የኢትዮ-ቴሌኮ ገቢ ሲጨምር ትርፉ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ምክንያት አሽቆልቁሏል
Description
ኢትዮ-ቴሌኮም ባለፈው ዓመት 148 ቢሊዮን ብር ገቢ ቢያገኝም የኩባንያው የተጣራ ትርፍ በ69.5 በመቶ መቀነሱን የሒሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን የኦዲት ሪፖርት አሳይቷል። በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አክሲዮኖቹን ለሽያጭ ያቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው ኩባንያ እስከ ሰኔ 2016 ባለው አንድ ዓመት ያገኘው ገቢ 91.4 ቢሊዮን ብር ገደማ ነበር።
የኩባንያው የ2017 ገቢ ከቀደመው ዓመት በ62 በመቶ ቢጨምርም በሐምሌ 2016 ተግባራዊ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ በትርፍ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮበታል።
በፋይናንስ መግለጫው መሠረት ኢትዮ-ቴሌኮም እስከ ሰኔ 2017 ባለው በጀት ዓመት ያገኘው የተጣራ ትርፍ 5.8 ቢሊዮን ብር ነው። በቀደመው በጀት ዓመት ኩባንያው 19 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ነበረው። የኩባንያው ያልተጣራ ትርፍ ከ29.8 ቢሊዮን ብር ወደ 20.4 ቢሊዮን ብር በአንድ ዓመት ብቻ ዝቅ ብሏል።
በሐምሌ 2016 ተግባራዊ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ “አትራፊ ከሚባሉ ዋና ዋና” ድርጅቶች አንዱ የሆነውን ኢትዮ-ቴሌኮም “ለከፍተኛ ወጪ” እንደዳረገ የፋይናንስ ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ይናገራሉ። የምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ ሲደረግ የበዛ ዕዳ ያለባቸው ድርጅቶች ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚያጋጥማቸው የፋይናንስ ባለሙያው አስረድተዋል።
የብር የመግዛት አቅምን በከፍተኛ መጠን ያዳከመው ለውጥ በኩባንያው የውጭ ዕዳ እና በውጭ ምንዛሪ የሚፈጸሙ የክፍያ ግዴታዎች ላይ ብርቱ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው። ኢትዮ ቴሌሌኮም ለሑዋዌ፣ ዜድቲኢ እና ኤሪክሰን የሚከፈል 29.8 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንዳለበት በሰነዱ ሰፍሯል።
ኢትዮ-ቴሌኮም ለሑዋዌ፣ ዜድቲኢ እና ኤሪክሰን የሚከፈል 29.8 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንዳለበት በሰነዱ ሰፍሯል። የኩባንያው የተጣራ ውጭ ምንዛሪ ኪሳራ የምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ ከመደረጉ በፊት በነበረው በጀት ዓመት ሦስት ቢሊዮን ብር ገደማ ብቻ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብድር በሚደጎመው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ያደረገው ሐምሌ 22 ቀን 2016 ነው።
ለውጡ ከተደረገ በኋላ የመጀመሪያው በሆነው የኢትዮ-ቴሌኮም ኦዲት ኩባንያው በአንድ ዓመት ውስጥ 42.6 ቢሊዮን ብር ገደማ የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ ገጥሞታል። በሒሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን የተዘጋጀው የፋይናንስ መግለጫ እንደሚለው የኢትዮ-ቴሌኮም “የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ1825% ጨምሯል።”
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር ከሚገኙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነውን የቴሌኮም ኩባንያ 40 እስከ 45 በመቶ ድርሻ ለግል ባለወረቶች ለመሸጥ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። ከዚያ በኋላ 100 ሚሊዮን የኢትዮ ቴሌኮም መደበኛ አክሲዮኖች ለሽያጭ ቢቀርቡም ገዥ ያገኙት 10.6 ሚሊዮን አክሲዮኖች ብቻ ናቸው።
በሽያጩ 47,377 ኢንቨስተሮች በ300 ብር በገዟቸው መደበኛ አክሲዮኖች የኩባንያው ባለድርሻ ሆነዋል። የኩባንያው አጠቃላይ ሐብት ወይም ጥሪት ባለፈው ዓመት ከነበረበት 214 ቢሊዮን ብር ወደ 331 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዳለ በፋይናንስ መግለጫው ሠፍሯል።
ኢትዮጵያ የገቢ እና የወጪ ንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማረቅ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ በገበያ ላይ ወደተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ከተሸጋገረች 15 ወራት ገደማ ተቆጥረዋል። ግብይቱ በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲወሰን ሲደረግ በባንኮች እና የትይዩ ገበያው ተመኖች ይቀራረባሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
መንግሥት በትይዩ ገበያው ተዋንያን ላይ በወሰዳቸው እርምጃዎች እና በተከታታይ በሚያካሒዳቸው ጨረታዎች ግብይቱን ለማረጋጋት ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም እስካሁን ሁለቱ ተመኖች አልተቀራረቡም። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አመልካች ዕለታዊ የምንዛሪ ተመን መሠረት በዛሬው ዕለት አንድ የአሜሪካ ዶላር በ153 ብር ከ90 ሣንቲም ገደማ ይመነዘራል። በንግድ ባንክ 163 ብር ከ50 ሣንቲም የሚመዘረው ዶላር በትይዩው ገበያ 180 ብር ገደማ ደርሷል።
የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ላይ የተደረገው ለውጥ ለከፍተኛ ወጪ የዳረገው ግን ኢትዮ ቴሌኮምን ብቻ አይደለም። “አሁንም ከፍተኛ ኪሳራ ሊዳረጉ ከሚችሉት ውስጥ ንግድ ባንክ እና ብሔራዊ ባንክን መጥቀስ ይቻላል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን ከግል ባንኮች መካከል “ለከፍተኛ ኪሳራ የተዳረጉ መኖራቸውንም አስረድተዋል።
ዶክተር አብዱልመናን “ጠንቃቃ” ሲሉ የገለጿቸው እና የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሲለወጥ “በእጃቸው ላይ የውጭ ምንዛሪ የነበረ” “በጣም ከፍተኛ ትርፍ ያተረፉ የግል ባንኮችም አሉ።”
የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት የዶላር ምንዛሪ በሐምሌ 2016 ከነበረበት 58 ብር በከፍተኛ መጠን ሲጨምር የሚደርስበት ኪሳራ ከፍተኛ እንደሚሆን ዶክተር አብዱልመናን ተናግረዋል።
ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ይፋ ያደረጉት ትንተና የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ እና የውጭ አጠቃላይ ዕዳ እስከ ሰኔ 2016 መጨረሻ ብቻ 71.379 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አሳይቷል።
ከዚህ ውስጥ 39.644 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው የሀገር ውስጥ ዕዳ ሲሆን ቀሪው 31.734 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ ነው። የዶላር የምንዛሪ ተመን ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ከነበረበት 58 ብር በከፍተኛ መጠን ሲጨምር የመንግሥትን ዕዳ በማናር ከፍተኛ ኪሳራ የሚያስከትል ነው። ዕዳውን ለመክፈል መንግሥት ግብር ለመጨመር እንደሚገደድ የገለጹት ዶክተር አብዱልመናን “ኪሳራውን ያው ዜጎች ይረከቡታል ማለት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
አርታዒ አዜብ ታደሰ























