ኢትዮጵያ ውስጥ ተጠናክሮ የቀጠለው የቲክቶከሮች እስራት
Description
የፖሊስ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያዎች
ማህበራዊ ሚዲያንበመጠቀም ሙያዊ ክብርን ያዋረዱ፣ ከህብረተሰቡ ባህልና ሞራል ተቃራኒ የሆኑ መልዕክቶችን ሲያሰራጩ ነበሩ ያላቸውን ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ፖሊስ እንዳስታወቀው፤ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦቹ የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሙያዊ ክብርን የሚያዋርዱ፣ ከህብረተሰቡ ባህል፣ እምነትና ሞራል ተቃራኒ የሆኑ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ የነበሩ ናቸው፡፡ “የማህበራዊ ሚዲያ አንቂና ይዘት ፈጣሪዎች ነን” ያሉት ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ የሀገሪቱን ባህል፣ ወግ፣ እምነትና ሞራል በማይመጥን መልኩ "Illuminant" ወይም "የሠይጣን ማህበርተኞች አባላት ነን እኛን ምሰሉና ገንዘብ ታገኛላችሁ" የሚሉ መልዕክቶችን ያስተላለፉ፤ የትምህርት እና መምህርነት ሙያን በመኒያሰራጩት ተንቀሳቀሽ ምስል ያቃለሉ፣ ልብስ በማውለቅና ራቁት በመሆን "ሰግጥ ፈምስ" በማለት በየመንገዱ ህብረተሰቡን ያወኩ እንደሚገኙበትም የፖሊስ መግለጫው አስረድቷል፡፡
የማኅበረሰቡ ዕይታ
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በተመሳሳይ ሁኔታ የታሰሩ ይዘት ፈጣሪና ተጽእኖ የሚያሳድሩ የተባሉ ተክቶከሮች በገፍ መታሰራቸውን ተከትሎ ከህብረተሰቡም የተለያዩ አስተያየቶች ተሰትተዋል፡፡ አንደኛው አስተያየት ሰጪ “አሁን ላይ ትኩረት ማግኘት የወጣቱ ትልቁ ስራ እየሆነ በመምጣቱ ማህበረሰቡ ሃይ ማለት አለበት” ሲሉ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ፤ “አሁን ላይ መንግስት የጀመረው ስርዓትን የማስየዝ ጅማሮ” በማድነቅ “አብዛኛው ነገሩ ከማስጠንቂያ የሚያልፍ አይደለም” በመናለት ነገሮች ወደ እስር ባያድጉ ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡
እስራቱ ሃሳብን በመነጻነት ከመግለጽ ሰብኣዊ መብት አኳያ
በጉዳዩ ላይ ከሀሳብ ነጻነት አኳያ አስተያየታቸውን የሰጡን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር በፍቃዱ ድሪባ ጉዳዩን በተለያዩ አቅጣጫዎች ማየት ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “አንደኛው ነገር አንድ ሰው ሃሳቡን በነጻነት የመግለጽ ሙሉ መብት አለው” በማለትም ነገር ግን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በራሱ ወሰን የለሽ እና ከልክ በላይ የሚለጠጥ እንዳልሆነ ማዋቅ ተገቢ ነው ሲሉ በአስተያየታቸው አንስተዋል፡፡ “የሃሳብ ነጻነት ላይ ገደብ የሚጣልበት በግለሰቦች እና በማህበረሰብ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ ነው” ያሉት አቶ በፍቃዱ፤ ከማህበረሰቡ እሴትና ባህል ጋር የሚጋጩ እንዲሁም የተለየ ጉዳት የሚያደርሱ ከሆነ ገደብ ልጣልበት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ፖሊስ በሰሞነኛው ተከታታይ እስራቶቹ ላይ ይዘት ፈጣሪ ነን ያሉት ግለሰቦቹ ማህበረሰቡን የማስደንገጥ፣ ራቁት በመሆን አላስፈላጊ ከህብረተሰቡ የተለመደ ባህል ተቃርኖ መቆምን የመሳሰሉ ተግባራት መፈጸማቸውን ጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ግለሰቦቹ ላይ ተገቢ ያለውን የወንጀል ምርመራ ስራ መጀመሩንና በቀጣይም ተመሳሳይ ድርጊት ውስጥ የሚገቡ "አንቂ ነን" ባዮችን እንደማይታገስም አሳስቧል፡፡
ገደቡ ተለጥጦ ሰብኣዊ መብትን እንዳይጎስ..
የህግ ባለሙያው በፍቃዱ ድሪባ ይህ የህግ ትርጉምም የሚፈልግ ነው ይላሉ፡፡ “ድርጊቱ ከህዝብ እሴት ጋር ይቃረናል አይቃረንም የሚለው ጉዳይ በፍርድ ቤት ውሳኔ የሚያገኝ ቢሆንም ግለሰቦች ሌሎችን እስካልነኩና እስካላዋረዱ ድረስ በነጻነት የሻቸውን ማድረግ እንደሚችሉ” ግን ሙያቸው እንደሚያስረዳ አንስተዋል፡፡ በግለሰቦች መብት ላይ የሚጣሉ ገደቦችም ዋናውን በዓለማቀፍ ህግጋት የሚሰጡ የሰብዓዊ ነጻነቶች ጋር እንዳይጋጭ ትንቃቄ መወሰድ እንደሚኖርበት በሙያዊ አስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ























