የገዳ-ሥርዓት ለኦሮሞ ነፃነት ፓርቲ (ገዳ ቢሊሱማ) አቤቱታ
Description
የገዳ-ሥርዓት ለኦሮሞ ነጸናት ፓርቲ ገዳ ቢሊሱማ የፖለቲካ ፓርቲነት ፍቃዱ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ መሰረዙን አመልክቶ፤ በፍረድ ቤት በመፋለም ሁለት ጊዜ ሕጋዊነቱን ማስመለሱን ገልጿል። ፍቃዱ በሕገ ወጥ መንገድ ሁለት ጊዜ ተሰርዞብኛል ያለው ደግሞ የቀድሞ ባለው የምርጫ ቦርድ አመራሮች መሆኑን አስታውቋል፡፡ አስተያየታቸውን በዚሁ ላይ የሰጡን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አባቦኩ ሮቤሌ ታደሰ ፓርቲው በፍ/ቤት ተከራክሮ ተሰርዞበት የነበረውን ፍቃዱን ቢያስመልስም የሕግ ጥበቃ ስለሌለው እና ከመንግስት የሚሰጠውን የፋይናንስ ድጋፍ ስለተከለከለ ግን ፓርቲው በነጻነት መንቀሳቀስ አዳጋች ሆኖበታል ነው ያሉት።
“ፓርቲያችን በስድስተኛው ዙር ምርጫ ያልተሳተፈው በሕጋዊነት ክርክር ላይ በመሆኑ ነው” የሚለውት አቶ ሮባሌ፤ አሁን ፓርቲው የህጋዊነት ፍቃዱን ባስመለሰበት ወቅት ዘንድሮ በ2018 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ሰባተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እቅድ ቢኖራቸውም ፓርቲው መክፈል የማይችለውን የጽህፈት ቤት ኪራይ ክፍያ በመጠየቁ በፓርቲነት ህልውናው ለመቀጠል አስቸጋሪ እንደሆነበትም አስረድተዋል፡፡
የተቀዛቀዘው የምርጫ እንቅስቃሴ
ኢትዮጵያ በዚህ በያዝነው 2018 ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ የማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኗን እና ይህም በበጀት ዓመቱ የመንግስት ዋናው እቅድ ውስጥ አንዱ ሆኖ የተካተተ ስለመሆኑ የኢፌዴሪ ርዕሰብሔር ታዬ አጽቀስላሴ በሁለቱ ምክርቤቶች የበጀት ዓመቱ የመክፈቻ መርሃግብር ላይ ባቀረቡት አበይት የመንግስት እቅዶች ላይ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም በዓመቱ ነጻና ፍትህአዊ ምርጫ ለማካሄድ መታቀዱን አንስተው፤ በዚህም ህዝቡና አጋር አካላት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡
የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጸናት ፓርቲ ገዳ ቢሊሱማ ፕሬዝዳንት አቶ ሮቤሌ ታደሰ ግን፤ “አገር አቀፍ ምርጫ ስኖር ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚጠበቅ ነገር ነበር፤ ግን አሁን ያን የሚመስል ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም” በማለት መንግስት ምርጫ ለማድረግ የሚወስንም ከሆነ በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን ግጭትና አስቻይ ሆኑታውን በማገናዘብ መሆኑ እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡
ለፓርቲዎች የሚመደብ ፋይናንስ
ከ 2017 ዓ.ም ሚያዚያ ወር የሚጀምር የ41,000 የቢሮ ኪራይ ውዝፍ ክፍያ ተጠይቀናል የሚለው ፓርቲው፤ አሁን ላይ ቤቱን ልቀቁ የሚል ማስጠንቀቂያ መጻፉ በፓርቲው እንቅስቃሴ ላይ እንደሚጣል ገድብ የሚታይ ነው ሲል አንስቷልም፡፡ የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ የሚታገለው “ሁሉም ፓርቲዎች በአገኙት የሕዝብ ድምጽ የመንግስት መቀመጫ ያገኛሉ” የሚለው የተመጣጣኝ ምርጫ ሥርዓት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ስራ ላይ እንደሚውል በማመን ነው በማለትም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ የእርስ በርስ ጦርነት መንስኤ የሆኑ ችግሮች ግን አስቀድሞ እንዲፈቱት ጠይቋል፡፡
“በ2017 ዓ.ም. ለሌሎች ፓርቲው የተመደበው የበጀት ክፍፍል ተከልክለናል” ያሉት አቶ ሮበሌ ዘንድሮም ምርጫው እንዲካሄድ ከተፈለገ የእርሰበርስ ግጭትና ህዝቡ ላይ ያው ችግር እንዲቆም ሲል ጠይቋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ፓርቲያቸው ከ2017 ሰኔ ወር ወዲህ ሕጋዊ ሰውነቱ ተመልሶለት በምርጫ ቦርድ እስካሁን ቀጥሉ የሚል ምላሽ አለመሰጠቱም አሳሳቢ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
ገዳ ነጻነት ፓርቲ ባቀረበው የሕጋዊነት ጥያቄ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡ ፓርቲው ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡት አማራጭ ሀሳብ ተቀባይነት ካላገኘና የተመጣጣኝ የምርጫ ሕግ በሕዝብ ተወካዮች ቀርቦ ካልጸደቀ ከ7ኛውም የምርጫ ውድድር ውጭ ለመሆን የሚገደድ መሆኑን አሳውቋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ