የኢትዮጵያንና የጀርመንን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት የሚያሳይ ቅርስ ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ተበረከተ
Description
በ 1920 ዎቹ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ በነበሩት፤ በፍሪዝ ቫይስ እጅ የነበሩ 12 የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶች ባለፈዉ ሳምንት ለኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም ተበርክቷል። ለተቋሙ ከተሰጡት ውድ ቅርሶች ውስጥ ዘውዶች፣ ጋሻዎች፣ ጎራዴ፣ ዝናር፣ ስዕሎች እንዲሁም ከራስ ተፈሪ መኮንን የተበረከቱ ስጦታዎች እንደሚገኙት ተገልጿል። አዲስ አበባ የሚገኘዉ የጀርመን ኤምባሲ በበኩሉ ቅርሶቹ በ 1920ዉቹ ዘመን የጀርመን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ በነበሩት በፍሪዝ ቫይስ ቤተሰቦች እጅ የነበሩትን ቅርሶች ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋም እንዲበረከት መንገድ አመቻችቷል።
ጤና ይስጥልኝ አድማጮች እንደምን ሰነበታችሁ፤ ባለፈዉ ሳምንት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በራስ መኮንን አዳራሽ ቅርሱን የማበርከት ሥነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ሰላማዊት ካሳ፤ በአዲስ አበባ የጀርመን ኤምባሲ ጉዳይ አስፈፃሚ ዶ/ር ፈርዲናንድ ፎን ቬይሄ፤ የቅርሶቹ ባለቤት የነበሩት የቀድሞ የጀርመን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ የልጅ ልጅ ፕሮፌሰር ራሞን ዊስ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት ወዳጆች ማህበር አባላት እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል። በስጦታ መልክ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ቅርሶች የርክክብ መርሐ-ግብር ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ፤ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት፤ ቅርሶቹን ወደ ሃገር ለማስገባት ብዙ ጊዜያቶችን የወሰደ የብዙዎች ትብብር እና ስራ ዉጤት ነዉ ሲሉ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
ከ 100 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የጀርመን ልዩ መልዕክተኛ በፍሪዝ ቫይስ ቤተሰቦች እጅ የነበረዉ ቅርስ ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ለማበርከት መንገድ ያመቻቸዉ፤ በአዲስ አበባ የሚገኘዉ የጀርመን ኤንባሲ መሆኑን የኤንባሲዉ ጉዳይ አስፈፃሚ ዶ/ር ፈርዲናንድ ፎን ቬይሄ ተናግረዋል። ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የተበረከቱት እነዚህ ቅርሶች፤ በጀርመን እና በኢትዮጵያ መካከል የዘላቂ ወዳጅነት እና የመከባበር ምልክት ናቸዉ ሲሉም አወድሰዉታል። ጀርመን የኢትዮጵያን የበለፀገ የባህል ቅርስ ለመጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነዉም ተብሏል። ጋሻ፤ ሰይፎች፤ ጥሩምባዎች እና ከሁሉም በላይ ዘውዶችን ያካተተዉ ይህ የቅርስ ስብስብ፤ የዛሬ 100 ዓመት በአብዛኛዉ ከራስ ተፈሪ ቆየት ብሎ ከንጉሠ ነገሥቱ በግል የተሰጠ ስጦታ እና ወራሾች ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ለማበርከት በመወሳናቸዉ መሆኑን፤ የጀርመን ኤንባሲ ጉዳይ አስፈፃሚ ፤ ዶ/ር ፈርዲናንድ ፎን ቬይሄ ገልፀዋል።
« ነገሩ የግል ስጦታ በመሆኑ፤ ከጀርመን ኤንምባሲ ጋር ምን አገናኘው ብሎ ሰዉ ሊጠይቅ ይችላል። እዚህ ላይ ሁለት ነጥቦችን ማንሳት እንችላለን። የእቃዉ ባለቤቶች ምናልባትም ከ100 ዓመት በፊት የአያታቸዉ ስጦታ ብለዉ ሥነ- ምግባራዊ አክብሮት ይዟቸዉ፤ እያስተላለፉ በመዝለቅ ነዉ ይህን እቃ አሁን ለመመለስ የወሰኑት። ሁለተኛው ነጥብ የዚህ ቅርስ ወራሾች ወደ ኢትዮጵያ ለሟጓጓዝ ትራንስፖርትን፣ ጉምሩክን እና ሌሎች ሌሎች ጉዳዮችን ለማስተናገድ የሚያስችል ምንም ትስስር ስለሌላቸው በጣም በተግባራዊ ጉዳዮች ድጋፍ ፈልገዉ አነጋግረዉናል። በዚህ መንገድ ይህንን ስጦታ ወደ ተፈለገበት ልናደርስ ችለናል። »
የጀርመን ኤንባሲ እነዚህ ቅርሶች ለማስመለስ ብዙ ስራዎችን እንዳከናወነ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ በድጋሚ አረጋግጠዋል። በግለሰብ ተይዘዉ ከነበሩት ከእነዚህ ጥንታዊ ቅርሶች ባሻገር፤ በ 1920 ዎቹ ኢትዮጵያ ምንትመስል እንደነበር የሚያሳዩ ፎቶዎችም በስጦታ መልክ መመለሳቸዉን ወ/ሮ ሰላማዊት ተናግረዋል።
በ1920ዎቹ አዲስ አበባ በነበሩት የጀርመን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ ፍሪዝ ቫይስ እና ባለቤታቸዉ ያነስዋቸዉ ፎቶግራፎች በጎተ ተቋም ለእይታ መቅረባቸዉን የጀርመን ኤንባሲ ጉዳይ አስፈፃሚ ዶ/ር ፈርዲናንድ ፎን ቬይሄ ተናግረዋል። ከዚህ ሌላ ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የተበረከተዉ ቅርሳቅርስ በኢግዚቢሽን ለእይታ እና ለሳይንሳዊ ጥናቶች እንደ አንድ ግብዓት እንደሚሆን እምነታቸዉን ገልፀዋል።
«ባለፈው ሳምንት የተካሄደዉ ዝግጅት በእውነት ልብ የሚነካ ገጠመኝ እንደነበር ልነግርሽ እፈልጋለሁ።፣ እርግጥ ነው የቅርሱ ወራሾች ለብዙ ዓመታት ይዘዉት ከቆዩት፤ ጥበባዊ ቅርሶች ጋር ተለያይተዋል። ይሁን እና ነገሩ ጥሩ እንደሆነ ይሰማኛል። ምክንያቱም ስጦታዉ የሄደዉ ጥሩ ወደ ሆነዉ አጋር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ነዉ። እምነት ሊጥሉባቸው የሚችሉ አጋሮች እንደሆኑ በእርግጠኝነት ስላመኑበትም ነው። እነዚህ ነገሮች አንድ ክፍል ተቀምጠዉ አባሯ እንደማይለብሱ እና ለእይታ የማይቀርቡ እንደማይሆኑ አረጋግጠዋል። ቅርሱ በተቋሙ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተቋሙ አረጋግጧል። ለምሁራዊ ምርምር፤ በክብካቤ እና ጥበቃ ለሕዝብ እይታም ጭምር ይቀርባል። አሁን ከጥቂት ጊዜ በፊት በሙዚየም ውስጥ ነበርኩኝ፣ እነዚህ በስጦታ የቀረቡት ቅርሶች ለሙዚየሙ ድንቅ ተጨማሪ ግብዓት ይሆናሉ ብዬ መገመት እችላለሁ።»
በግለሰብ እጅ በስጦታ መልክ ተይዘዉ የነበሩ እና ዳግም በስጦታ መልክ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት የእነዚህ ታሪካዊ ቅርሶችን በማየት ምናልባትም በግለሰብ እጅ የተያዙ ሌሎች ቅርሶች እንዲመለሱ ምሳሌ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸዉ የጀርመን ኤንባሲ ጉዳይ አስፈፃሚ አክለዉ ገልፀዋል።
«ይህ አንድ መልስ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። የባህል ቅርሶችን በዉርስ ያገኙ ወይም በግዢ ያገኙ ግለሰቦች እንዳሉ አስባለሁ፣ ምናልባትም እንደ ቅድመ አያቶቻቸዉ በትልቅ ቤት ውስጥ መኖር ባለመቻላቸው ወይም በሌላ ምክንያት የያዙትን ታሪካዊ ቁሶች ላይፈልጉ ይችላሉ። እንደዚህ ያሉ ባህላዊ ዕቃዎችን እና ቅርሶች ግለሰቦች መጠቀም በማይፈልጉበት ጊዜ እና ለሳይንሳዊ ተቋም ወይም ሙዚየም ለመለገስ በሚፈልጉበት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለባቸዉ ይህ እርምጃ እንደምሳሌ ሊያገለግል ይችላል። እናም ብዙዎች እነዚህ ቅርሶች እንዴት እንደተያዙ የት እንደደረሱ ለማየት በቅርብ ይከታተላሉ ብዬ አምናለሁ። ቅርሶቹ ጤናማ፣ ሳይንሳዊ እና ህዝባዊ በሆነ መንገድ ከተያዙ ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ እና ንብረታቸውን እንዲሰጡ ሊያበረታታ ይችላል የሚል እምነት አለኝ።»
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸዉ፤ የቅርሶቹ መመለስ በኢትዮጵያና በጀርመን መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያሳይ፤ ጀርመናዉያኑ ቤተሰቦች ቅርሶቹን ጠብቀው በማቆየትና ወደ ሀገር በመመለስ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር ያሳዩበት ነዉ ሲሉ አክለዋል። 120 ዓመታትን ያስቆጠረዉ የ እና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባለፈዉ ዓመት መጋቢት 28 ቀን 2017 ማለት ከጎርጎረሳዉያኑ ማርች 7 ቀን፤ 2025 ጀምሮ እየታሰበ መሆኑን በአዲስ አበባ የሚገኘዉ የጀርመን ኤንባሲ ይፋ ያደረገዉ መረጃ ያመለክታል። ሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸዉን በጎርጎረሳዉያኑ መጋቢት 7 ቀን 1905 ዓ.ም ከተፈራረሙ በኋላ በመከባበር ፣በመተባበር እና በመደጋገፍ ርቀትን መጓዛቸዉ ተገልፃል። ሙሉዉን ስርጭት የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን ተጭናችሁ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ























