ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ የበላይነት ለምን አሽቆለቆለ?
Description
የዓለም አቀፍ የፍትህ ፕሮጀክት (WJP) በየዓመቱ የዓለም አቀፍ ሀገራትን የህግ የበላይነት ሁኔታ ይገመግማል። ዘንድሮ ከገመገማቸው 143 ሀገራት በ 68 በመቶ ያህሉ የህግ የበላይነት ሁኔታ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ማሽቆልቆሉን አስታውቋል ። ይህም የዓለም አቀፍ የፍትህ ፕሮጀክት ምዘናውን መሰብሰብ ከጀመረ ከጎርጎሮሲያኑ 2009 አንስቶ «ከፍተኛ ማሽቆልቆል» የታየበት ነው ተብሏል። ከአፍሪቃ 38 ሀገራት የተካተቱ ሲሆን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ከመጨረሻዎቹ አምስት ሀገራት ተርታ ተካተዋል።
ይህ የዓለም አቀፍ የፍትህ ፕሮጀክት (WJP) የዘንድሮ ምዘና ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት በትክክል ያለውን የህግ የበላይነት ሁኔታ ያሳያል? የህግ ባለሙያ ዶክተር አደም ካሴ « ይሄ ሪፖርት በየአመቱ የሚወጣ፣ የአፍሪቃ አገሮችን ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ሀገራትን የሚያካትት ነው። የተለያዩ ሀገሮች ነጥብ ቢለያይ እንኳን የአንድን ሀገር በተለያየ ዓመት ያለበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥም ያለው ሁኔታ ካለፈው ዓመት አንፃር ሲታይ፤ በብዙ ነገሮች እና ምክንያቶች ከህግ የበላይነት ጋር የሚነካኩ ጉዳዮች ስናይ ነገሮች ተሻሽለዋል ለማለት ይከብዳል።»
የዓለም አቀፍ የፍትህ ፕሮጀክት (WJP) ለዚህ ምዘና ስምንት የህግ የበላይነት መስፈርቶችን ገምግሟል። ኢትዮጵያ በምዘናው በተለያዩ መስፈርቶች ጥሩ ውጤት አላገኘችም። እነዚህ መስፈርቶች የትኞቹ እንደሆኑ እንዲያብራሩልን የህግ ባለሙያ ዶክተር አደም ካሴን ጠይቀናል። «የሚመዝነው ብዙ ነገሮችን ነው። በአጠቃላይ የመብት ጉዳይን፣ የፀጥታ ጉዳይን ይመዝናል፤ የተለያዩ በመንግሥት የሚወጡ መመሪያዎች ፤ህጎች ምን ያህል ይፈፀማሉ የሚለውን ይመዝናል። ሙስናን ይመዝናል። ፍትሐብሄር ፤የወንጀል ፍትህ ምን ያህል ይፈፀማል የሚለውን ይመዝናል። በአጠቃላይ ሰፋ አድርጎ ደግሞ በህግ የሚገዛ መንግሥት ነው ወይ? በተለይ የህግ አስፈፃሚው አካል በፓርላማ፣ በፍርድ ቤቶች፤ በማህበረሰቡ እና ሌሎች አካላት ቁጥጥር ውስጥ ነው ወይስ ውጪ ነው የሚለውን ሰፋ አድርጎ የሚያይ ነገር ነው። »
የህግ ባለሙያው ዶክተር አደም በኢትዮጵያ ለህግ የበላይነት ማሽቆልቆል በዋናነት ሁለት ነገሮችን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። « አንደኛው የፀጥታ ችግር ነው። የኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር በአጠቃላይ አልተሻሻለም። አንዳንድ ቦታዎች የበለጠ ብሷል። ከዛ ጋር ተያይዞ ደግሞ በህግ መገዛት ሳይሆን ዘፈቀደኝነት የበዛበት ይመስላል። በተለይ በህግ አስፈፃሚው አካል ውስጥ በዘፈቀደኝነት ቤት የሚሰጥ፤ በዘፈቀደኝነት ቤት የሚያፈርስ ፤ በዘፈቀደኝነት ሰው የሚታሰርበት፤ በዘፈቀደኝነት ሰው የሚፈታበት፣ በአጠቃላይ ስርዓቱ መመሪያ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በሰዎች ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አይነት የሚመስል ሂደት ነው ያለው። ከዛ አንፃር የኢትዮጵያ ሁኔታ ወደታች መውረዱ የሚገርም አይደለም። »
በዚህ የዘንድሮ የዓለም አቀፍ የፍትህ ፕሮጀክት (WJP) መረጃ ላይ የ ኢትዮጵያ የፍትሕ ሚኒስቴር ምላሽን ለማካተት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ግን ይህ የዓለም አቀፍ የፍትህ ፕሮጀክት ምዘና ይፋ ከመሆኑ ቀናት በፊት ፓርላማ ቀርበው ከፍትህ ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄ የፍትህ ሰርዓቱን ለማሻሻል ፤ በአቃቢ ህግ፣ በፖሊስ እና ፍርድ ቤቶች «ጥሩ» ሲሉ የገለፁት ስራ መጀመሩን ገልጸው ነበር።
«የፍትህ ሥርዓቱ በአንድ በኩል ነፃነት ሊጠብቅ በሌላ በኩል ደግም ስርዓት እንዲያሻሽል ነው የምንፈልገው። ገብተን ይህን ፍረድ ያን አፍረድ ማለት አንፈልግም። ነፃ ተቋም ነው። ተጠሪነቱ ደግሞ ለኛ ሳይሆን ለእናንተ ነው። ይኼ ተቋም ነፃ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ስርዓት ማሻሻል ላይ ደግሞ ማገዝ እንደ መንግሥትም እንደ ምክር ቤትም ያስፈልጋም። ለዚህም በስነ ምግባር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የኢንስፔክሽን ስራ ጀምረዋል። ያንን እንደግፋለን። አቅም ማነስ እንዳለ አውቀው በኦቶሜሽን ቨርቹዋል ስርዓት እየዘረጉ ይገኛሉ። ሥልጠና እየሰጡ ይገኛሉ።»
በዓለም አቀፍ የፍትህ ፕሮጀክት (WJP) የህግ የበላይነትን በማስከበር በቀደምትነት ደረጃ የተቀመጡት ሀገራት እንደቅደም ተከተላቸው፤ ዴንማርክ ፣ ኖርዌይ፣ ፊንላንድ ፣ ስዊድን ፣ እና ኒውዚላንድ ሲሆኑ ከመጨረሻ ደግሞ ቬንዙዌላ 143ኛ፤ አፍጋኒስታን ፤ ካምቦዲያ ፤ ሄይቲ እና ኒካራጉዋይ ይገኛሉ።























