DiscoverDW | Amharic - Newsለአገራቸውና ለማኅበረሰባቸው በጎ የሠሩ ግለሰቦች ሽልማት
ለአገራቸውና ለማኅበረሰባቸው በጎ የሠሩ ግለሰቦች ሽልማት

ለአገራቸውና ለማኅበረሰባቸው በጎ የሠሩ ግለሰቦች ሽልማት

Update: 2025-12-17
Share

Description

ለአገራቸው እና ማኅበረሰባቸው በጎ ያደረጉ ናቸው የተባሉ ግለሰቦች፣ ዩናይትድ ስቴትስ አትላንታ ጆርጂያ ውስጥ ዕውቅና እና ሽልማት ተሰጣቸው። አትላንታ ውስጥ የሚገኘው ምሳሌ የግብረ ሰናይ ድርጅት፣ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ባካሄደው የምስጋና እና ሽልማት ሥነ ሥርዓት፣11 ግለሰቦችን ሸልሟል።



ምሳሌ የግብረ ሰናይ ድርጅት፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት ላቅ ያለ የበጎ ሥራ ሠርተው፣ያለፉትን እና በመሥራት ላይ ያሉትን ግለሰቦች ማመስገን እና ዕውቅና መስጠትን ዋና ግቡ አድርጎ ይንቀሳቀሳል። በሁለተኛ ደረጃ እና በኮሌጅ ትምህርታቸው ብልጫ ያመጡ ተማሪዎችንም ፣ያበታታል፤ይሸልማል ። ድርጅቱ፣ሦስተኛ መርሐ ግብሩን፣እንደ ጎርጎሮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር፣እሁድ ታኅሣሥ 14 ቀን 2025 አካሄዷል።



የድርጅቱ እንቅስቃሴ



እንቅስቃሴያቸውን አስመልክቶ ዶቼ ቨለ ያነጋገራቸው የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ዳግም መንበረ እንደሚከተለው መልሰዋል። "ወጣቶች ላይ ይሰራል። ያለፉትን ያልተዘከረላቸውን ሰዎች ያስታውሳል።እንደገና ደግሞ በሕይወት እያሉ ልናመሰግናቸው ልናሞግሳቸው፣ለሌላው አርያ ሊሆኑ የሚችሉ የማኅበረሰቡ ክፍል አባላትን እና የዓመቱ ደግሞ ዘመን ተሻጋሪ ተሸላሚ፣ከሌላም ሃገር ቢሆን ብዙ ታሪክ በኢትዮጵያ የሰሩትን ሰዎች፣እነሱን በማንሳት፣እንዘክራለን እንሸልማለን፣ዕውቅና እንሰጣለን፣ካባም እናጎናጽፋለን።"



የዘንደሮ ተሸላሚዎች



የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ጸሐፊ አቶ አምዴ ጥላሁን በበኩላቸው፣ዘንድሮ በማኅበራዊ አገልግሎት፣በስፖርት ሥነ ጽሑፍና ሚዲያ፣እንዲሁም ቅን ልብን ጨምሮ በስምንት ዘርፎች፣ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ፣ለማኅበረሰቡ ከፍተኛ አገልግሎት ያበረከቱ ግለሰቦች መሸለማቸውን ገልጸዋል። «በአጠቃላይ፣በዘንድሮ ዓመት የሸለምናቸው፣ 11 የሚደርሱ ሰዎች፣ዕውቅና ሰጥተናል።በሚቀጥለው ምናልባት፣ከዚህ አጠናክረን የተሻለ ሥራ ለመስራት እንሞክራለን።ዋናው ጥሩ ሥራ እያመሰገን እና እያሞግሰን፣ሌላ ደግሞ ጥሩ ሥራ የሚሰሩ ሰዎችን የመፍጠር ሥራ ነው ዋና ዓላማችን እና እየተጋንበት እንገኛለን።»



በሦስቱም ዙር የተካሄደው፣ ምሳሌ ተብለው የተመረጡ ግለሰቦች፣በጎ የሰሩ ሰዎችን አንዱን ከአንዱ አበላልጦ እና አወዳድሮ ለመሸለም ሳይሆን፣ማኅበረሰቡ የተሳተፈበትን ጥቆማ በመቀበል፣ሚዛን የደፋውን የበጎ ሥራ አሸናፊ በማመስገን እናሽልማት በመስጠት፣አርአያ የሚሆኑ ሰዎችን መፍጠር እንደሆነ ተመልክቷል።



የማኅበራዊ አገልግሎት ተሸላሚዋ



በበጎ ሥራቸው፣ዘንድሮ ከተሸለሙት መኻከል፣ወይዘሮ ጤናአዳም ግርማ፣የካሌብ ፋውንዴሽን የበጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች ናቸው፥ፋውንዴሽናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ 200 ሺህ የሚሆኑ አቅም የሌላቸው ግለሰቦችን በተለይ ደግሞ እናቶች እና ህጻናትን፣በተለያዩ መስኮች ይደግፋል። «ካሌብ ፋውንዴሽን አትላንታ ውስጥ ቢሆንም የተቋቋመው፣ኮተቤ ካራ መድኃኔዓለም በተክርስትያን አጠገብ ነው ያለነው አዲስ አበባ፤ መስራት ስንጀምር 11 ዓመታት ሆኖናል።» ወይዘሮ ጤናአዳም እንዳሉት፣ካሌብ ፋውንዴሽን ትምህርት፣የምጣኔ ሀብት ድጋፍ፣የጤና መድኅን አገልግሎት እና የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አትኩሮ ከሚሰራቸው ዘርፎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ''



«አገልግሎት ነው የምንሰጠው፤ገንዘብ አንሰጥም።በትምህርት፣ከ 25 ሺህ ሰዎች በላይ፣በልጆች ማሳደጊያ ከአንድ ሺህ 400 በላይ ህጻናትና እናቶች በላይ፣በኢኮኖሚ ድጋፍ ከሁለት ሺህ በተሰብ በላይ፣አቋቁመናል።በዓመታዊ የጤና መድኅን በዚህ ዓመት ከሁለት ሺህ እንበልጣለን፣በዚህ ዓመት ደግሞ በዚህና በሚቀጥለው ወር፣በሥራቸው ካሉት ጨምሮ ወደ 500 ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት እየሰጠን ነው እና በአስቸኳይ ጊዜ፣ድጋፍ ደግሞ፣ከዘጠኝ ሺህ በላይ ሰዎች ላይ ሰርተናል ማለት ነው።»



በዘመን ተሻጋሪ ዘርፍ በቀደሙት ሁለት ዙሮች አርቲስት ማሪቱ ለገስን እና ተሾመ አሰግድን የሸለመው ምሳሌ የግበረ ሰናይ ድርጅት ዘንድሮ ድምፃዊ ፀሐዬ ዩሐንስን ሸልሟል።



ታሪኩ ኃይሉ



ማንተጋፍቶት ስለሺ



ሸዋዬ ለገሠ

Comments 
loading
In Channel
loading
00:00
00:00
1.0x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ለአገራቸውና ለማኅበረሰባቸው በጎ የሠሩ ግለሰቦች ሽልማት

ለአገራቸውና ለማኅበረሰባቸው በጎ የሠሩ ግለሰቦች ሽልማት

ታሪኩ ኃይሉ