አንድ - ለ - አንድ ፤ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች ያሬድ ኃይለማርያም ጋር
Description
አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ከ25 ዓመት በላይ በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ሰርተዋል።አቶ ያሬድ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ) የሄዱት የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት እና በግዳጅ መለመኛ የሆኑ ህፃትን ጉዳይ ይዘው አቤቱታ ለማሰማት ቢሆንም፤ ቆይተው ግን በዚያው ድርጅት ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጋር ለሰባት ዓመታት ሰርተዋል።
አቶ ያሬድ ምርጫ 97ን ተከትሎ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለእስር ከዚያም ለስደት ተዳርገዋል። በ2010 ዓ/ም አጋማሽ በኢትዮጵያ የመጣውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ ከሚኖሩበት ቤልጄም፤ ብራስልስ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተማጋቾች ማዕከልን በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል። በቅርቡ ግን ከሚመሩት ተቋም በጫና መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንለአውሮፓ ህብረት እና ለተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በማጋለጥ ለበርካታ አመታት የሰሩት አቶ ያሬድ፤ ከሚመሩት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ቢለቁም በግላቸው ለሰብዓዊ መብት መታገላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ማስታወሻ በሚል በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ባሳተሙት መፅሃፋቸው ከ25 ዓመታት በላይ ለቆሙለት የሰብዓዊ መብት መከበር ያደረጉትን ትግል እና የገጠሟቸውን ፈተናዎች በዝርዝር ከትበዋል። አቶ ያሬድ ለሰብዓዊ መብት መከበር ላደረጉት ትግል ፤የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ በኢትዮጵያ ለመብት ተሟጓች የሚሰጠውን "ሹማን" የተባለውን ሽልማት በጎርጎሪያኑ 2024 ዓ/ም ሰጥቷቸዋል።እኝህ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የዛሬው የአንድ ለአንድ ዝግጅት እንግዳ ናቸው።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ልደት አበበ























