መፍትሄ ያጣው ግጭትና የልማት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ
Description
መንግሥት የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን ይገልጻል። በቅርቡም የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ምረቃ እና አዳዲስ እንቅስቃሴዎችም ታይተዋል። የሀገሪቱ ኤኮኖሚዊ እድገትን ከማፋጠን በተጨማሪ የኅብረተሰቡን ኑሮውን ሊያሻሽሉ እንደሚችሉም ተስፋ ይሰጣል። በአንጻሩ ሃገሪቱ ውስጥ ያላባራው ግጭት የልማት ተስፋውን እንዳያጨልመው የሚሰጉ ጥቂት አይደሉም። በአንድ አካባቢ የሚኖረው ግጭት ወደሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ ሊያስከትል የሚችለው ውድመት በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ጀምሮ ወደ አማራና አፋር ክልል በመዛመት የተከሰተው የቅርብ ጊዜ ተሞክሮ ነው። አሁንም በኦሮሚያ ከአምስት ዓመታት በላይ የዘለቀው ግጭት፤ እንዲሁም በአማራ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ የቀጠለው ውጊያ፤ በተመሳሳይ በአንዳንድ አካባቢዎችም ያለው የጸጥታ አለመረጋጋት ለልማት እንቅስቃሴው ስጋትነቱም አያነጋግርም። የልማት እንቅስቃሴ እና መፍትሄ ያጣው ግጭት በኢትዮጵያ የዚህ ሳምንት የዶቼ ቬለ መወያያ ርዕሰ ጉዳይ ነው።
ተወያዮች ኢትዮጵያ ውስጥ የንድ ባንክ ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ መምህርነት ያገለገሉ፤ በዩኤስ ኤድ ካሜሮንና ቻድ፤ እንዲሁም ለ30 ዓመታት በዓለም ባንክ በልዩ ልዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶክተር አክሎግ ቢራራ ከአሜሪካ፤ መምህርና ፖለቲከኛ አቶ አበበ አካሉ ከኢትዮጵያ፤ዶክተር ተኽለወይኒ ገብረመድኅን ከጀርመን የምጣኔ ሃብት ባለሙያ፤ እንዲሁም አቶ ግርማ ሠይፉ የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ አባልና በአዲስ አበባ መስተዳደር የውበትና አረንጓዴ ቢሮ ኃላፊ ናቸው። በዚህ ውይይት እንዲሳተፉ ለመንግሥትን ባለሥልጣናት ለጠቅላይ ሚኒስትር ሴክሬታሪያት እንዲሁም ለኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የኢሜይል ግብዣ ልከናል፤ በስልክም ደጋግመን ደውለን ምላሽ እንዳላገኘን መግለጽ እንወዳለን።
ሸዋዬ ለገሠ























