DiscoverDW | Amharic - Newsኢትዮጵያ ዉስጥ ታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፤ የመገናኛ ብዙኀን ነጻነት እንዲከበር ተጠየቀ
ኢትዮጵያ ዉስጥ ታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፤ የመገናኛ ብዙኀን ነጻነት እንዲከበር ተጠየቀ

ኢትዮጵያ ዉስጥ ታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፤ የመገናኛ ብዙኀን ነጻነት እንዲከበር ተጠየቀ

Update: 2025-12-18
Share

Description

የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፤ የመገናኛ ብዙኀን ነጻነት እንዲከበር የመብት ተከራካሪዉ ድርጅት ጠየቀ



ጋዜጠኛ ኢዮብ ሽመልስ በአስቸኳይ እንዲፈታ የዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት በድጋሚ ጠየቀ። ከኅዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሀሰት መረጃ በማሰራጨት እና ስም በማጥፋት ክስ ተመስርቶበት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ኢዮብ ሽመልስ፤ ፍርድ ቤት ትናንት ቀጠሮዉን ለተጨማሪ ዘጠኝ ቀናት ማራዘሙ ተመልክቷል። አዜብ ታደሰ ተጨማሪ ዘገባ አላት።



ከኅዳር 22 ጀምሮ የሀሰት መረጃ በማሰራጨት እና ስም በማጥፋት ክስ በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ኢዮብ ሽመልስ በአስቸኳይ እንዲፈታ ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት «CPJ» ድጋሚ ጠይቋል። በሲዳማ ክልል ሙስናን በተመለከተ ከሲዳማ በቲክቶክ ዘገባን ያሰራጨዉ ግል ጋዜጠኛ ኢዮብ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በክልሉ ርዕሰ መዲና ሀዋሳ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ አቅራብያ ተይዞ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወደሚገኘዉ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱን CPJ ጉዳዩን ያዉቃሉ ያላቸዉን ሁለት ሰዎች ጠቅሶ ባለፈዉ ሳምንት ነበር፤ በግል የሚንቀሳቀሰዉ ጋዜጠኛ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ሲል መግለጫ ያወጣዉ። አቶ ኢዮብ በቅርቡ በሲዳማ ክልል በባለሥልጣናት ተፈጽሟል ስለተባለው በደል ዘገባዉ መጠየቁን ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት «CPJ» የዓይን እማኞችን ጠይቆ መረዳቱን በመግለጫዉ አክሏል። ኬኒያ ናይሮቢ ላይ የሚገኙት የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት የ«CPJ» ሲፒጄ የአፍሪቃ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ፤ በቲክቶክ መረጃን የሚጋራዉ ጋዜጠኛ ኢዮብ ሚዛናዊ እና እዉነተኛ ዘገቦችን የሚያሰራጭ ነው ይላሉ።







የደህንነት ማረጋገጫ ቢሰጠዉም ታስሯል

«ኢዮብ ሸመልስ ሲዳማ ዜና የተሰኘ የቲክቶክ ገፅ ያለዉ ጋዜጠኛ ነዉ። በደረሰን መረጃ መሰረት፣ በዚህ የቲክቶክ ገፁ ላይ፣ በእዉነተኛ የጋዜጠኝነት ስነምግባርን ተላብሶ ይሠራ ነበር። በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ዘገባ እና ትንታኔዎችን ሲያካፍል ቆይቷል። አካባቢዉ ላይ የባለሥልጣናት የሙስና ውንጀላዎችን እና የመብት ጥሰቶችን አጋልጧል። ይሁን እና በቲክ ቶክ ገፁ ላይ ከሚሠራቸው እነዚህ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ማስፈራሪያዎች አጋጥመውታል። በዚህ በያዝነዉ ዓመት መጀመርያ ላይ ለአጭር ጊዜ ታስሮ ነበር። በዚህም ምክንያት ወደ ምሥራቅ አፍሪቃ ማለትም ወደ ኬንያ እና ዩጋንዳ ለመሰደድ ተገድዶ ነበር። ምንም እንደማይሆን ደኅንነቱ የተጠበቀ እንደሆን የተወሰነ ማረጋገጫ ካገኘ በኋላ ከተሰደደበት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። ግን እንደተነገረዉ ደኅንነቱ የተጠበቀ አልነበረም። በያዝነዉ ወር መጀመርያ ታኅሣሥ 1 ቀን በሲዳማ ክልል በተለይም አዋሳ ውስጥ በመንግሥት ባለሥልጣናት ተይዞ በእስር ላይ ይገኛል። ከቲክቶክ ገጹ ጋር በተያያዘ ተጠይቋል። እና እንደውም ዛሬ ዲሴምበር 17 ቀን ፍርድ ቤት ይቀርባል ብለን ጠብቀን ነበር። ግን እኛ እስከምናውቀው ድረስ ኢዮብ እንደታገደ ይቆያል። እና እኛ እስከምናውቀው ድረስ የፈፀመው ወንጀሉ በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ የሚደርሰውን በደል ማጋለጥ ነው።»



ስድስት ጋዜጠኞች ታስረዋል ሁለት የDW ጋዜጠኞችም ከስራ ታግደዋል

የCPJ የአፍሪቃ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ «ሙስናን የሚያጋልጥ ጋዜጠኛ እስራትና ማስፈራሪያ እየደረሰበት መሆኑ አሳሳቢ ነው» ብለዋል። «የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ኢዮብ ሽመልስን በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና የጸጥታ ሃይሎች እና ፍርድ ቤቶችን በመጠቀም ገለልተኛ ዘገባዎችን ማፈን ማቆም አለባቸው» ሲሉም አክለዋል።

«አዎ እንዲፈታ እየጠየቅን ነው። ምክንያቱም ጉዳዩን በኢትዮጵያ በተለይም ጋዜጠኞች ላይ ትኩረት ተደርጎ ለእስር እየተዳረጉ የመሆናቸዉ አካል አድርገን ስለምንመለከተው ነው። ሲፒጄ ያለውን ወቅታዊ መረጃ ከተመለከትን ኢዮብ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በእስር ላይ ከሚገኙት 6 ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው። ሌሎች ታስረዉ የነበሩ ጋዜጠኞች ከቅርብ ወራት በፊት ተፈተዋል። ነገር ግን እርስዎ በግልጽ እንደሚያውቁት፣ ቢያንስ ሁለት የዶይቼ ቬለ DW ዘጋቢዎች በቋሚነት መታገድን የመሳሰሉ ሌሎች በፕሪስ ነጻነት ላይ የጭቆና ድርጊቶችን አይተናል። እና በግል የሚንቀሳቀሱ ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰዉን ማስፈራሪያ እና ሌሎች ነገሮችን ዘግበናል። ይህንን ደግሞ ጋዜጠኞች በሥልጣን ላይ ላሉት የማይመቹ ወይም ወሳኝ የሆኑ ነገሮችን ሲናገሩ በሰፊው የጥቃት ኢላማ አካል ሆነዉ እናያለን። ስለዚህም ኢዮብ እንዲፈታ እየጠየቅን ነው። የኢዮብን መፈታት ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች ሥራቸውን እንዲሠሩ፣ ሕዝብ ጉዳዮችን እንዲያውቅ ለማድረግ ለሚደረገዉ ጥረት ሰፊ ማሻሻያ አካል አድርገን እንቆጥረዋለን።»



መንግሥታት ምርጫ ሲቃረብ ጋዜጠኞችን ማዋከባቸዉ የተለመደ ነዉ



የዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት CPJ ፤ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተሟጋቾች የዶይቸ ቬለ ሁለት ወኪሎች በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለ ሥልጣን ለዘለቄታው መታገዳቸውን አዉግዘዋል። ሂውማን ራይትስ ዎች ከቀናት በፊት «ኢትዮጵያ ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ነጻነት ላይ ሌላ አሉታዊ ተግዳሮት» በሚል ዐቢይ ርእስ ባወጣው መግለጫ በንዑስ ርእሱ፦ «ዶይቸ ቬለ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ገለልተኛው ፕሬስ ላይ የተደቀነ መጠነ ሰፊ ሥጋት መሆኑን ያረጋግጣል» ብሏል። የዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት የአፍሪቃ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ፤ መንግሥታት ብሔራዊ ምርጫ ሲቃረብ ጋዜጠኞችን ማዋከባቸዉ የተለመደ ነዉ። በኢትዮጵያ እና በቀጠናዉ አካባቢም የሚታየዉ ይኸዉ ተግባር ነዉ ይላሉ።

«የጋዜጠኞች እስር በኢትዮጵያብቻ ሳይሆን በቀጣናዉም እንዲህ ዓይነት ነገር ይታያል። በተለይም የምርጫ ሰሞን ጋዜጠኞች ይታደናሉ። በምርጫ ወቅት ጋዜጠኞች ሥራቸውን በነጻነት እንዲሠሩ ከሚፈለግባቸዉ ወሳኝ ጊዜያት አንዱ ነው። ምክንያቱም ከምርጫ በፊት ጋዜጠኞች ለሕዝብ ብዙ ነገሮችን ያሳዉቃሉ። በምርጫ ወቅት ጋዜጠኞች የምርጫውን ግልፅነት ፣ የድምጽ ቆጠራውን ግልፅነት በዘገቦቻቸዉ የሚያረጋግጡ ናቸዉ። ከምርጫ በኋላም ጋዜጠኞች በሥልጣን ላይ ያሉት፤ ለመራጮቻቸዉ የገቡትን ቃል መፈፀም አለመፈፀማቸዉን ይጠይቃሉ። ስለዚህ ጋዜጠኞች በምርጫ ወቅት በጣም የሚፈለጉ ናቸው። ይሁንና በዚህ ክልል በምርጫ ሰሞን ጋዜጠኝነት አደጋ ላይ የሚወድቅበት፣ ባሥስልጣናት ጋዜጠኞችን ለመገደብ የሚሞክሩበት ጊዜ መሆኑንም አይተናል። ይህ ለመጭዉ የኢትዮጵያ ምርጫ ምን ማለት ነው? እንደሌሎች ቦታዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሥራውን ለመሥራት ነጻ መገናኛ ብዙኀን ያስፈልገዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ አሁን ባለንበት መንገድ ከቀጠለ፣ የቅድመ ምርመራ ድርጊቶች ከቀጠሉ፣ ጋዜጠኞች እንደ ሙስና ያሉ ድርጊቶችን ሲያጋልጡ ሊታሰሩ የሚችሉ ከሆነ፣ በዚህ ወሳኝ የምርጫ ወቅት ሚዲያዎች ሥራቸውን መሥራት ይችላሉ የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል።»





ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት CPJ ፤ ከሲዳማ ፖሊስ እና ለክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምላሽ ለማግኘት ሞክሮ እንዳልተሳካለትም በመግለጫው አስታውቋል። በ CPJ መግለጫ መሠረት ቢሮው በፌስቡክ ገጹ በላይ ባስቀመጠዉ የኢሜል አድራሻ ኢሜል ቢልክም፤ አድራሻዉ ስህተት ጠቁሞ መልእክቱ ተመላሽ ሆኗል።





አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ኢትዮጵያ ዉስጥ ታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፤ የመገናኛ ብዙኀን ነጻነት እንዲከበር ተጠየቀ

ኢትዮጵያ ዉስጥ ታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፤ የመገናኛ ብዙኀን ነጻነት እንዲከበር ተጠየቀ

Azeb Tadesse Hahn