የኦሮሚያው ግጭት ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሻገር
Description
ዓመታትን ያስቆጠረው የትጥቅ ትግል አሁንም ድረስ መቋጫ አላገኘም ። አንዴ ውጥረት እያነገሰ ሌላ ጊዜ ረገብ እያለ የቀጠለው የታጣቂዎች እና የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ አካላት ግጭት ለማህበረሰቡ ሌላ ስጋት ካስከተለ ሰነበተ ። ዕገታ ፤ የዘፈቀደ ግድያ እና ዘረፋ ደግሞ ዋነኞቹ ናቸው ። አልፎ ጂያጅ መንገደኛ ፤ ተራ የየአካባቢው ነዋሪ ብሎም የመንግስት ሹመኛ የዚሁ የጠራራ ፀሐይ የተደራጀ ወንጀል ሰለባ መሆናቸው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ቢሆንም ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ግን ትልቁ ፈተና ሆኗል። መንግስት እና ታጣቂ ቡድኖች ርስ በርስ ይካሰሱበታልና። ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የሚይዘው እና ከትግራይ በቀር ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ጋር የሚዋሰነው የኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እንዲሁ እንደታመሙ ወደ አዲሱ የኢትዮጵያዉያን ዓመት ሊሸጋገሩ ነው።
“ነሐሴ 29 ቀን፣ 2017 ዓ.ም. ንጋት ላይ ሰዎች በተኙበት ገብተውባቸው ቤት ንብረታቸው ጠፍቷል፤ ሰዎችም ተገድለዋል” “በጥቃቱ ከነዋሪው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 19 የደረሰ ሲሆን 11 ሰዎች ደግሞ በአጠቃላይ ቆስለዋል። ”
እነዚህ ድምጾች በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እና ጊዜያት አጋጣሚዎች እየተጠበቁ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች የደረሱ ሰብአዊ ጥፋቶች ናቸው። ከሰሜን እስከ ምስራቅ ሸዋ ፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ወለጋ የሰሞንኛውን ጉዳይ ብቻ እንኳ ብንወስድ አሁንም ድረስ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ ግድያ እና ዕገታ አለመቆሙን ነው። አንዴ ጠንከር አንዴ ረገብ እያለ ዓመታትን በከተሻገረው የኦሮሚያ ክልል የአንዳንድ አካባቢዎች በዚህ ዓመት የከፋ ጊዜ ካሳለፉ አካባቢዎች አንዱ የሰሜን ሸዋ አካባቢ እንደሆነ ነው የሚነገረው። የሀገር ውስጥን ጨምሮ ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጭምር በተደጋጋሚ ድምፆቻቸውን ያሰሙበት እና በርካቶች የታገቱበት ፣ ሕይወታቸውን ያጡበት ፤ የቆሰሉበት ብሎም ሃብታቸውን የተዘረፉበት የደገም ፣ አሊዶሮ፣ እና የጫንጮ አካባቢዎች ተጠቃሾች ናቸው።
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ወይዘሮ እንደሚሉት በአካባቢው ያለው ግጭት መሻሻል ቢኖረውም እገታው ግን አልቀረም ።
«ከበፊቱ ትንሽ የተሻለ አለ፤ ትንሽ መሻሻሎች አሉ ፤ እግዚአብሔር ይመስገን ቢኖርም ታዲያ እነሱ ሰው መውሰዱን አልተውም ። ሰው ይወስዳሉ ፤ ከወሰዱ በኋላ ገንዘብ አምጡ ይሏቸዋል። እኔ እንዲሁ የጥቅማ ጥቅም ጉዲይ ይመስለኛል እንጂ ዕቅድ ያላቸው አይመስለኝም። ነገሩን ስንገምተው ማለት ነው። »
በሰሜን ሸዋ ዞን ቀደም ሲል በጠቀስናቸው እና በሌሎችም አካባቢዎች መነሻቸውን ከአዲስ አበባ አድርገው አካባቢውን አቋርጠው በሚያልፍ ተሽከርካሪዎች ላይ ያነጣጠረ ዕገታ እና ግድያ በተደጋጋሚ መፈጸሙ ተዘግቧል።
እንደ ነዋሪዋ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እየደረሰ ያለው ዕገታ እና የሰብአዊ ጉዳት ከክልሉ ውጭ በሚጓዙ መንገደኞች ላይ ብቻ ያነጣጠረ አይደለም። እርሳቸው «ሽፍቶች» ብለው የጠሯቸው የድርጊቱ ፈጻሚዎች በተራ የአካባቢው ነዋሪ ላይም አስከፊ ጉዳት አድርሰዋል።
« ኸረ በነዋሪም ላይ ነው፤ ነዋሪም ላይ ትንሽ እንዲህ ቅርስ አለው ፣ በልቶ ያድራል ከተባለ ዘመቱበት ሌሊት ፣ በቃ አግተው የሚወስዱትን ሰዎች መረጃ ነው የሚለቅሙት ከእነርሱ ላይ ፤ እንደሚባለው እነርሱም ይጠይቃሉ ። ማን ብር አለው ፣ ማን ምን አለው ፣ ማን ምን ይሰራ ነበር የሚለውን የሚታገተው ሰው መረጃ ይሰጣቸዋል ነው የሚባለው፤ ከዚያ መልስ እንግዲህ መረጃ ካልሰጠ ያው መሞት አለ እነርሱም ደግሞ ሕይወት ነው ፤ ያንን መደበቅ አይችሉም። ትልቁ በሽታ ነው ለሰው መቼ እንደሚስተካከል ፈጣሪ ይወቀው»
እስቲ አሁን ደግሞ ለአንድ አፍታ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ወይም መንግስት ሸኔ ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን እና በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ተደጋጋሚ ግጭት ወደሚያስተናግደው የወለጋ አካባቢ እናቅና ። የቶሌውን ዕልቂት ጨምሮ ብርቱ ሰብአዊ ቀውስ ያስተናገደው የምዕራብ ወለጋ ዞን ዓመታት እንደዋዛ እየተቆጠሩ ትውልድ እስከመሻገር ያደረሰ ያልተቋረጠ ግጭት ሰለባ መሆኑን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪ ሃሳባቸውን ያጋራሉ። መምህር ናቸው ፤ ሄድ መለስ የሚለው ግጭት እርሳቸው ለሚያስተምሯቸው ልጆች እና ወላጆች ብርቱ ፈተና እንደሆነ ነው።
«ትልቅ ተጽዕኖ ነው ያለው ፤ በተለይ በልጆች ላይ ፤ እዚህ እኛ ጋ አሁን ልጆች በትምህርት ቤታቸው ፈተና መፈተን ካቆሙ ወደ አስራ አምስት አመታት ሆናቸዋል ። ወደ ከተማ እየሄዱ ነው የሚፈተኑት ። ልጆቹ ከከተማ ጋር አይተዋወቁም ፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የስድስተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ፈተና እንዲፈተኑ እየተደረገ ነው። ይህ ደግሞ ቤት ተከራይቶ እና ወጪአቸውን ሸፍኖ ለማቆየት ቤተሰብ ስቃዩን እያየ ነው።»
እንደመምህሩ ይህ ፈተና በትምህርት ላይ በደረሰ ጉዳት ብቻ አይመዘንም ። ብርቱ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳት አስከትሏል።
«የመጓጓዣ ነገር ካየህ በአሁኑ ጊዜ ልቅ ነው ። መምህራን ደግሞ ይህንን መክፈል አይችሉም። ለዚህ ያለን ምርጫ በእግር መጓዝ ብቻ ነው። »
የፀጥታ መደፍረስ በክልሉ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች እና የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች አማካኝነት ከሚደርሱ ጉዳቶች ባሻገር ከአጎራባች ክልል በመጡ ታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ማባባሳቸውን የአስተዳደር አካላት ጭምር ማረጋገጫ ይሰጣሉ ። የአቤ ደንጎሮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ከተማ ዋቁማ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ይህኑ አጠናክረዋል።
‹‹ መሰል ጥቃቶችን ለመካከል ቀበሌዎች እየተደራጀ ነው፣ ምሊሻም በየቀበሌው እየተደረጀና እየታጠቀ ነው፤ በየአካባቢው የመከላከያ ሰራዊትም ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ደን በብዛት በአካቢው መገኘቱን እነዚህ ኃይሎች ለዝርፍና ግድያ ይጠቀሙበታል፡፡ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን ይወስዳሉ ይዘርፋሉ፡፡ ››
ይህ አስከፊ ሰብአዊ ጥሰት የኃይማኖት አባቶችን እስከ መግደል ያደረሰም ነበር።
በዓመቱ በክልሉ በታጣቂዎች እና በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መካከል በሚደረጉ ግጭቶች ከሚፈጠሩ ሰብአዊ እና ማህበራዊ ጉዳቶች ባሻገር የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች በሚጋሯት የሞያሌ ከተማ የተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ አንደኛው ነበር ። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት የሞያሌ ከተማ የይገባኛል ጥያቄ ሦስት ዐሥርተ ዓመታት ያስቆጠረ ነው።
«ችግሩ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሳይፈታ የመጣ ነው። የድንበር ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን እስካሁንም ድረስ ሳይፈታ ነው የቆየው ። ጥግሩ የሽግግር መንግስቱ ከተቋቋመበት ወቅት አንስቶ ከተማዋ አንዳች ዕልባት ሳይበጅላት ነው የዘለቅችው። የኦሮሚያ ክልል የኔ ይላል ፤ የሶማሌ ክልልም የኔ ነው ይላል። አሁን ደግሞ የድንበሩ ችግር አድሮ አዲስ መዋቅር አዘጋጀን ብለው ተግባራዊ ለማድረግ ሲሞክሩ ነው ህዝቡ ለተቃዉሞ አደባባይ የወጣው። »
በሁለቱ ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች «ለሰዎች እገታ እና ሞት ምክንያት የሆኑ ግጭቶች» እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆነው ኹነቱ በመጨረሻም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጣልቃ እንዲገባ ጋብዞ ለጊዜውም ቢሆን መረጋጋቱን እኚሁ ነዋሪ ይናገራሉ።
«በታጣቂዎች በኩል አሁን ተረጋግቷል፤ ችግር የለም። ኢትዮጵያ እና ኬንያ ተቀናጅተው ኦፕሬሽን ካደረጉ ወዲህ አሁን ተረጋግቷል። »
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በየአጋጣሚው የሚቀሰቀሱ ጥቃቶችን ለማስቆም ለምን እንዳልተቻለ የክልሉ ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የሆኑትን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳን ለቃለ ምልልስ ጋብዘን ነበር ። ነገር ግን ኮሚሽነሩ በስልክ ልናናግራቸው ቀጠሮ ከሰጡን በኋላ በተደጋጋሚ በስልክ መስመራቸው ላይ ብንደውልላቸውም ልናገኛቸው አልቻልንም ።
የሰሜን ሸዋ ነዋሪዋ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ግን የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢያቸው ጸጥታ ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከሞላ ጎደል አገልግሎት እየሰጡ ነው።
«እነርሱ ይሰራሉ፤ አሁን የመከላከያ ሰራዊት ገብቶ እየጠበቀ ይሰራሉ ። ትምህርት ቤትም እየተማማረ ነው ፤ ጤና ጣቢያዉም ምኑም ምኑም ይሰራል ። መከላከያው እየተንገላታ እየወጡ እየወረዱ አስፋልቱ ላይ እየዞሩ እየጠበቁ ነው የሚሰራው »
ዶ/ር ደረጀ ታምሩ ነዋሪነታቸው እዚሁ ጀርመን ሲሆን የኦሮሚያን የጸጥታ ሁኔታ በቅርበት ይከታተላሉ ። እርሳቸው ተወልደው ባደጉበት የሰሜን ሸዋ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ጨምሮ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ሄድ መለስ የሚለው እና የቀጠለው ግጭት እና በሲቪሊያውያን ላይ የሚደርሰውን ሰብአዊ ጉዳት መፍትሄ ማጣት ምክንያት ነው ያሉትን እንዲህ ይገልጻሉ
“እንደኔ ይኽ ለምን ቀጠለ ብዬ ሳስበው የመንግስት ድክመት ነው ብዬ ነው የማምነው ፤ ምክንያቱም የመጀመሪያው የመንግስት ቁጥር አንድ ስራው መሆን የነበረበት ህዝቡን ከውስጣዊ እና ዉጫዊ ስጋት መጠበቅ ነው። እና መንግስት ይህን ማድረግ አልቻለም። አንዳንዴ ይህ ለምንድነው ያልሆነው ብሎ ያስጠይቃል ግን መንግስት ኃላፊነቱን መወጣት አለመቻሉ እንዲቀጥል እና እንዲባባስ አድርጓል። “
በርግጥ ነው ፤ ፖለቲካዊ ይዘትን ጨምሮ በነዋሪዎች የተገለጹ የሽፍትነት ተግባራትን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ሁለንተናዊ ጉዳቶች ምክንያታቸው ብዙ ሊሆን ይችላል። በዚህ ሂደት ግን እንደሀገር የመጣበትን የኑሮ ውድነት ጨምሮ የጸጥታ መደፍረሱ ገፈት ቀማሹ ሲቪሉ ማህበረሰብ ነው፤ ። የሰሜን ሸዋዋ ነዋሪዋ በሰጡት አስተያየታቸው ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው። በሁለት ኃይሎች መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የሚኖር ህዝብ የሚያደርገው ግራ ሆኖበታል።።
«ህብረተሰቡማ ምን ሊያደርግ ይችላል? ህብረተሰቡኮ አንድ ሰው የሆነ ጥቆማ ቢሰጥ ወይ ልጁ ወይ እርሱ መሞቱ ነው። ሞት ነው የሚጠብቀው። ስለዚህ አሁን ለመንግስትምኮ ሰው ጥቆማ ቢሰጥ እና ከመንግስት ጎን ቢቆም በትክክለኛ እንደሚረጋጋ ነው ። ያንን ለማድረግ ሰው ለሕይወቱ ይፈራል ፤ ታጣቂ ራሱ መንግስት አምኖ ያሰማራቸው ራሳቸው የእምነታቸውን አይሰሩም፤ ይፈራሉ»
እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽናልእና የሰብአዊ ተመልካቹ ሁማን ራይትስ ዋች አይነት ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተመልካች ተቋማት በክልሉ ግጭት በተስፋፋባቸው እና ለበርካቶች ሞት ምክንያት ለሆኑ ጥቃቶች የመንግስት እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን ይከሳሉ ።
ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹ በተናጥል ጥቃቶች ከሚፈጸሙ የጅምላ ግድያ ባሻገር የጅምላ አፈሳ እና መንደሮች መቃጠላቸውን በጎርጎርሳዉያኑ 2023 ያወጧቸውን ሪፖርቶች ያስታውሳሉ ። እነዚህ ሁነቶች የሰሞንኛ የአቤ ደንጎሮ እና ምስራቅ ሸዋ የታጣቂዎች ጥቃት ሪፖርቶች ለሰብአዊ ቀውሱ መቀጠል እና አሁንም ድረስ ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት ላለማቻሉ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
አሮጌ ዓመት አልፎ በአዲስ ሲተካ ፤ ሁሉም አዲስ ተስፋ፣ ያለፈው አስከፊ ጊዜ እንዳይመለስ ሆኖ እንዲያልፍ መመኘቱ አይቀርም ። በዚህ ሂደት ቀዳሚው ሃገራዊ ሰላም እና መረጋጋት መስፈን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቀዳሚ መሻት መሆኑ ባይካድም ለዚህ መንደርደሪያው ግን እንደየአካባቢው ችግር መፍትሄ መሻቱ ላይ ሊተኮር እንደሚገባ ነው ማሳሰቢያ የሚቀርበው ። የምዕራብ ወለጋው መምህር እንደሚሉት መንግስት ለህዝብ ሃሳብ ጆሮ መስጠት ቀዳሚ ጉዳይ ቢያደርገው ባይ ናቸው ።
«መፍትሄው የሚሆነው ከህዝብ ላይ ሃሳብ ቢቀበሉ ነበር መፍትሔ የሚሆነው። ስላለው ችግር ህዝቡን አነጋግረው ለመፍትሄው የሚሆን ሃሳብ ቢወስዱ መልካም ነበር ። ብዙ ጊዜ ከላይ የሚመጡት የሚያደርጉት ከመንስት ባለስልጣናት ብቻ አስተያየት አሰባስበው የሚመለሱት ። ችግር እየደረሰበት ያለውን ህዝብ በቀጥታ ቢያናግሩ ለሁሉ ችግር መፍትሄ ገኝ የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ ነበር። በአሁኑ አካሄድ መፍትሄ አይኖርም»
ዶ/ር ደረጀ በበኩላቸው ለዘላቂ መፍትሔየመንግስትን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ እና ለጥያቄዎች መልስ መስጠት ላይ ያተኮረ መሆን አለበት ባይ ናቸው።
« አንደኛ የፖለቲካ ጥያቄ ላለው አካል ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት ይኖርበታል መንግስት ፤ እንዲሁም ከዚህ የዘለለ የፖለቲካ ጥያቄ የሌለው ግን ደግሞ የህብረተሰቡን ሰላም የሚረብሽውን ደግሞ መንግስት ህብረተሰቡን የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት ህግ ማስከበር አለበት ማለት ነው። »
በክልሉ በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ እና ቀላል ቁጥር የማይሰጣቸው ታጣቂዎች በተለያዩ ጊዜያት በሰላም መመለሳቸው ሲነገር ቆይቷል። ከእነዚህ ውስጥ በምዕራብ ፤ ሰሜን እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ፤ በወለጋ አካባቢዎች በቅርቡ ደግሞ ቦረና አካባቢ ይንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች መመለሳቸውን የመንግስት የመገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ ቆይተዋል። ምንም እንኳ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን ተመላሽ ታጣቂዎች የርሱ ታጣቂዎች መሆናቸውን ማረጋገጫ ባይሰጥም።
ህዝቡ ግን የማያቋርጥ ፤ ምናልባትም ተመሳሳይ ጥያቄ ያነሳል ። ሰላም እና መረጋጋት ይመጣ ዘንድ ሁሉም ለሰላም ይሸነፍ ዘንድ ጥሪውን ያቀርባል።
«በዚህ አያያዝ ሰላም ይሰፍናል፤ ለችግሮችም መፍትሔ ይመጣል የሚል ተስፋ የለኝም። ይሄም ትቶ ያም ትቶ ወደ ሰላም ካልተኬደ በቀር እና ሁሉም የኔ የኔ የሚል ከሆነ መፍትሄ አያገኝም ። እየባሰበት ይሄድ ካልሆነ በቀር ። ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነት ነው ያመጣብን ። አለመረጋጋት ነው ያመጣብን ። አሁን ባለንበት ሁኔታ መኖር በማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። »
አዎ 2017 አሮጌ ዓመት ተብሎ አዲሱን የ2018 ልቀበል ከደጅ ደርሰናል። ነገር ግን አዲስ ዓመት አዲስ የሚሆነው ሰላም ባለበት ሀገር ነውና ፤ የአውድ ዓመት ድባብ የሚሰፍነው ዜጎች በአዲስ ዓመት አዲስ ነገር ለመያዝ ተስፋ ሲያደርጉ ነውና ፤ አዲሱን ዓመት ዓዲስ ለማድረግ መንግስት እና ታጣቂዎች ቢያንስ በሮቻቸውን ለመነጋገር እና ለመደራደር ዝግጁ ቢያደርጉ ምንኛ መልካም በሆነ
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ























