በጋምቤላ ክልል ውጥረት ሰፍኗል ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ
Description
ውጥረት በጋምቤላ ክልል
በጋምቤላ ክልል ከከተማው ፖሊስ አዛዥ ግዲያ በኃላ በከተማይቱ ውጥረት መስፈኑን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ወደ አቦልና ላሬ የሚወስዱ የትራንስፖርት አገልግሎቶችም መስተጓጎላቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ ነዋሪዎቹ እንዳሉት የከተማ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዛሬም ዝግ ሆኖ መዋላቸውን አመልክተዋል፡፡ ይህ የሆነውም ማክሰኞ ጋምቤላ ከተማ ውስጥ የከተማው ፖሊሲ አዛዥ ኮማንደር ኡሞድ ኡጁሉ ባልታወቁ ሰዎች መገደልን ተከትሎ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር መባባስ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በመቀናጀት በክልሉ የጸጥታ ችግር የፈጠሩ አካላትን አድኖ በመያዝ ላይ መሆኑንና በርካቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ለጸጥታ ስራ ተመድበው ከሚሰሩት ጸጥታ ኃይሎች ውጪ የትኛውንም የጦር መሳሪያ ይዞ የሚገኝ አካል ላይ የጸጥታ ኃይሎች አስፈላጊውን እርምጃ›› ይወስዳሉ ሲል አብራርተዋል፡፡
የጋምቤላ ከተማ ፖሊሲ አዛዥ ባልታወቁ ሰዎች ተገደሉ
በጋምቤላከተማ ከትናትናው ዕለት አንስቶ ሱቆችና የተለያዩ ተቋማት ዝግ ሆኖ የዋሉ ሲሆን የሰዎች እንቅስቃሴም ተገድቦ መዋሉን ተገልጸዋል፡፡ ለዚህም ምክንያት ደግሞ አመልክተዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ የከተማው ፖሊስ አዛዥ ኮምደር ኡሞድ ኡጁሉ ባልተወቁ ሰዎች መገደላቸውን አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም ባልታወቁ ሰዎች ይደርሳሉ የተባሉ ጥቃቶች መበራከት ስጋት ምክንያት እንደሆነ አቶ ሮች የተባሉ ከተማው ነዋሪ በሰጡን አስተያየት አክለዋል፡፡ ከዛ ቀደም ብሎ በህዳር ወር መጨረሻ በከተማው ውስጥ የአንድ የባንክ ማነጀርን ጨምሮ ሁለት ሰዎች በታጠቀ ግለሰብ ተተኩሶባቸው የአንዱ ሰው ህይወቱ ሲያልፍ አንዱ ደግሞ መቁሰሉን አክለዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህዝብ ማመላለሻ መኪኖች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችም መደጋገማቸውን ገልጸው ህዳር 30/2018 በተመሳሳይ አቦል በተባለው ወረዳ ውስጥ በአንድ ተሽከርካሪ ላይ የታጣቁ ሀይሎች ጥቃት ማድረሳቸውን ገልጸዋል።
በጋምቤላ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርስ ጥቃት መባባስ
በጋምቤላ ክልል ለወራት የጸጥታ ሁኔታው ተሻሽሎ መቆየቱን የተናገሩት ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ሌላው ነዋሪም በጋምቤላ ከተማ ከማክሰኞ አነስቶ የጸጥታ ሁኔታ ተባብሶ መቆየቱን አሰታውቋል፡፡ በዚህ ሁለት ቀናት ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ቀደም ብሎ ህዳር 28 እና 30 በጋምቤላ ከተማ እና አቦል የተባለ ቦታ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በታጠቁ ሐይሎች ጥቃት በመፈጸሙ የጸጥታው ችግር እንዲስፋፋ ማድረጉን አክለዋል፡፡ በዚህ ጥቃትም የሰላማዊ ሰዎች ህይወት ማለፉን ያብራሩት ነዋሪው አቦል በተባለ በወረዳ ውስጥ በተደጋጋሚ በተሽከርካሪ ላይ ጥቃቱ መድረሱን አስረድተዋል፡፡ በክልሉ በነሔሴ 2016.ዓ.ም አድስ አመራር መተካቱን ተከትሎ በክልሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ቀንሶ እንደነበሩ ነዋሪው ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የተከሰተውን የጸጥታ አለመረጋጋትን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡን ወደ ከተማው ከንቲባ፣ክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ቢንደውልም መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ የክልሉ መንግስት በማህበራዊ መገናኛ ዜዴ ባስተላለፈው መግለጫም ግጭትና የሰው ሞት የሚያደስታቸው ብሎ የጠራቸው ኃይሎች የጋምቤላን ከተማን ጨምሮ በሌሎች ወረዳዎች ትርምስ መፍጠራቸውን ገልጸዋል፡፡ የክልሉ መንግስት በዚሁ መግለጫው ሰላም እና ልማትን ወደኃላ ለመመለስ ይሰራሉ ያላቸው ኃይሎች በየቦታው ሰዎችን መግደልና፣ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ማድረስ እና አመራሩ ዒላማ ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ























