በዐማራ ክልል ይፈጸማል የተባለ ጥቃትና ኢሰብአዊ ድርጊት በገለተኛ አካል እንዲጣራ ተጠየቀ
Description
በዐማራ ክልል በንጹሐን ዜጎች ላይ ይፈጸማል ያለውን ጥቃትና ኢሰብአዊ ድርጊት ለማጣራት፣ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም፣ የዓለም ዓቀፍ የዐማራ ዲያስፖራ ዲፕሎማሲ ግብረ ኃይል ጥሪ አቀረበ። ግብረ ኃይሉ ሰሞኑን ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፦ በጉዳዩ ላይ ዓለም አቀፍ ተጠያቂነት ለማምጣት እንዲሠራም ጥሪ አስተላልፏል ። ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው አንድ የፓለቲካ ተንታኝ፣ በዐማራ ክልል የሚካሄደው የትጥቅ ትግል በዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ የሚታወቅ በመሆኑ፣ የሚጣራ ነገር የለውም ብለዋል ።
የዓለም አቀፍ ዐማራ ዲያስፖራ ዲፕሎማሲ ግብረ ኃይል ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ሽፈራው ገሰሰ፣ ግብረ ኃይሉ በውጭ ያለውን የዐማራ ማኀበረሰብ ጥያቄ በተቀናጀ መልኩ ለማቅረብ በቅርቡ የተቋቋመ መሆኑን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።
የዐማራ ዲያስፖራ ዲፕሎማሲ
''ይኼ የዐማራው ድምፅ ሊሆን የሚችል፣ የዐማራ ዲፕሎማሲ፣ዲያስፖራውን በሙሉ በአንድ ድምፅ ሊያቀርብለት የሚችል አወቃቀር ያስፈልጋል በሚል ብዙ ከተነጋገርንበት በኋላ፣ብዙ አለም ዓቀፍ ማኀበራት ታዋቂ ሰዎች ስብሰባ፣ ይህ የዐለም አቀፍ የዐማራ ዲያስፖራ ዲፕሎማሲ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል። '' ይኸው ግብረ ኃይል ለመጀመሪያ ጊዜ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫም፣የተለያዩ ወቅታዊ ጥያቄዎችን ለዓለሙ ማኀበረሰብ አቅርቧል ብለዋል ዶክተር ሽፈራው። ''
''ገለልተኛ የሆነ የሚያጣራ ቡድን እንዲቋቋም እና ጉዳዩን እንዲያጣራ» ጠይቀዋል ። የድሮን ጥቃትም ሆነ ይፈጸማል ያሉት «ኢሰብአዊ ድርጊት» እንዲቆም ጠይቀዋል። እንደዚሁም ደግሞ ዓለም አቀፍ ተጠያቂነት እንዲመጣ በዚህም ዙሪያ እንዲሠራ ጥያቄ አቅርቧል። ይህንን የድሮን ጭፍጨፋ በንፁዓን ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን፣ የዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ እንዲያወግዝ ጥያቄ አቅርቧል። ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ባለመከታተል ብዙ ጥፋት እየደረሰ ስለሆነ፣ የዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በደንብ ተገንዝቦ ይሄንን ነገር ከዚህ በፊትም እንደገለጽነው፣በፊት በተደረገው የሰሜኑ ጦርነት ጊዜ የድሮን ጥቃትም ሆነ ሌሎችም በከፍተኛ ደረጃ፣እስከ ፀጥታው ምክር ቤት ድረስ በከፍተኛ ደረጃ በተከታታይ ይመለከቱት እንደነበር እናስታውሳለን። ይህንን ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል። ግን እኛም በርትተን ሰብሰብ ብለን ጥያቄዎችን ማቅረብ አለብን፣ግፊት ማድረግ አለብን። በእዛ ረገድ ለውጥ ሊመጣና በደንብ ትኩረት ሰጥተው በዐማራው ላይ እየደረሰ ያለውን፣በደልና ግፍ ትኩረት ሰጥተው፣ወደ መፍትሄ ሊያመጣ የሚያስችል የዲፕሎማሲ ስራ ይሠራል ብለን እናምናለን። ''
የዓለም አቀፍ የዐማራ ኅብረት አቤቱታ
በተመሳሳይ ሁኔታ፣ዓለም አቀፍ የዐማራ ኅብረት፣ በዐማራ ክልል እየተባባሰ ነው ባለው ሰብአዊ ቀውስ ጥልቅ ስጋት እንደገባው፣ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ባስገባው አስቸኳይ የአቤቱታ ደብዳቤ አመልክቷል። ''
ኅብረቱ አቤቱታውን ያቀረበው፣ ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ ጄኔቭ-ሲዊዘርላንድ ለሚገኘው የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት፣ለአውሮጳ ኅብረት፣ለአፍሪቃ ኅብረት ሰብአዊ መብቶች ዳይሬክቶሬት፣ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ለሂውማን ራይትስ ዎችና ለለምኪን የዘር ማጥፋት መከላከል ተቋም ነው። የኅብረቱ የአቤቱታ ደብዳቤ፣ በቅርብ ጊዜ በዐማራ ክልል የተከሰሱት ሁኔታዎች፣ ከባድ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ጥሰቶችን ያሳያል ሲል ገልጿል።
የፓለቲካ ተንታኝ አስተያየት
በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ዶቼ ቬለ የጠየቃቸው የፓለቲካ ተንታኝ አቶ አዱኛ ፈይሳ፣የዐማራ ክልል በግልጽ የትጥቅ ትግል የሚካሄድበት በመሆኑ ገለልተኛ አካል ገብቶ የሚያጣራው ነገር የለውም ይላሉ።
''ገለልተኛ አካል ያጣራው የሚለው፣ገለልተኝነት ጠይቀናል የአንድ ወገን አይደለንም የሚለውን ለማሳየት የሚደረግ ሸፋን ካልሆነ በስተቀር፣ምንም ገለልተኛ ወገን ገብቶ ሊያጠራው የሚጠይቅም ነገርም የለም። በትጥቅ ሥልጣንን ለመቆጣጠር፣የመንግስትን ኃይል ለመምታት ተደርጎ የነበረው ጥረት፣ዓለም አቀፍ ማኀበረሰብ የሚያውቀው በደንብ የተዘገበ፣ እነሱም ራሳቸው በአደባባይ የተናገሩት ነው። ጋሽናን ለመያዝ ሌሎች ቦታዎችን ለመያዝ ተንቀሳቅሰን ተሳካልን፣የመንግስት ሰራዊትን ማረክን የሚለው እንዳለ ሆኖ፣እዛ ቦታ ላይ የደረሰው ጥቃት ደግሞ ማኀበረሰብ ላይ ነው ማለት፣ እርስ በእርሱ ስለሚጣረስ፣ገለልተኝነትን የጠየቁበት መንገድ፣ ራስን ገለልተኛ አስመስሎ ለመሳል ከሚደረግ ጥረት አንፃር እንጂ፣ብዙ የሚጣራ ነገር ኖሮ አይደለም ብዬ ነው የማምነው። ''
እንደ ፖለቲካ ተንታኙ አስተያየት፣የመግለጫዎቹ መንፈስ መግጫዎችን ያወጡት አካላት፣ ዐማራ ክልል ውስጥ ነፍጥ ያነሳ ካሉት ኃይል ጋር ተናበውው እንደሚሰሩ የሚያመለክት ነው። ''እነኚህ ዐይነት መግለጫዎች፣ራሳቸውን ከፖለቲካ ተሳትፎ ነጻ አድርገው ለማሳየት የሚሞክሩበት መንገድ፣እንደሚታየው፣ሙሉ ከአንድ የፖለቲካ እሳቤ፣መሬት አገር ውስጥ ዐማራ ክልል ላይ ነፍጥ አንግቦ ከሚንቀሳቀሰው አካል ጋር በትርክትም፣ በንግግርም፣በትስስርም አንድ እንደሆነ የሚያሳይ መግለጫ ነው። ''
በተነሱት ጉዳዮች ላይ ዋሺንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተያየት ለማግኘት ጥረት ብናደርግም ለጊዜው ምላሻቸውን አላገኘንም።
ታሪኩ ኃይሉ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ

























