ህወሓት ከመጭው ምርጫ በፊት ሕጋዊ ሰውነቱ መመለስ እንዳለበት ገለፀ
Description
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል አስገዶም ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት ህወሓት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው በሕገ ወጥ መንገድ ነው።ህወሓት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከፌደራል መንግስቱ ጋር አብሮ የፈረመ ፓርቲ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ «ፓርቲውን ከሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት የሰረዘው በሕገ ወጥ መንገድ ነበረ» ሲሉ አስታውሰዋል።«ውሳኔው ስምምነቱን በመጣስ የተደረገ እና በፖለቲካዊ መንገድ አላግባብ የተሰራ ነው» በማለትም ተችተዋል። እናም ከመጭው ምርጫው በፊት ሕጋዊ ሰውነቱ መመለስ እንዳለበት ተናግረዋል።
ከምርጫ በፊት ህጋዊ ሰውነት ይመለስ
«ምርጫው እየመጣ መሆኑ ይታወቃል።ግን ምርጫው ከመምጣቱ በፊት ከለአግባብ የተሰረዘውን ህጋዊነት መመለስ አለበት የሚል ነው።ምክንያቱም ከለአግባብ ነው ህጋዊነቱ የተቀማው ህጋዊ መሰረትም የለውም ህገመንግስታዊ መሰረትም የለውም።ተደራድረን በእኩል ተስማምተን በሁለታችንም በኩል እንደ ሀገር በፌደራል መንግስቱም በትግራይ መንግስትም በኩል ያለውን ነገር አብረን ተደራድረን እንድንፈታ ነው የተደራደርነው። ስለዚህ ምክንያት በሌለበት መሰረዝ ትክክል ስላልሆነ ምርጫ ከመምጣቱ በፊት ወደ ፕሪቶሪያው ስምምነት ተመልሰን ህጋዊ ሰውነቱ መመለስ አለበት»ብለዋል።
ህወሓት ከኅዳር 8 ቀን እስከ ኅዳር 13//2018 ዓ.ም. የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ማካሄዱን የገለፁት ቃል አአቀባዩ ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ እና የፕሪቶሪያውን የሰላም ውል ተግባራዊ እንዲሆን ውሉን አቋረጠ ካሉት የፌደራል መንግስት ጋር ድርድር ማድረግ ቀጣይ የፓርቲው እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።ከዚህ ባሻገር በስምምነቱ አደራዳሪ የነበሩ አካላት ስምምነቱን ዳር እንዲያደርሱትም ጥሪ አቅርበዋል።
«የፕሪቶሪያው ስምምነት ተባብረን ነው መፈፀም ያለብን ሁላችንም ማክብር ነው ያለብን ብለን እስከመጨረሻው ድረስ የበኩላችንን ጥረት እያደረግን ነው ሁላችንም።በዚህ ነው እየሄድን ያለነው ።በሌላ በኩል ደግሞ አደራዳሪዎቹ የዓለም ማህበረሰብ የአፍሪቃ ህብረትም የአውሮፓ ህብረትም የጀመሩትን የማደራደር ስራ እስከመጨረሻው እንዲያደርሱት በድርድሩ እና በፈረምነው መሰረት እንድዲዳኙን ጥያቄዎች እያቀረብን ነው ያለነው።ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበናል።ይወጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።» ሲሉ ገልፀዋል።
ሕወሓት ከኤርትራ መንግስት ጋር ይሰራልን?
በሌላ በኩል ህወሓት የሚጠበቅበትን አላደረገም በሚል በምርጫ ቦርድሕጋዊ ሰውነት ከመሻሩ ባሻገር፤ ከኤርትራ መንግስት ጋር ይሰራል በሚል በተደጋጋሚ መተቸቱን በመጥቀስ ዶቼቬለ ላቀረበላቸው ጥያቄ፤በዚህ ዓመት በኤርትራ እና በትግራይ ድንበር አካባቢ ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱን ገልፀው፤ከኤርትራ መንግስት ጋር አለ የሚባለው ግንኙነት ግን አሉባልታ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
«አሉባልታ ነው በተደጋጋሚ መግለጫ ሰጥተንበታል።በዚህ አመት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በተሻሻለበት ሁኔታ ነው ያለው።በድንበር አካባቢ ያለው ህዝብ እየተወያየ እየተጠያየቀ ነው ያለው።እሱን አንቃወምም እንደግፈዋለን።ምክንያቱም ከመነሻ አላማችንም ከህዝብ ጋር ያለን ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ነው።ከሁሉም ህዝቦች ጋር ከኤርትራም ህዝብ ይሁን ከሱዳንም ህዝብ ይሁን ከአማራም ህዝብ ይሁን ከአፋርም ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ጋር የግዝብለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር እንፈልጋለን።በዚህ ያለን አቋም ፅኑ ነው» ካሉ በኃላ ፤ «ከዚህ አልፎ ግን ከኤርትራ መንግስትም ሆነ ከሻቢያ ጋር ተገናኝተን ያደረግነው ውይይትም የለም።ያደረግነው ስምምነትም የለም» ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ህወሓት ጉባኤ መጥራትን ጨምሮ ለሕጋዊ ፓርቲነት ማማላት የሚገባዉን መስፈርቶች አላሟላም በሚል ከግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙንማስታወቁ ይታወሳል።የፌደራል ምርጫ ቦርድ ሕወሓት "ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመፃ ተግባር ላይ መሳተፉን" ማረጋገጡን በመጥቀስ በ2013 ዓ.ም. ሰርዞት የነበረ ሲሆን፤ፓርቲው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጆ ነበር። ቆይቶ ግን ፍረጃው ተነሶቶለት በድጋሚ "በልዩ ሁኔታ" መመዝገቡ ይታወሳል።
ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ























