DiscoverDW | Amharic - Newsየጀርመን ገበሬዎችን ያሰጋው የአእዋፍ ጉንፋን ወረርሽኝ
የጀርመን ገበሬዎችን ያሰጋው የአእዋፍ ጉንፋን ወረርሽኝ

የጀርመን ገበሬዎችን ያሰጋው የአእዋፍ ጉንፋን ወረርሽኝ

Update: 2025-11-04
Share

Description

የአእዋፍ ጉንፋን ወረርሽኝ ጀርመን በርሊን አቅራቢያ በሚገኙ የዶሮ እርባታ ስፍራዎች መዳረሱ በዘርፉ የተሰማሩ ገበሬዎችን ስጋት ላይ ጥሏል። በሳይንሳዊ አጠራሩ H1 N1 የተሰኘው የአእዋፍ ጉንፋን በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ በወረርሽኝነት ተቀስቅሷል። የሰሜኑን ንፍቀ ክበብ የክረምት ወር ቅዝቃዜ መጠናከሩን ተከትሎም ወረርሽኙ ተባብሶ መቀጠሉ እንደማይቀር እየተነገረ ነው። ክስተቱ በዶሮና አእዋፍ እርባታ ሥራ የተሰማሩ ገበሬዎችን ስጋት ላይ ጥሏል።



መረጃዎች እንደሚያሳዩበት በተለይ በአሁኑ ወቅት እየተዛመተ የሚገኘው H5 N1 በሚል የተገለጸው የአእዋፍ ጉንፋን ዝርያ በከፍተኛ ፍጥነት የሚተላለፍ መሆኑ ችግሩን አባብሶታል። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉትም ይህ ተሀዋሲ የአእዋፍ ኢንፍሉውዌንዛ ሊያስከትል ይችላል። ይህ ዓይነቱ ተሀዋሲ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተውና የታወቀው በጎርጎሪዮሳዊው 1990ዎቹ አካማሽ አካባቢ ነበር። ከዚያ ወዲህ በድጋሚ በዚሁ የዘመን ቀመር 2020ላይ ከተከሰተ በኋላ በየዓመቱ መደጋገሙን ባለሙያዎች ያመለክታሉ። እናም በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክፍለ ዓለም አንታርክቲካን ጨምሮ ይህ ተሀዋሲ እንደሚገኝ ነው የጤና ባለሥልጣናት፤ በሽታዎች ላይ የሚመራመሩ እና የዱር እንስሳትን በቅርበት የሚያጠኑ ባለሙያዎች የሚናገሩት።



ጀርመን ውስጥ በሽታው በብዛት እንዳይዛመት በሚል ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ዶሮዎች፤ ዳክዬዎች፤ ዝየዎች እና ተርኪዎች እንዲሁም በሺህዎች የሚቆጠሩ ከብቶች ተገድለው እንዲወገዱ ተገድጓል።



ዴንማርክ እና ኔዘርላንድስም እንዲሁ በበሽታው የተያዙ በሺህዎች የሚገመቱ የአእዋፍ ዝርያዎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል። ስጋት የገባቸው ቤልጂየም እና ፈረንሳይ ደግሞ የዶሮ እና እንስሳ እርባታዎቻቸውን ከወረርሽኙ ለመከላከል እየታገሉ ነው።



ለምድነው አሁኑ የአእዋፍ ጉንፋን የተስፋፋው?



በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ አሁን የመጸው ወቅት ነው፤ ወደ ክረምቱ የመሸጋገሪያ ወቅት እንደመሆኑም አብዛኞቹ የአእዋፍ ዘሮች በየዓመቱ ሞቃት የአየር ሁኔታ ወዳለበት ወደ ደቡባዊ ንፍቀክበብ ይሰደዳሉ። በረዥሙ ጉዟቸው መሀልም በሚያርፉበት ከአካባቢው የዱር እና የእርባታ ስፍራ አእዋፍ ጋር ይገናኛሉ። በዚህ አጋጣሚ ታዲያ የታመሙ ካሉ ይሞታሉ።



የአእዋፉ የዘንድሮ ጉዞ ከወትሮው ቀደም ያለ እንደሆነ ነው የተገለጸው። አጋጣሚውም የH5 N1 ተሀዋሲን መዛመት አስከተለ። በስፔኑ ካስቴላ ላ ማንቻ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ተመራማሪ የሆኑት ዑርዙላ ሆይፍለ እንደሚሉት፤ «ከዚህ በፊት የአእዋፍ ጉንፋን ይቀሰቀሳል ተብሎ የሚገመተው በክረምት ወቅት ነበር። አሁን ግን ቢያንስ በዱር አእዋፍ ላይ ቢሆንም እንኳን ዓመቱን ሙሉ እያጋጣመ ነው።»



የዱር እና የቤት እንስሳት የሚቀራረቡበት አጋጣሚ በቅርቡ ጀርመን ውስጥ እንደታየ ነው መረጃዎች የሚመለክቱት። በበሽታው የተያዙ የውኃ አካባቢ አእዋፍ ወደ ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ በጉዞ ላይ ሳሉ ከበርሊን ከተማ አቅራቢያ፣ በምሥራቅ ጀርመን አካባቢ እንዲሁም ሽቱትጋር ከተማ ሞተው ተገኝተዋል። ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ በመስጋት ታዲያ በዶሮ እርባታ የተሰማሩ የጀርመን ገበሬዎች ግማሽ ሚሊየን የሚጠጉ የአእዋፍ ዝርያዎችን እያረዱ ለማስወገድ ተገደዋል።





ማልተ ፎይግትስ በዋና ከተማ በርሊን አካባቢ በዶሮ እርባታ የተሰማሩ ገበሬ ናቸው።



«በሚያሳዝን ሁኔታ ማለዳ ስንነሳ ካሉን የውኃ ዳር አካባቢ ወፎች የተወሰኑት ሞተው አገኘን። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሞታቸው ቀጠለ። እዚህ አምስት መንጋ ነበሩን፤ እያንዳንዱ መንጋ አንድ ሺህ ዝየዎች አሏቸው፤ ወረርሽኙ ታዲያ በጣም ኃይለኛ ነበር በዚህም ምክንያት የውኃ አካባቢ ወፎቹ ሞተው ተገኙ።»



በብራንደንቡርግ ብቻ ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ በተወሰደው እርምጃ 150 ሺህ አእዋፍ ተገድለዋል። በመላው ጀርመን ደረጃ ደግሞ ከግማሽ ሚሊየን ይበልጣል። በዚህ ምክንያት በእርባታቸው ላይ ተጽዕኖ የደረሰባቸው ገበሬዎች በአንድ ዶሮ ከ50 እስከ 110 ዩሮ ካሳ ተከፍሏቸዋል። ድጋፉ የተገኘው ለእንስሳት ህክምና ከሚዋጣ ገንዘብ ነው። በጀርመን የእንስሳት ጤና ላይ ለሚደረገው ምርምር ኃላፊነት ያለው ፍሬድሪሽ ሎይፈር ተቋም እንደሚለው የአእዋፍ ወረርሽኝ በተለይ ክረምቱ እየተጠናከረ ሲሄድ ሊባባስ ይችላል።



ጀርመን ውስጥ ወረርሽኙ የተስፋፋባቸው አካባቢዎች



በአእዋፍ ጉንፋን ወርሽኙ በጣም የተጎዱት ሰሜንና ምሥራቅ ሎወር ዛክሰን፤ ቱሪንገን ፤ ብራንደንቡርግ፤ እና ሜክለንቡርግ ፎርፖመረን ግዛቶች ናቸው። ከዚህም ሌላ ባየርን እና ኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራል ግዛቶች ውስጥም በሽታው ተገኝቷል።



እግረ ረዣዥሞቹ የውኃ አካባቢ አእዋፍ ሞተው ክፉኛ ከተጎዱት መካከል ናቸው። በዚህ ምክንያት ሰሜናዊ ብራንደንቡርግ እና ዋና ከተማ በርሊን ላይ የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ሰጪዎች በሜዳዎች ላይ የወደቁ በሺህዎች የሚቆጠሩ የሞቱ እንስሳት ለማስወገድ ተረባርበዋል።



ወረርሽኙ በዶሮ ምርትና አቅርቦት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ



የአእዋፍ ጉንፋን በሚያስከትለው ሞት ምክንያት ለገበያ የሚቀርበው ከዘርፉ የሚገኘው ምርት ተጽዕኖ ሊያጋጥመው እንደሚችል የሚናገሩ አሉ። በዘርፉ የተሰማሩ ገበሬዎች ለገበያ የሚያቀርቡት እንቁላልም ሆነ ሥጋ ሊቀንስ እንደሚችል ይገመታል። እንደ ማልተ ፎይግስ ያሉት ዶሮ አርቢ ገበሬዎች ሙሉ በሙሉ በዚህ ዘርፍ ላይ ጥገኛ አለመሆናቸው ከከባድ ኪሳራ እንደታደጋቸው ነው የገለጹት። ምንም እንኳን ጀርመን ውስጥ በተጠቀሱት አካባቢዎች ወረርሽኙ ተጽዕኖው ቀላይ ባይባልም ለጊዜው ገበያው ላይ ያን ኃይል መዘዝ አላስከተለም ይላሉ የጀርመን የዶሮ አርቢዎች ማሕበርት ተጠሪ ካተሪና ሽታንድከ። አሁን ላይ ሆኖ ግን የወደፊቱን ተጽዕኖ ለመገመት አዳጋች መሆኑን ግን አልሸሸጉም።



«ውሎ አድሮ የሚሆነውን ለመናገር በጣም ገና ነው፤ የረዥም ጊዜ ተጽዕኖውን ለመተንበይ አስቸጋሪ ነው። ሁሉም ነገር የሚወሰነው በወረርሽኙ ሂደት ይሆናል። ለገና ወቅት ከወዲሁ በደንብ ተዘጋጅተናል ብዬ አስባለሁ፤ ስለዚህ እጥረት ይከሰታል ብለን አንገምትም። ለገና በዓል የሚቀርበው አብዛኛው የተጠበሰ ዳክዬና ዝዬ ከውጭ እንደሚገባም መገንዘቡ ጠቃሚ ጉዳይ ነው።»



በሽታው የመጣው በዱር በሚሰማሩት የአእዋፍ ዝርያዎች ምክንያት መሆኑን የተረዱት የዘርፉ ባለሙያዎች ባስተላለፉት መረጃ መሠረት ዶሮዎች ከቤታቸው ውጪ እንዳይወጡ እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። አሁንም ግን መርማሪዎች ወረርሽኙ የት እንደጀመረ በመፈለግ ላይ ናቸው። የተፈጥሮ ይዞታ እንዲጠበቅ የሚሟገተው ሪንሉህ የተሰኘው ማዕከል ባልደረባ ኖርበት ሽኒቫይስ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ምርመራ መደረግ እንዳለበት ያሳስባሉ።



«ይህ ከቦታቸው የሚሰደዱ የዱር አእዋፍ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የውኃ አካባቢ አእዋፍ ላይ ወረርሽኙ ሲከሰት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።። የእነሱን የመመገቢያ እና ማረፊያ አካባቢዎች የሚጋሩ ሌሎች የሚሰደዱ የወፍ ዘሮችም አሉ፤ እግረ ረዣዝሞቹ የውኃ አካባቢ አእዋፍ በሚተኙበት ከሚያድሩት አንድም የሞተ ዝዬ አላገኘንም።»



እንዲያም ሆኖ የአእዋፍ ጉንፋን በሽታው የአውሮጳ ሃገራትን ማዳረሱን ቀጥሏል። ክረምቱ እየገባ እንደመሆኑ ስደታቸው ገና መጀመሩ ነውና ሊቀጥል እንደሚችል ስጋት አለ። ሁኔታውን የጀርመን ገበሬዎች በፍርሃት እየተከታተሉት ነው።





H5N1 ወደ ሰዎች ይተላለፋል?



የአእዋፍ ጉንፋን ሰዎችን ያሰጋ ይሆን? መረጃዎች እንደሚሉት H5 N 1 የተሰኘው ተሀዋሲው ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድሉ ዝቅተኛ ቢሆንም ተአማኒ ስጋት ግን አለ። ሰዎች በተሀዋሲው ከተያዙ አእዋፍ ጋር በቅርበት በተደጋጋሚ የሚገናኙ ከሆነ ብቻ ስጋቱ ከፍ ይላል። የጀርመኑ ሮበርት ኮኽ ተቋም ግን እስካሁን በዚህ ተሀዋሲ የተያዘ ሰው ስለመኖሩ መረጃ እንደሌለው አስታውቋል።



በመሠረቱ የኢንፍሉዌንዛ ተሀዋሲ የአእዋፍ ጉንፋኑን ጨምሮ ከያዙት ፍጥረት አልፈው ሌላውም ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው የማይቀር ነው። በየጊዜው በእንስሳትም ሆነ በሰዎች ላይ እንዲሁም በአእዋፍ ዘሮች ውስጥ በተደጋጋሚ በመከሰት ዑደቱን እየደጋገሙ ይኖራሉ። H5N1 ተሀዋሲ ከአንድ ወፍ ወደ ሌላው በቀላሉ የሚተላለፍ ዓይነት መሆኑ ነው የተነገረው። ይህ የመተላለፍ ፍጥነቱ ደግሞ ከዱር አእዋፍ ቤት ውስጥ በእርባታ ስፍራ ወደሚጠበቁ ዶሮዎችም ሆነ ሌሎች የአእዋፍ ዘሮች በቀላሉ እንዲተላለፍ ዕድል ይከፍትለታል። ለዚህ ነው ዶሮዎችን የሚያረቡ ገበሬዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲሁም ለእጃቸው ጓንትን የመሳሰለ መከላከያ እንዲለብሱ የተመከረው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ባለፉት ቅርብ ዓመታት በተለይ በእንዲህ ያለ የዶሮዎች የእርባታ ስፍራ የሚሠሩ ወገኖች ለH5N1 ተሀዋሲ ተጋልጠዋል። ሆኖም ለሕልፈት ሕይወት አላደረሳቸውም ተብሏል።



ሆኖም እንስሳት ማለትም ላሞችም ሆኑ አሳማዎች ግን ለዚህ የተጋለጡ መሆናቸው ተገልጿል። በዚህም ምክንያት ሰዎች ያልበሰ ምግብ ወተትን ጨምሮ እሳት ያልነካው ነገር እንዳይመገቡ ነው የተመከረው። ጉዳዩ ያሳሰበው የጀርመን ምክር ቤት ማለትም ቡንደስታኽ በጉዳዩ ላይ እየተነጋገረ ሲሆን፤ በምክር ቤቱ የአረንጓዴ ፓርቲ ቃል አቀባይ አሁን የተከሰተው የአእዋፍ ጉንፋን ወረርሽኝ፤ ለችግር የተጋለጠ ዘርፍ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።



በአሁኑ ወቅት የአእዋፍ ብቻ ሳይሆን በሰዎችም ላይ እንዲሁ የጉንፋን መዛመት እየታየ ነው። ለግል ጥንቃቄ ከማድረግ ጎን ለጎን ያልበሰለ የእንስሳት ተዋጽኦ ከመመገብ መቆጠብ እየተመከረ ነው።



ሸዋዬ ለገሠ



እሸቴ በቀለ

Comments 
loading
In Channel
loading
00:00
00:00
1.0x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የጀርመን ገበሬዎችን ያሰጋው የአእዋፍ ጉንፋን ወረርሽኝ

የጀርመን ገበሬዎችን ያሰጋው የአእዋፍ ጉንፋን ወረርሽኝ

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse