በኢሉባቦር የጉቲ ተራራ መደርመስ ለሕይወት ማስጋቱ
Description
በደቡብ ምዕራብኢትዮጵያአቅጣጫ፤ በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር ዞን በቾ ወረዳ ጉቲ የሚባል ተራራ በመደርመሱ የአከባቢው ነዋሪዎችን አስግቷል ። በተራራው መደርመስ እስካሁን የጠፋ የሰው ሕይወት ባኖርም፤ በንብረት ላይ ግን አስከፊ ጉዳት አስከትሏል ተብሏል ።
ደጋጋ በንቲ በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር ዞን በቾ ወረዳ ገመቺሳ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነዋሪ ናቸው፡፡ ስድስት የቤተሰብ አባላት በዚሁ ስፍራ አፍርተው የኖሩት አቶ ደጋጋ ከሰሞኑ የገጠመን ግን እንግዳ ነገር ነው ይላሉ፡፡ በሚኖሩበት በዚህ ቀበሌ ማህበር ጉቲ የሚባል ግዙፍ ተራራ ከሰሞኑ በተለይም ከስድሰት ሳምንታት ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ እየተደረመሰ ተራራውን ከበው ለሚኖሩ 90 ገደማ አባወራዎች ብርቱ ስጋት መደቀኑን ያስረዳሉ፡፡
«ጉቲ የሚባል ተራራ ተደርምሶ ከተራራው ግርጌ ያሉ ከ90 በላይ አባወራዎች ላይ ስጋት ደቅኗል፡፡ በያንዳንዱ ቤት ውስጥ ከስምንት እስከ አስር ሰው ይኖራል፡፡ በዚህ አከባቢ ያሉ እንግዲህ ያላቸው የቡና እና ሌሎችም ማሳ ከጥቅም ውጪ ሆኖባቸዋል ባጠቃላይ፡፡ የቡዙዎች መተዳደሪያ የሆነው ቡና ከ18 ሄክታር በላይ በተደረመሰው አፈር ወድሟል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአከባቢው ሚገኝ እስከ 6ኛ ክፍል የሚያስተምር ትምህርት ቤትም ከተራራው አናት አፈር ተደርምሶበት ወደ ትምህርት ቤቱ መሄድ አልተቻለም፡፡ ነገ ደግሞ ምን ይፈጠር ይሆን የሚለው አስግቶናል» ብለዋል፡፡
ጉቲ ተራራ እጅግ ግዙፍ መሆኑን የሚያስረዱት የአከባቢው ነዋሪ አርሶ አደር ከተራራው ግዝፈት የተነሳ ከተራራው ወገብ በላይ ሰውም እንደማይወጣበት ነግረውናል፡፡ መሰል አደጋን ያስከተለው የተራራው መደርመስ ስድስት ሳምንታትን ማስቆጠሩን የሚገልጹት አስተያየት ሰጪ ከትናንት በስትያ እሁድ ጥቅምት 18 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. ድጋሚ የተከሰተው የተራራው አፈር መደርመስ ስጋቱን አስከፊ አድርጎታል ብለዋልም፡፡
«ከትናት ወዲያ እንደገና መደርመሱ ተጀምሮ መሬቱን እየሸረሸረ ነው» ይላሉ አርሶ አደሩ፡፡ እስካሁን በተራራው ወደ ግርጌው መንደር መደርመስ የጠፋ የሰው ሕይወትና የወደመ ቤት አለመኖሩን በመግለጽም በማሳ ያሉ ቡና እና ሌሎች ምርቶች ግን መውደሙን አስረድተዋልም፡፡ በዚህም በተራራው ግርጌ ያሉ ነዋሪዎች በስጋት እየሸሹ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሲደረመስ አሊያም የመሬት መንሸራተት በአከባቢው ሲያጋጥም ያላዩት ነዋሪዎች የጉቲ ተራራ መደርመስ ምክንያትንም አያውቁም፡፡
አርሶ አደር ነዋሪዎቹ የተራራው መደርመስ ሰበቡን አያውቁትምም፡፡ «አንዳንዴ ጠዋት ጠዋት ጭስ ብቻ እንደመለከታለን ከተራራው አናት ላይ፡፡ ከዚያን ዳገቱ ወርዶ መሬቱን ሲያናውጥ ነው የምንመለከተው፡፡»
የአርሶ አደሮቹ ስጋት አሁንም የተራራው መደርመስ ከቀጠለ በአከባቢው ያሉ ቤቶች በአፈር የመሸፈን እድል ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ አርሶ አደሮቹ መተዳደሪያቸው የሆነው ቡና ለለቀማ በደረሰበት እንዳልነበረ ሆኖ ቀዬያቸውን ጥለው በመፈናቀል ላይ ቢሆኑም እስካሁን ያገኙት እርዳታም አለመኖሩን ያመለክታሉ፡፡
በኢሉባቦር ዞን በቾ ወረዳ ገመቺሳ ወረዳ የሚገኘው ጉቲ ተራራ ለመጀመሪያ ጊዜ መደርመስ የጀመረው በዚሁ ዓመት ከመስከረም 07 መሆኑን የገለጹልን የበቾ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ነቢዩ ታመነ፤ ክስተቱን ተከትሎ አጥኚዎች ምክኒያቱን እንዲያጠኑ ተደርጎ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የተራራው መደርመስ በዚያው የሚያቆም መስሎ ነበር ያሉት ኃላፊው ከትናንት በስቲያ እሁድ ጥቅምት 18 ቀንም በከፍተኛ ደረጃ የተራራው መደርመስ ተከስተዋልም ብለውናል፡፡
«በቀደም ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ ተራራው ሲንሸራተት በአከባቢው የሚገኙ የአርሶአደሮች የቡና እና የግጦሽ ማሳዎችን እንዳለ ነው በአፈር የሸፈነባቸው፡፡ የአከባቢው ማህበረሰቡ ጭስ ሲወጣ አይተናል ይላሉ ግን እስካሁን በጥናት የታወቀ ነገር የለም፡፡ አጥኚዎች ግን ከዞን እና መቱ ዩኒቨርሲቲ መጥተው አይተውታል፡፡ ለጊዜው የተንሸራተተው ተራራ ውስጥ ያየነው የሚፈልቅ ውሃ ነገር ነው፡፡ በአከባቢው የሰፈሩ በተለይም 21 አባወራዎች አከባቢውን ለቀው ስጋት ወደ ሌለበት አከባቢ እንዲጠጉ አወያይተናል፡፡»
የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ነቢዩ ታመነ አክለውም እስካሁን ከማሳ ውጪ በሰዎች ህይወት አሊያም መኖሪያቸው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም፡፡ አሁን ለሁለተኛ ዙር የተከሰተው የጥቅምት 18ቱ የመሬት መንሸራተትክስተት ከመጀመሪያ ዙሩ አስከፊና ከባድ ነው ብለዋልም፡፡ በአከባቢው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ምናልባትም ለመሬት መንሸራተቱ የራሱ ሚና ይኖረው ይሆናል የሚል መላ ምት መኖሩንም አክለው አብራርተዋል፡፡ የችግሩ ሁነኛ መንስኤ በመጠናት ላይ መሆኑንም ነግረውናል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ























