DiscoverDW | Amharic - News“ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው። ከዚያ በኋላ እዬዬ አይሠራም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
“ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው። ከዚያ በኋላ እዬዬ አይሠራም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

“ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው። ከዚያ በኋላ እዬዬ አይሠራም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

Update: 2025-10-28
Share

Description

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል ወደብ እንድታገኝ “እባካችሁን ሸምግሉን እና መፍትሔ አምጡልን” የሚል ጥያቄ ለአሜሪካ፣ ቻይና ሩሲያ፣ አውሮፓ እና የአፍሪካ ሀገራት ማቅረባቸውን ተናግረዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል ወደብ የማግኘቷን ጉዳይ “አይቀሬ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አዎ እንሸመግልላችኋለን ሰላም ያስፈልጋል እያሉ ማዘናጋት ከሆነ ግን ጉዳዩ ብዙ የሚሔድ አይመስለኝም” ሲሉ ተደምጠዋል።



ዐቢይ “የቀይ ባሕር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው” የሚል ሙግታቸውን በድጋሚ አቅርበዋል። ሀገሪቱ ከቀይ ባሕር ገሸሽ የተደረገችው “በ30 ዓመት ትግል፤ በብዙዎች ርብርብ” እንደሆነ የገለጹት ዐቢይ የወደብ ባለቤትነቷን ለማስመለስ “ሌላ 30 ዓመት ያስፈልጋታል” የሚል ዕምነት የላቸውም።



መንግሥታቸው የወደብ ጥያቄውን ለኤርትራ አቅርቦ እንደነበር ለምክር ቤቱ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በግልጽ ባላወቅንው መንገድ ለዚያ ጉዳይ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ አልነበሩም” ሲሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የአሰብ ወደብን ለመጠቀም አገናኝ መንገዶችን ጠግኖ “ከጋራ ወዳጅ ሀገር ጀሬተር እና ክሬን በዕርዳታ ወደ ኤርትራ እንዲመጣ” ቢያደርግም “አሰብ ወደብ ሲደርስ የኤርትራ መንግሥት አልፈልግም ብሎ መለሰ” ሲሉ ተደምጠዋል።



ይሁንና የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት የሻከረው ፌደራል መንግሥት እና ህወሓት በጥቅምት 2015 በፕሪቶሪያ ከተፈራረሙት ግጭት የማቆም ሥምምነት በኋላ እንደሆነ የተናገሩት ዐቢይ ሦስት ክልሎች ያዳረሰው ጦርነት “ለምን ይቆማል? ትክክል አይደለም” የሚል ተቃውሞ ከአስመራ እንደቀረበ ተናግረዋል።



የኤርትራ መንግሥት “ህወሓት እና ትግራይ ተጠቅለው ካልጠፉ” የሚል አቋም ነበረው ያሉት ዐቢይ “በዚህ በኩል ሲያቅታቸው አሁን በዚያ በኩል ጀመሩ” በማለት በኢትዮጵያ ግጭቶች ውስጥ እጃቸው አለበት የሚል ክስ አቅርበዋል።



“ኤርትራውያን ወንድሞቻችን ናቸው። ከእነሱ ጋር ውጊያ አንፈልግም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሚመሩት የኤርትራ መንግሥት “ጥይት አስተላላፊ አትሁኑ። ሀገር ሁኑ፤ ወደ ጎረቤት ሀገር ጥይት ማስተላለፍ ጥሩ አይደለም” የሚል ክስ ያዘለ መልዕክት አስተላልፈዋል።



“ዐባይም ጸባይ ገዝቷል፤ የእኛም ሽፍቶች ጸባይ ይገዛሉ። አንድ ቀን ጥይት ሳመላልስ ብሎ ታሪክ ስለሚናገረው፤ ጥይት ማቀባበል ቢቀርባችሁ” ሲሉ የተደመጡት የኢትዮጵያ መሪ “ስለማናውቅ አይደለም እናያችኋለን” ሲሉ ተደምጠዋል። “ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ቢቀር፤ የሚመጣ ሰው ካለ በሕጋዊ መንገድ ቢመጣ፤ ሕገ-ወጥ ንግድ ቢቀር፤ ፎርጅድ ብር ቢቀር፤ አሜሪካ አስቀምጣችሁ የምትሠሯቸው ጥቁር ገበያ ማሳደግ ቢቀር” የሚሉ ውንጀላ የተጫናቸው ጥሪዎች አስተላልፈዋል።



በምክር ቤቱ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ እና የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ባነሷቸው ጥያቄዎች የሻከረው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ከፍ ያለ ቦታ ይዞ ታይቷል። አቶ ጫላ ለሚ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል “አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የህወሓቱ የአዛውንቶች ቡድን ከሻዕቢያ ኃይሎች ጋር ግንባር ፈጥረው ለጥፋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ይሰማል” ሲሉ ተደምጠዋል።



“ሉዓላዊነታችንን የሚዳፈር የሻዕቢያ እንቅስቃሴ ለመፍታት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች እና በአጠቃላይ አሁናዊ የትግራይ ክልል የሰላም፣ የጸጥታ እና የፖለቲካ ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማብራሪያ ቢሰጡ” በማለት የግዥው ብልጽግና ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ጫላ ጠይቀዋል።



የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ የሆኑት የምክር ቤት አባል ደሳለኝ ጫኔ በወደብ ጉዳይ ምክንያት “ከኤርትራ ጋር የጦርነት ዋዜማ ላይ የምንገኝ ይመስለኛል” ሲሉ ሥጋታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በሁለቱም ሃገራት “የተሟላ የጦርነት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ” ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “ሥጋት” እንደገባው ያነሱት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ “የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ከፍተኛ መካረር ውስጥ እንደገባ ግልጽ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።



“ሁላችንም ካለፈው ጥፋቶቻችን ለምን አንማርም? እንደ ሀገር ስንት ትውልድ በጦርነት እየበላን እንቀጥላለን?” በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ያቀረቡት ዶክተር ደሳለኝ “ከትግራይ ኃይሎች፣ ከፋኖ እና ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር መንግሥትዎ የገባበትን ሁኔታ በአርቆ አስተዋይነት እና በድርድር እንዲፈታ፤ የባሕር በር ጉዳይንም አስመልክቶ ከኤርትራ ጋር የገባንበትን እሰጥ አገባ በሰላማዊ ሕጋዊ እና ሰጥቶ መቀበልን መሠረት ባደረገ አካሔድ ብቻ እንዲፈታ” ጠይቀዋል።



ለምክር ቤት አባላቱ በሰጡት ማብራሪያ “ከማንም ጋር የመዋጋት ፍላጎት የለንም” ያሉት ዐቢይ “ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው። ከዚያ በኋላ እዬ ዬ አይሠራም” በማለት አስጠንቅቀዋል። በውጊያ “እንትና ያግዘኛል እንትና ያግዘኛል” ብሎ መተማመን እንደማይቻል ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ልማት ነው የምንፈልገው፤ ሰላም ነው የምንፈልገው፤ ከማንም ጋር ግጭት ለማድረግ ፍላጎት የለንም” በማለት እንደ ከዚህ ቀደሙ ማስተማመኛ ለመስጠት ሞክረዋል። ውጊያ ውስጥ “ከገባን ግን ግልጽ ነው ውጤቱ፤ አስተማማኝ አቅም ነው ያለን፤ ማንም አያቆመንም” ሲሉ ተደምጠዋል።



የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት የተፈራረሙት ግጭት የማቆም ሥምምነት “መሣሪያ መደበቅ” እና ታጣቂዎች “ማሰልጠን እና ማስመረቅን” እንደማይጨምር ገልጸው ተችተዋል። የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ከሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሚገባቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ትግራይ ክልል ተጨማሪ ውጊያ አያስፈልግም። ትግራይ የሚደረግ ውጊያ ዓላማ የለውም” ሲሉ የመንግሥታቸውን ፍላጎት አስረድተዋል።



“ህወሓትም በሰከነ መንገድ ምርጫ ቦርድን አክብሮ፤ ሕገ-መንግሥት አክብሮ፤ ትክክለኛ ጉባኤ አድርጎ ሕጋዊ ፓርቲ መሆን ነው የሚጠበቅበት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ብትዋጉም አታሸንፉም፤ አይታችሁታል፤ ጥቅም የለውም” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።



ዐቢይ በአማራ ክልል ከፋኖ ታጣቂዎች፤ በኦሮሚያ ክልል ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር ስለሚደረጉ ውጊያዎች ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች “ተወያይቶ የመጣውን ተቀብለናል” ይበሉ እንጂ “ተላላኪ ናቸው። ዓላማ የላቸውም” ሲሉ አጣጥለዋል።



ታጣቂዎቹ “ታገልኩለት የሚሉትን ሕዝብ እየገደሉ፤ ልማት እያደናቀፉ፤ ማዳበሪያ እንዳይሔድ እያደረጉ” እንደሆነ የገለጹት ዐቢይ “ማንም ሰው በሰላማዊ መንገድ ሕግ እና ሥርዓት አክብሮ የሚመጣ ከሆነ ለመታረቅ አይደለም አብረን ለመሥራት ዝግጁ ነን” ሲሉ ተናግረዋል።



አርታዒ ሸዋዬ ለገሰ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

“ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው። ከዚያ በኋላ እዬዬ አይሠራም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

“ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው። ከዚያ በኋላ እዬዬ አይሠራም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

Eshete Bekele