በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትና በዋጋዉ ንረት ምክንያት ፋብሪካዎች እየከሰሩ ነዉ
Description
ኮምቦልቻ-ደቡብ ወሎ የሚገኙ የፋብሪካ ባለቤቶች በኤልክትሪክ ኃይል እጥረትና በየጊዜዉ በሚንረዉ የኃይል ዋጋ ምክንያት ፋብሪካዎቻቸዉ እየከሠሩ መሆኑን አስታወቁ።ኮምቦልቻ የተለያዩ ፋብሪካዎች የሚገኙባት የኢንዱስትሪ ከተማ ናት።የፋብሪካዎቹ ባለቤቶች እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲሕ የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ በመቆራረጡ ከሥራ ለመዉጣት እየተገደዱ ነዉ።ሠራተኞች በበኩላቸዉ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ አነስተኛ አምራቾችንም መጉዳቱን ይናገራሉ
የኤሌትሪክ ሀይል ለወራት እየተቆራረጠፋብሪካዎቻቸው ከሚያመርቱበት ቀን ይልቅ ያለምርት የሚያሳልፉበት ሰራተኞቻቸው ያለስራ ደመወዝ የሚከፈልባቸው በአማራ ክልል የኢንድስትሪ መዳረሻ የሆነችው ኮምቦልቻ ከተማ እና በዙሪያው ያሉ ፋብሪካ ባለቤቶች አሁን ያለው ሁኔታ ፈትኖናል አሉ፡፡ ‹‹አሁን ግቢ ውስጥ ሔደህ ሰራተኞችን ብታይልኝ ምንም እየሰራን አይደለም፤ ለህዝብ ተደራሽ አልሆንም፤ ምርት እያለን እቃ እያለን፤ መፍጨት አቃተን፤ ሰራተኛ ቁጭ ብሎ ደመወዝ እየከፈልን ነው፡፡››
በመብራት ሀይል መቆራረጥ ምክንያት ፋብሪካ መዝጋት ማሰብ
የመብራት ሀይል መቆራረጡ ከፍተኛ በመሆኑ ፋብሪካ ለመዝጋት እስከ ማሰብ ያደርሳል የሚሉት የፋብሪካ ባለቤቶች መቆራረጡ እንዳለ ሆኖ እንኳን ለመስራት፤ መብራት ከሚኖርበት የማይኖርበት ጊዜ ይበዛል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
‹‹ያለው ችግር በጣም ከፍተኛ ነው፤ ከምንሰራበት የማንሰራበት ነው የሚበልጠው እና ከአቅም በላይ ሆኗል እየሰራን አይደለም፤ ለመዝጋት የሚያስችል ነው ያለው ሁኔታ ስራ አያስቀጥልም፤ የሚበራበትን ጊዜ ብትጠይቀኝ ነው የሚሻለኝ፡፡››
ችግሩ ከከፍተኛ ፋብሪካዎች በዘለለም በአነስተኛ እና ጥቃቅን ተደራጅተው የሚሰሩ አምራቾች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት የስራ አንቀሳቃሾች ያለ ስራ ለሰራተኛ ደመወዝ ለመክፈል ተገደናል ሲሉ ይገልፃሉ፡፡
‹‹በጣም ጎድቶናል ይቆራረጣል፤ ለአንድ ቀን ሙሉ የሚቋረጥበት ጊዜ አለ፣ አልፎ አልፎ የሚቆራረጠው ብቻ ሳይሆን ማምረት ላይ በብዙ ይጎዳል ዝም ብለን ለሰራተኛ የምንከፍለው፡፡››
ሰራተኞች ለመቀነስ ማሰብ
አሁን ላይ ሰራተኞችን ለመቀነስ እያጤንን እንገኛለን የሚሉት ባለሀብቶች ከመብራት በተጨማሪ የውሃ እጥረት ስራውን አስተጓጉሎታል ይላሉ፡፡
‹‹አሁን ላይ ያለን አማራጭ ሰራተኞቻችንን እንዴት እናድርግ ነው፤ አሁን የመብራቱን ስላያችሁት ነው በእያንዳንዱ ቤት ስለሚጠፋ፤ ውሃም እንደዚሁ ነው የሚጫወትብን፤ ሆን ብለውም ሊሆን ይችላል የመልካም አስተዳደርም ችግር ይመስላል፡፡››
የመብራት መቆራረጡ ለወራት እንደዘለቀ የሚገልፁት በአነስተኛ የልብስ ስፌት ስራ ላይ የተሰማሩ ስራ ፈጣሪዎችን መቆራረጡ በመቀጠሉ ቤተሰቦቻችንን ለመመገብ አልቻልንም በማለት ይናገራሉ፡፡
‹‹አብዝሃኛው ማህበረሰብ በቀን ስራ የሚተዳደር ነው ቀኑን ሙሉ መብራት ከሌለ እኛ የምንበላው የለም፡፡ የምናገኘው ነገር የለን፤ ይህ በተደጋጋሚ ለወራት የቆየ ነው በዚህ ሁኔታ ላይ ይህ ማህበረሰብ እንዴት ነው ሰርቶ መብላት የምንችለው፡፡››
በስድስት ከተሞች የሚሰራ የመብራት ፕሮጀክት አለመጠናቀቅ
በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሀይል ደሴ ሪጅን ዳይሬክተርአቶ ሀብቱ አበበ እንደሚገልፁግትም አሁን በኮምቦልቻ ደሴ እና የተለያዩ አካባቢ የተፈጠረው የሀይል መቆራረጥ በ6 ከተሞች ላይ በሚሰራ ፕሮጀክት ምክንያት የመጣ በመሆኑ ፕሮጀክቱን በፍጥነት አጠናቀን ወደቀደመ የሀይል ስርጭት እንመለሳለን ይላሉ፡፡
‹‹ትንሽ ችግሩን ያባባሰው የ6 ከተሞች ፕሮጀክት እየተሰራ በመሆኑ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በባለፈው የጀመረው ያላጠናቀቀው ምሰሶውን አቁሞ ሽቦ ያልተዘረጋ ከነባሩ መስመር ጋር ስለተጠጋጋ ኮንክሪቱ ጋር ሲጋጭ ነው ሀይል እያጠፋብን ያለው፡፡ ፕሮጀክቱን ቶሎ እንዲጠናቀቅ ተነጋግረናል፡፡ እሱ ከጨረሰ ይስተካከላል፡፡
ለተወሰነ ሰዓታት ለ8፡00 እና 9፡00 ሰዓት ሀይል ያጠፋሉ ስራውን ለመስራት እና በአጭር ጊዜ አጠናቁ ተብሏል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይስተካከላል፡፡››
በኮምቦልቻ ከተማ 3 ሰብስቲቲዩሽን ያሉ በመሀኑ ምንም አይት የሀይል እጥረት አለጋጠመንም የሚሉት አቶ ሀብቱ አበበ የቀደሙት የመብራት ሀይል አስተላላፊ መስመሮችን በአዲስ የመተካት ስራው ሲጠናቀቅ አስተማማኝ የሀይል አቅርቦት ይኖረናል ብለዋል፡፡
ኢሳያስ ገላዉ
ነጋሽ መሐመድ
ልደት አበበ























