆኗል። ሲፕሪ በጥናቱ ከተመለከታቸው 100 ኩባንያዎች 39ኙ መቀመጫቸው ዩናይትድ ስቴትስ ነው። እነዚህ 39 ኩባንያዎች ከዓለም የጦር መሣሪያ ንግድ ግማሽ ያህሉን የሚያካሂዱ ናቸው። በአውሮጳምእንዲሁ ሩስያን ሳይጨምር 26 የአውሮጳ የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች በ2024 ዓ.ም. ከጦር መሣሪያ ሽያጭ ያገኙት አጠቃላይ ገቢ ከቀደመው 2023 13 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
Sipri ባወጣው ዘገባ እንዳለው ከሁሉም የበለጠ ስኬታማዎቹ የጀርመን ኩባንያዎች ናቸው። የጀርመንየጦር መሣሪያ ሽያጭ ገቢ የጨመረው በ36 በመቶ ነው። ዘገባውን ከጻፉት መካከል ናን ትያን ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የጀርመን የጦር መሣሪያ ሽያጭ ገቢ ያደገው የጀርመን ጦር ኃይል ተጨማሪ የጦር መሣሪያ ጥያቄ በማቅረቡ ነው። ሀገሪቱ ለዩክሬን በወታደራዊ እርዳታ የሰጠቻቸውን የጦር መሣሪያዎች ለመተካትና የጦር መሣሪያ ክምችታቸውንም ለማሳደግ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ራይንሜታል እና ዲል የተባሉት ኩባንያዎች ታንኮች፣ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እና ጥይቶችን አምርተዋል። ሌሎች ኩባንያዎችም የዩክሬኑ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ምርታቸውን ይበልጥ ማሳደጋቸውን ጀርመን የተማሩትና የሚሰሩት የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። ዶክተር ፀጋዬ በተለይ በ2024 ዓ.ም. ጀርመን በዘርፉ ስኬታማ እንድትሆን ምክንያት የሆኗት አጋጣሚዎችም እንደነበሩም ወደ ኃላ መለስ ብለው አስታውሰዋል ።
የሲፕሪ ዘገባ እንደሚያሳየው ካጠናቸው ከ100 የዓለማችን ዋነኛ የጦር መሣሪያአምራቾች መካከል አምስቱ መቀመጫቸው ዩናይትድ ስቴትስያልሆነ በመከላከያ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ናቸው። ይህም እንደ ተቋሙ ዘገባ ከጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ ለውጥ ነው። ከመካከላቸው ራይንሜታል፣ ቲሰንክሩፕ፣ ሄንሶልድት እና ዲል የተባሉት አራት የጀርመን የጦር መሣሪያዎች አምራች ኩባንያዎች በ2024 ዓ.ም.፣14.9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተዋል። ራይንሜታል የተባለው ኩባንያ በ2024 ዓ.ም. ከታንኮችና ከብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ከጥይቶች ሽያጭ ያገኘው ገቢ ከ2023 ዓ.ም. በ47 በመቶ ጨምሯል።
ይህን ዓይነቱን የጦር መሣሪያ ንግድ የጦርነት ኤኮኖሚ ሲሉ የገለጹት ዶክተር ፀጋዮ በአጭር ጊዜ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች እንዳሉ ጠቁመዋል። ሆኖም ጦርነቶች ረዥም ጊዜ ሲቆዩ ደግሞ የሚያስከትሏቸው ጉዳቶች እንዳሉም ሳይጠቅሱ አላለፉም። እናም በርሳቸው አስተያየት ጦርነቶችን በንግግርና በድርድር አስወግዶ ሰላም ለማሰፈን በመጣር የጦርነት ኤኮኖሚን በሌላ መተካት ይገባል።
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ























