የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ በድሮን ጥቃት እንደፈጸመ ህወሓት ገለጸ
Description
የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት ኃይላት፣ በትግራይ እና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በትግራይ ኃይሎች ላይ “በድሮን ጥቃት ፈጽመዋል” በማለት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ወነጀል። ፓርቲው በጥቃቱ በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
ስለ ጥቃቱም ሆነ ዉንጀላዉ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሰጠ መግለጫ የለም።
የህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጻፉት ደብዳቤ ግን ጥቃቱ የተፈጸመው ለዛሬ ጥቅምት 28 ቀን 2018 አጥቢያ ከሌሊቱ 9፣ 30 ሰዓት ገደማ እንደሆነ ገልጸዋል።
ጥቃቱ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት የተፈረመው ግጭትን የማቆም ሥምምነት አብይ መርሕ የሆኑትን “ጠብመንጃዎች ዝም የማሰኘት እና ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ግልጽ እና በአሳሳቢ በሆነ መንገድ የሚጥስ” እንደሆነ ሊቀ-መንበሩ ገልጸዋል።
ህወሓት በትግራይ ኃይሎች ላይ በድሮን ጥቃት መፈጸሙን ያስታወቀው “በአፋር ክልል ወሰን ውስጥ በማግባት 6 መንደሮችን በጉልበት” ተቆጣጥሯል የሚል ክስ በቀረበበት በማግሥቱ መሆኑ ነው።
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ “የህወሓት ቡድን” በክልሉ ዞን ሁለት ውስጥ በሚገኙ “በንጹሐን የአፋር አርብቶ-አደሮች ላይ የከባድ መሳሪያ ተኩስ በመክፈት የፕሪቶሪያ ስምምነትን በግጭት አዋጅ በግልጽ አፍርሷል” በማለት ወቅሶ ነበር።
ጥቅምት 2015 የተፈረመው ሥምምነት ሦስተኛ ዓመቱን ሲደፍን ፈራሚዎቹ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት በተደጋጋሚ በመካሰስ ላይ ይገኛሉ።
በፕሪቶሪያ የተፈረመውን ግጭት የማቆም ሥምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እና በፖለቲካዊ ውይይት ሰላም ለማውረድ የማይወላውል ቁርጠኝነት እንዳለው ህወሓት አስታውቋል።
ህወሓት አክሎም፣ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት “ግጭቶችን እንዲያቆም” ፣ በፕሪቶሪያ በተፈረመው ሥምምነት መሠረት “ግዴታዎቹን እንዲያከብር እና በቅን ልቦና እንደገና እንዲወያይ” የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስፈላጊውን ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፏል። ህወሓት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በግንቦት 2017 ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙ አይዘነጋም።






















