ተፈጥሮን ተከባካቢዋ የእጽዋት ወዳጅ በኮምቦልቻ
Description
እጽዋትን የመንከባከብ ፍቅር
ከልጅነቷ የነበራት የእጽዋት ፍቅር ዛሬ የግሏን መናፈሻ ተወልዳ ላደገችባት ከተማ ኮምቦልቻ እንድታበረክት አብቅቷታል። ለእርሷ እጽዋት ከፈጣሪ ጋር የሚያገናኙ ገጸ በረከቶች ናቸው። ወ/ሮ ሠናይት ጋሻው በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኘው የሠናይት ጋርደን ሴንተር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናት። እራሷን የሴት ገበሬ በማለት አስተዋወቀችን፤ ያለችውን ታሟላለች፤ ችግኝ በማፍላትና ለኅብረተሰቡ በማዳረስ የጀመረችው ሥራ ዛሬ የከተማዋ ነዋሪዎች ንጹሕ አየር እየተነፈሱ የሚዝናኑበትን፤ ለሠርግና ለተለያዩ ማኅበራዊ ዝግጅቶቻቸው የሚመርጡትን መናፈሻ አስገኝቷል።
ወ/ሮ ሠናይት ተወልዳ ባደገችባት ኮምቦልቻ ከተማ ሠናይት ጋርደን ሴንተርን አደራጅታ ለኅብረተሰቡ መናፈሻና መዝናኛነት አቅርባለች። አትክልት መትከልና መከባከብ ግን የጀመረችው በቤታቸው ጓሮ ነው። የእግሏ ተሞክሮም ለኅብረተሰቡ ችግኝ እያፈሉ ወደማቅረብ እንዳሸጋገራት ትናገራለች።
የመናፈሻ ስፍራ
በኮምቦልቻ ከተማ ከቦርከና ወንዝ ዳርቻ በከተማው አስተዳደር በተፈቀደላት መሬት ላይ ችግኝ ማፍላት የጀመረችው የእጽዋቶች ወዳጅ ኅብረተሰቡ ዛፎቹ አድገው ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ በተግባር እንዲያይ በሚል የራሷን የአትክልት ስፍራ ማሳመር ጀመረች። ውሎ አድሮም ወደ መናፈሻ ስፍራነት አደገ።
ወ/ሮ ሠናይት ለእጽዋት ካላት ፍቅር የተነሳ እራሷ ችግኞችን በሚያፈሉበትና በሚከባከቡባቸው ቦታዎች ከሠራተኞቿ ጋ አብራ እንደምትሠራ ነው ያጫወተችን። የእሷ በዚህ ስፍራ ጊዜዋን ማሳለፍም የተሻለ ውጤት እንዲታይ ለማድረጉ አስተዋጽኦ እንዳለው ታምናለች። የተለያዩ ተክሎችን ችግኝ እያፈሉ ለኅብረተሰቡ በማቅረብ የተጀመረው ጥረት ዛሬ ቆሻሻ መጣያ የነበረን ስፍራ ወደ መናፈሻነት እስከመለወጥ ደርሷል። ለመሆኑ ምን ያህል ጊዜ ወሰደ? ያልናት ወ/ሮ ሠናይት፤ በቤታቸው ጓሮ ይህንኑ ሥራ ለ15 ዓመታት ስትሠራ መቆየቷን፤ ጥረቷን ወደ መናፈሻ ስፍራ ለማሳደግ የረዳትን ቦታ ካገኘች በኋላ ደግሞ 12 ዓመታት ገደማ ማለፋቸውን ነው የገለጸችልን።
የችግኝ አቅርቦት
ወ/ሮ ሠናይት ላለፉት 25 ዓመታት ገደማ ለኅብረተሰቡ በየዓመቱ በክረምት ወቅት ያለማሰለስ የተለያዩ አትክልቶች ችግኞችን በማቅረብ ላይ ናት። የተለያዩ ወገኖች የሚወስዷቸው እነዚህ ችግኞች ከአካባቢያቸው አልፈው ወደ ሌሎች አጎራባች ከተሞችና ወረዳዎችም ይሰራጫሉ። በዚህም ከዓመታት በፊት ተራቁቶ ይታይ የነበረው የሚኖሩት አካባቢ አሁን አረንጓዴ መልበሱን ነው የገለጸችልን።
ቦርከና ወንዝ አለና የውኃ ችግር አይነሳም። አንድ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው «ሠናይት ጋርደን ሴንተር» በውስጡ ጽድና ቀርከሃን ጨምሮ ሌሎች የውበትና ጌጥ ተክሎችን ከሳር ጋር ደምሮ አካባቢውን አስውቧል። ይህ ደግሞ በተፈጥሮ ጸጋ ከውስጥ ባለ ፍቅር ላይ ተመስርቶ በጓሮ አትክልት የተጀመረ ጥረት ውጤት ነው። ወ/ሮ ሠናይት ከኬንያዊቱ የተፈጥሮ አካባቢ ተቆርቋሪ ዋንጋሪ ማታይ ጋር ለእጽዋት ያላት ፍቅር ያመሳስላታል። ዋንጋሪ ማታይ ኬንያውያን ሴቶች በሀገራቸው የደን መራቆትን ቀልብሰው ከድህነት እንዲላቀቁ የዛፍ ችግኞችን እንዲተክሉ በማበረታታት ትታወሳለች። ወ/ሮ ሠናይትም ለአካባቢ ተፈጥሮ ያበረከተችው አስተዋጽኦ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ የ10ኛ ክፍል አማርኛ መማሪያ መጽሐፍ »ሴቶች እና ልማት» በሚል ንዑስ ርዕስ በአርአያነት ተጠቅሷል። እሷ ግን ሥራዋ ትኩረት ያገኛል ብላ አልገመተችም።
የመናፈሻ ስፍራው መዝናኛ እንደመሆኑ በዚህ ስፍራ የሚበላ የሚጠጣውን ማቅረብም የገቢ ምንጭ ነው። ለዚያ ደግሞ ከብቶችን በማርባት ወተት፤ እንቁላል ለመሳሰሉት ግብአቶች እራሳቸውን መቻላቸውንም ወ/ሮ ሠናይት ገልጻልናለች። በአትክልት ፍቅር የተጀመረው ሥራ ዛሬ ጥቂት ለማይባሉ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም እንዲሁ። እሷ እንደምትለው የአትክልት ስፍራው ከመዝናኛነት ባለፈ ሌሎችም ያንን ተመልክተው በየአካባቢያቸው ተመሳሳይ አረንጓዴ መስኮችን እንዲያዘጋጁ ትምህርት መቅሰሚያ ነው።
FAO ለደን ልማት ፕሮጀክቶች እውቅና መስጠቱ
ባሳለፍነው ሳምንት የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት FAO የደን ልማት ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ጨምሮ በመላው ዓለም የተራቆቱ አካባቢዎችን በዛፎች ለመሸፈን ለሚከናወኑ 24 ፕሮጀክቶች እውቅና ሰጥቷል። በግለሰቦች ደረጃ የሚከናወኑ እንዲህ ያሉት ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ሥራዎች በየሀገሩ የተጎዳው የአካባቢ ተፈጥሮ እንዲያገግምና እንዲሻሻል የሚኖራቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። ጀግኒት መባል የሚገባት የአካባቢ ተፈጥሮ ተከባካቢ ወ/ሮ ሠናይት ጋሻውን ለዚህ ጥረትና አስተዋጽኦዋ ትመሰገናለች።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ