በምሥራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት አራት ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ
Description
የኪረሙ ወረዳ ጥቃት የሰዎች ሕይወት ማለፉ
በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ በደረሰ የታጣቂዎች ጥቃት 4 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለው ሌሎች አራት መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ ። ነዋሪዎቹ እንዳሉት ከጥቃቱ በተጨማሪ ታጣቂዎቹ በርካታ የቁም እንስሳት ዘርፈዋል። ስለ ኹኔታው ለዶቼ ቬለ አስተያየየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪዎች የመንስግ የጸጥታ ኃይሎች ሊከላከሉልን አልቻሉም ሲሉ ወቅሰዋል። በጉዳዩ ላይ ከወረዳ እስከ ክልል ያሉ የመንግስት ባለስልጣናትን ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
በምሥራቅ ወለጋ የኪረሙ ወረዳ ለዓመታት የዘለቀው የጸጥታ ስጋት ዛሬም መቋጫ እንዳለገኘ ነው የወረዳው ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ የገለጹት ። ነዋሪዎቹ እንዳሉት በወረዳው የአባይ ሸለቆ አዋሳኝ በሆነችው የዋስቲ ቀበሌ በደረሰ የታጣቂዎች ጥቃት አራት ሰዎች ተገድለው አራቱ ቆስለዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን የአካባቢው ነዋሪ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ህብረተሰቡ በራሱ ታጣቂዎችን እንዳይከላከል የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የቀበሌዋን ነዋሪ ትጥቅ አስፈትተው ወስደዋል ሲሉም ይወቅሳሉ
«አልፈው ሂደው ነው እንግዲህ ስምንት አርሶ አደሮችን በጥይት መትተው አራቱ ወዲያው ሞተው ተቀብረዋል፤ በትንሹ ከህዝቡ ላይ ወደ 25 የጦር መሳሪያ ነጥቀው ወስደዋል፤ በዚህም እንግዲህ ትናንት የሞተው ሞቶ የተቀረው ጫካ ለመግባት ተገዷል»
መንግሥት የነዋሪውን ደህንነት ማስጠበቅ አልቻለም መባሉ
በተለያዩ «የጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን» አደረጃጀቶች ለጥቃት እና ዘረፋ ተጋላጭ ናት በተባለችው በዚህችው ቀበሌባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ በደረሰ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት እኚው አስተያየት ሰጭ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ሊከላከሏቸው አልቻሉም ሲሉ ወቅሰዋል።
« በአርሶ አደሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዉበታል። ለጽንፈኞች ሲባል አርሶ አደሩ ማዳበሪያ ለማግኘት ወደከተማ መውጣት አልተቻለውም፤ እቤቱ ተቀምጦ ከብቶቹ ብቻ እንኳ እንዳይጠቀም እንዲህ አድርገዉታል። »
ድምጻቸውን እንድንቀይር የጠየቁን እና በዋስቲ ቀበሌ የደረሰውን ግድያ ያረጋገጡልን ሌላ የወረዳው ነዋሪ እንዳሉት «ጽንፈኛ » የተባሉ እነዚሁ የታጠቁ ኃይሎች በምስራቅ ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ከሚያደርሷቸው ጥቃቶች በተጨማሪ የአርሶ አደሩን ከብቶች ዘርፈው ወስደዋል። በተጨማሪም አልፈው በከተሞች ጭምር ሳይቀር ሰዎችን አግተው በመውሰድ ቤዛ ይጠይቁበታል፤ ይህ ከህዝቡ አቅም በላይ እየሆነ መጥቷል፤ በማለት ገልጸዋል።
« ሁሉም ሰው በደንብ የሚያውቀው የጊዳ ከተማ ነዋሪ የአባ ጃቢር ልጅ ጃቢርን አግተው በመውሰድ 2 ሚሊዮን ጠይቀውበት ገንዘቡ ከተሰጣቸው በኋላም ሊለቁት ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም ፤ ምናልባት የልጁ እጣ ፈንታ ሞት ሊሆን ይችላል ። ዕለት ዕለት ነው ሰው እያፈኑ የሚወስዱት »
በአካባቢው የቀጠለው ግጭት እና ጥቃት
በምስራቅ ወለጋ ዞን ቀደም ሲል በኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል ዓመታት የወሰደ ግጭት ሲካሄድ ቆይቷል። መፍትሔ ሳያገኝ ዛሬም የቀጠለው ግጭቱ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ግድያ እና ዘረፋ እየተባባሰ መሄዱን የሚገልጹት ነዋሪዎች ነዋሪው አሁንም በሰቆቃ ውስጥ እንዲኖር አስገድዶታል ይላሉ ።
በኪረሙ የዋስቲ ቀበሌ ደረሰ ስለተባለ ጥቃት እና ዘረፋ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ፍቃዱ ማብራሪያ እንዲሰጡን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ቆይታችሁ ደውሉ የሚል መልስ ከሰጡን በኋላ ቆይተን በተደጋጋሚ ብንደውልላቸውም ስልካቸውን ሳያነሱ ቀርተዋል። በምስራቅ ወለጋ ዞን አሁንም የቀጠለው የታጣቂዎች ጥቃት እና የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ሰላማዊውን ሰው መከላከል አልቻሉም ተብሎ ለቀረበ ቅሬታ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ዋቅ ጋሪ ነገራ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ሙከራ ስልካቸው ባለመነሳቱ ሳይሳካልን ቀርቷል። የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ በዚሁ ጉዳይ መልስ እንዲሰጡን ያደርገነው ጥረት በተመሳሳይ ስልክ ባለመነሳቱ ሳይሰምርልን ቀርቷል።
የነዋሪው ስጋት ከፍ ማለቱ
የሆነ ሆኖ ግን በምስራቅ ወለጋ በኪረሙ እና በአጎራባች ወረዳዎች በታጣቂዎች እየተፈጸሙ ነው ስለተባሉ እና የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ሊከላከሉን አልቻሉም ለተባሉ ጥቃቶች ዶቼ ቬለ የነዋሪዎችን አስተያየት ለማሰባሰብ ባደረገው ጥረቱ የነዋሪውን ስጋት ከብዙ በጥቂቱ መረዳት ችሏል። በአካባቢው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲገልጹልን ጥያቄ ያቀረብንላቸው በርከት ያሉ ነዋሪዎች በደህንነት ስጋት አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ነግረዉናል ።
የተቀየረ ድምጽ
«ተው ይቅርብኝ አሁን ምንም ልልህ አልችልም። ያለንበት ሁኔታ ራሱ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ፤ እንዲሁ ግን በማህበራዊ መገናኛ ገጾች ላይ የተሰራጩ መረጃዎችን ማየት ትችላላችሁ ፤ እሱ ነው የሆነው። ስለሆነው ነገር ጽሁፉ ብዙ ቦታ ደርሷል፤ ሁኔታውን እንደዚያ ተረዱት »
ባለፉት ስድስት ዓመታት ኪረሙ ወረዳ ውስጥ በደረሱ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች ሲገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ዶቼ ቬለ በተለያየ ጊዜ ሲዘግብ ቆይቷል።
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ























