የምርጫ አስቻይ ኹኔታዎች በኢትዮጵያ
Description
የምርጫ አስቻይ ኹኔታዎች በኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድምርጫ ለማስፈጸም አስቻይ ሁኔታ ያሉባቸውን አካባቢዎች እንዴት እንደሚወስን ይፋ ባደረገው መግለጫ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ "ተሞክሮ" ያለውን በመውሰድ ከስድስት ወራት በኋላ ለሚያከናውነው 7ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ "ከክልል መንግሥታትና ከከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም ከፀጥታ ተቋማት" መረጃዎችን ሲሰበስብ መቆየቱን ገልጿል። ምርጫ ማድረግ ይቻላል ለሚላቸው ቦታዎች አረንጓዴ፣ ከጥንቃቄ ጋር ማድረግ የሚቻልባቸው የተባሉትን ቢጫ እና ምርጫ ማድረግ የማይቻልባቸውን በቀይ ቀለማት እንደሚበይን፣ ይህንኑም በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግም ገልጿል። የመንግሥት መዋቅሮች ጋር በዚህ መስፈርት ውይይት ያደረገው በዋናነት "በሰላምና ፀጥታ ሁኔታ" ዙሪያ እንደሆነም ጠቅሷል።
ቦርዱ ይህንን ከለየ በኋላ "ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከክልል መንግሥታት እና ከከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም ከፀጥታ ተቋማት ጋር ውይይት ያደርጋል።" ተብሏል።
በቅርቡ መግለጫ የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተ ወርቅ ኃይሉ አባሎቻቸው ለእሥር፣ ለእንግልት፣ የጽሕፈት ቤት መዘጋት፣ ስብሰባ እንዳያደርጉ የመከልከል ፈተና ውስጥ መሆናቸውን የሚገልፁ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳሉ ገልፀዋል።"አስቻይ ኹኔታ በአንድ አቅጣጫ በሰላም ብቻ አይደለም የሚተረጎመው።"
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሥጋት እና የብልጽግና ግምገማ
ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ሕዳር 17 ባወጣው መግለጫ ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ "አስቻይ ኹኔታዎች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ" ገምግሟል። በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶች ቅድሚያ በመንግሥት ፖለቲካዊ ርምጃ መፍትሔ እንዲሰጣቸ በመጠየቅ "ግጭቶችን ማስቆም እና የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ" የግድ እንደሚያስፈልጉ በመጥቀስ።
ከሁለት ሳምንት በፊት ለፓርቲያቸው ከፍተኛ አመራሮች ሰጡት በተባለው ስልጠና የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዐቢይ አሕመድ "መቶ በመቶ የምርጫ ምቹነት ማረጋገጥ አለብን" ሲሉ ተደምጠዋል። "ሰላም የለም፣ ምርጫ አያስፈልግም የሚባል ነገር ሥርዓተ - መንግሥት ለማፍረስ፣ ለማዳከም እንደ መግቢያ ነጥብ የሚያገለግል ስልት ነው" ያሉት ዐቢይ እያንዳንዱ ወረዳ፣ ዞን እና ክልል "ራሱን ሊፈትሽ ይገባል" ሲሉ "ምርጫ ዴሞክራሲዊ፣ ለሁሉም ኃይሎች አስቻይ እንዲሆን መሥራት ነው" ብለዋል። "ውድድሩን ብቁ ካደረግን በሀሳብ ልቀን ለመመረጥ ሰፊ እድል አለን" ያሉት የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት "ያ ዕድል የሚበላሸው አስቻይ ምቹ ኹኔታ መፍጠር ካቃተን ነው"ብለዋል።
ኢዜማ ከትናንት በፊት በሰጠው መግለጫ ግንኢትዮጵያ ውስጥ "በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ጦርነቶች የብሔር ፖለቲካ ውጤቶች ናቸው" በማለት የዘር ፖለቲካ እንደማይበጅ ተጨባጭ ማስረጃ ይዘን ወደ ምርጫ ስለምንገባ ለማሸነፍ ይህ ይበቃናል" ሲሉ የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኢዮብ መሣፍንት ገልፀዋል። ይህንን ለመቀስቀስ ግን "እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች አሉ" ሲሉ ተችተዋል። ለምርጫ አስቻይ ኹኔታ እንደሌለ በመግለጽ የምርጫ ሕጉን መስፈርት ለማሟላት ብቻ የሚሳተፉ መኖራቸው የገለፁ የፖለቲካ ፓርቲችም አሉ። ከሳምንታት በፊት ስብሰባ ማድረግ ተከለከልኩ ያለው ኢሕአፓ ውድድር ውስጥ እንደሚገባ ገልጾ ምህዳሩ ግን እንዲሰፋ ጠይቋል።
የምርጫ ምኅዳር በአወንታዊነት የሚገለፀው ምን ሲሟላ ነው?
የምርጫ ምኅዳር በአወንታዊነት የሚገለፀው በዋናነት ሰላም እና ደህንነት፣ የፖለቲካ ነፃነት እና ምቹ የሲቪክ ምህዳር፣ ገለልተኛ የምርጫ ተቋማት፣ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና እኩል የመገናኛ ዐውታሮች ተደራሽነት፣ የሰብአዊ መብቶች መከበር፣ የሕግ የበላይነት፣ የዜጎችን ነፃነት መጠበቅ እና የፖለቲካ እሥረኞችን መፍታትን ሲጨምር ነው።
ሶሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ























