አሜሪካ ሰሞኑን በተገን ጠያቂዎች ላይ ያሳለፈቻቸው ውሳኔዎች አንድምታ
Description
አሜሪካ፣ዋሽንግተን ዲሲ ከነጩ ቤተ መንግሥት በቅርብ ርቀት ላይ ሁለት የብሔራዊ ዘብ አባላት ባለፈው ሣምንት በጥይት ተመትተው የአንደኛዋ ሕይወት ማለፍን ተከትሎ፣በአሜሪካ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ ላይ በርካታ ለውጥ እንደሚኖር አየተነገረ ነው። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳስታወቁት፣በጥይት ከመቱት የብሔራዊ ዘብ አባላት አንደኛዋ ስትሞት፣ ሁለተኛው ደግሞ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
ጥቃቱን ተከትሎ ከአፍጋኒስታን የመጡ የሁሉም የስደተኝነት ጥያቄዎች የታገዱ ሲሆን፣በአሜሪካ ያሉ አፍጋኒስታናዊ ዜጎች ተጠርጣሪው አነሱን እንደማይወክል በመግለጽ ውሳኔውን እየተቃወሙ ነው።
የስዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት ከ19 አገሮች ወደ አሜሪካ ለተሰደዱ ግለሰቦች የተሰጠውን የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ እንደገና እንደሚመረምር አስታውቋል። ትራምፕ ከዚህ ውሳኔ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ፣ ከሁሉም "የሦስተኛ ዓለም አገሮች" ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ "ዘላቂ ዕገዳ" ለመጣል ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።ይሁንና፣በትናንትናው ዕለት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ቆይታ ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ የሃገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ ክሪስቲ ኖም፣አሜሪካ ከጥቃት፣ከረሃብና ከሌሎች ችግሮች የሚሸሹትን የምትቀበል አገር መሆኗን ገልጸው ዕገዳው የተከማቹ የጥገኝነት ጥያቂዎች ጉዳይ፣ በትራምፕ አስተዳደር ጥብቅ መስፈርት መሰረት እስኪፈተሹ ድረስ የሚቆይ መሆኑን አስታውቀዋል ።
በእነዚህና ተያያዥ የሰሞኑ ጉዳዮች ዙሪያ፣ከአትላንታው ዘጋቢያችን ታሪኩ ኃይሉ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ሙሉ ቃለ ምልልሱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ታሪኩ ሐይሉ
ፀሀይ ጫኔ























