DiscoverDW | Amharic - Newsበሰውሰራሽ አስተውሎት የሚሰሩ ሀሰተኛ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን እንዴት እንለይ?
በሰውሰራሽ አስተውሎት የሚሰሩ ሀሰተኛ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን እንዴት እንለይ?

በሰውሰራሽ አስተውሎት የሚሰሩ ሀሰተኛ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን እንዴት እንለይ?

Update: 2025-10-29
Share

Description

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በሰዎች የሚከወኑ ሥራዎችን ማሽን ተክቶ እንዲሠራ በማድረግ በዓለማችን ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው። የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በውስጡ ከያዛቸው ዘርፎች አንዱ የሆነው ጀነሬቲቭ ኤአይ /Generative AI /በአሁኑ ጊዜ እንደ ንግድ እና ሳይንስ ባሉ የፈጠራ ዘርፎች ውስጥ ቴክኖሎጂው በርካታ ጥቅሞችን እየሰጠ ይገኛል። የሳይበር እና የሰውሠራሽ አስተውሎት ደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ባለሙያው ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ፤ እንደሚለው መደበኛው የሰውሠራሽ አስተውሎት ከ1950ቹ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ይሰጥ የነበረ ሲሆን ጄነሬቲቭ ኤአይአዲስ ይዘት የመፍጠር አቅምን አሳድጓል።



ያም ሆኖ ጄነሬቲቭ ኤአይ ሀሰተኛ ክስተቶች እውነተኛ እንዲመስሉ አድርጎ በመሥራት ጠቃሚ ያልሆኑ ይዘቶችንም ለመፍጠር ያገለግላል።በተለይ ዲፕ ፌክ የሚባለው ዘዴ ሰዎች ያልተናገሩትን አስመስለው የሚናገሩ፣ ያላደረጉትን ድርጊት የሚፈጽሙ ነገር ግን እውነተኛ የሚመስሉ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን ለመፍጠር ይውላል። አንዳንዶች ታዲያ ይህን የቴክኖሎጂ ውጤት ላልተገባ ዓላማ በመጠቀም እውነት የሚመስሉ ይዘቶችን በማሰራጨት በርካቶችን እያሳሳቱ ይገኛሉ። ተመራማሪዎች እንዲህ ዓይነቱ ይዘት ሀሰተኛ ዜናን በማስራጨት፣ የሰዎችን መልካም ስም በማጉደፍ ፣ በምርጫ ጣልቃ በመግባት እንዲሁም ማኅበራዊ አለመረጋጋትን በመፍጠር ከፍተኛ አደጋዎችን እንደሚያስከትል ያስጠነቅቃሉ። ቴክኖሎጂው ፈጠራን በማቀጨጭ እንዲሁም የሰዎችን ሥራ በመተካት ሥራ አጥነት እንዲጨምር ያደርጋል። አበበ በበኩሉ ቴክኖሎጂው ከዚህ ቀደም ከነበሩት በተለዬ ሁኔታ የተሳሳተ መረጃ በማቅረብ እንዲሁም የማጭበርበር ወንጀሎች እንዲፈፀም መንገድ የሚከፍት ነው ይላል። የሰው ሠራሽ አስተውሎትውጤት የሆኑ ይዘቶች፤ ሰዎች ጄኔሬቲቭ ኤአይ /generative AI/ ወደሚባሉ ድረ-ገጾች በመሄድ በጽሑፍ ትዕዛዝ በመሰጠት የተፈለገውን ዓይነት የምስል እና የቪዲዮ ይዘት በቀላሉ የሚያገኙበት ነው። ቴክኖሎጂው ምስሎች እና ቪዲዮዎችን የሚፈጥረው ደግሞ «ማሽን ለርኒንግ» በሚባለው ሂደት በተሰጠው የውሂብ ክምችት ላይ ተመስርቶ ነው። ከዚህ አኳያ መረጃው በዘር፣ በፆታ ፣ በሃይማኖት ወይም በሌሎች ጉዳዮች አድሏዊ እና ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ የተሰበሰበ ከሆነ ቴክኖሎጅው ይህንኑ ችግር መድገም የሚችል መሆኑም ሌላው እና ሦስተኛው አሉታዊ ጎን መሆኑን ባለሙያው ያስረዳል።የፈጠራ ሥራን ማቀጨጭ እንዲሁም የፈጠራ መብት ባለቤትነትን ማሳጣትም ቴክኖሎጅው ይዞት የመጣው ሌላው ችግር ነው።



የችግሩ አባባሽ ምክንያቶች



ይህ ቴክኖሎጂ ይዞት የመጣውን አደጋ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ እነዚህ ሥራዎች ለእውነታ እጅግ የቀረቡ በመሆናቸው የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት ከሆኑት እውነተኛ ሥራዎች ለመለየት አስቸጋሪ መሆኑ ነው።በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአብዛኛው ሰዎች እውነተኛ ፎቶዎችን፣ ድምፆችን እና ቢዲዮዎችን በሰውሠራሽ አስተውሎት ከተፈጠሩት ለመለየት እና በውል ለመረዳት ይቸገራሉ።በዚያ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በጄነሬቲቭ ኤአይ በሚባለው የሰውሠራሽ አስተውሎት በተፈጠሩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ግራ ይጋባሉ። በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ የሚሰራጩ የሰውሠራሽ አስተውሎት የሚፈጠሩ ሀሰተኛ ይዘቶች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የቴክኖሎጂ እውቀት ባልዳበረባቸው አዳጊ ሃገራት የጥላቻ የግጭት እና የመከፋፈል ምክንያት እየሆኑ ነው።

በዚህ ሁኔታ አንዳንዶች ለገንዘብ ጥቅም ወይም ለፖለቲካዊ ትርፍ አልያም ለበቀል ሲሉ በሰውሠራሽ አስተውሎት የተሰሩ ይዘቶችን በመጠቀም ሰዎችን ሆነ ብለው ሲያሳስቱ ይታያል።

በኢትዮጵያም ሐሰተኛ ዜናዎችን ሆነ ብሎ ለማሰራጨት በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተዘጋጁ ምሥሎችን እና ቪዲዮዎችን እንደ ፌስቡክ ቲክቶክ እና ቴሌግራም በመሳሰሉት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ማጋራት በስፋት ይስተዋላል። በዚህም በርካቶች ገንዘባቸውን ተጭበርብረዋል ሌሎች ደግሞ መልካም ስማቸው ጠልሽቷል። በየዕለቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ውስብስብ እየሆኑ በመጡበት ባለንበት ዓለም እንዲህ ዓይነት ይዘቶችን የቴክኖሎጂ ፈጠራ መሆናቸውን መለየት ቀላል ባይሆንም፤ የሳይበር እና የሰውሠራሽ አስተውሎት ደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ባለሙያው ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ፤ እንደሚለው እነዚህን ይዘቶች ከእውነተኛው ለመለየት የሚረዱ ለተጠቃሚዎች አንዳንድ ተግባራዊ ምክሮች አሉ።



ከነዚህም መካከል ይዘቱ ሌላ ቦታ ወይም ከታማኝ ምንጭ በይፋ የተሰራጨ መሆኑን ማረጋገጥ፡ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ መብራቶች ወይም ጥላዎች፣ ከምስሉ ወይም ከቪዲዮው ጋር የማይዛመዱ ነጸብራቆች ለምሳሌ በዓይን አካባቢ የሚታዩ ጉድለቶች እንዲሁም ሙሉ ያልሆኑ የሰውነት ክፍሎች ወይም ከተለመደው ወጣ ያለ የሰውነት ቅርፅ እና እንቅስቃሴዎችም ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ናቸው።አንዳንድ ጊዜም በዚህ ቴክኖሎጂ የተሰሩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች የተለመደው የውሂብ እና የመረጃ ታሪክ ይጎድላቸዋል። ወይም ያልተለመደ የአርትዖት ታሪክ ይኖራቸዋል።በሰውሠራሽ አስተውሎት የተሰራ ይዘት ላይ መለያ ወይም ምልክት ማድረግ በመጀመሩ እሱን ማረጋገጥ ጠቃሚ መሆኑን አስረድቷል። በሰፈው የተሰራጩ ወይም «ቫይራል» ክሊፖችን በተለይም ጠንካራ ስሜትን የሚቀሰቅሱ እና ታማኝ ካልሆኑ ምንጮች የሚደርሱትን መጠራጠርና እና መመርመር ይመከራል።ይዘቱን ከሌሎች የመረጃ ምንጮች ማመሳከርም ሀሰተኛ ይዘትን ለመለየት ይረዳል።



ለመለየት በጣም አስቸጋሪ የሆነው ለምንድነው?



በዚህ ሁኔታ ባለሙያዎች የሚጠቁሙት ብዙ የማረጋገጫ መንገዶች ቢኖሩም በአሳማኝ ደረጃ እውነተኛ መስለው ከሚፈበረኩት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ ከመጡት የምስል እና የቪዲዮ ይዘቶች ጋር በማያቋርጥ እሽቅድድም ውስጥ ናቸው።ከሀሰተኛ ይዘቶች ጀርባ ያለው ቴክኖሎጂ በየጊዜው እየተሻሻለ መምጣትም የሰዎች ግንዛቤ አሁንም ለተሳሳተ ብያኔ የተጋለጠ እንዲሆን አድርጓል። ተዋናዮቹ ይህንን መሰሉን ይዘት መፍጠር ብቻ ሳይሆን በፍጥነት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንዲሰራጭ ማድረጋቸው፣ደግሞ የበለጠ ግራ መጋባትን እና አለመተማመንን ሊፈጥር ይችላል።

በሌላ በኩል የአውሮፓ ሕብረት የሳይበር ደኅንነት ኤጀንሲመረጃ እንደሚያሳየው በዚህ ዘርፍ የሚሳተፉ ተዋናዮች ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ ፤ አነስተኛ ቴክኒካል ክህሎት ያላቸው ጭምር ጥልቅ ሀሰተኛ መረጃዎችን በመፍጠር ላይ ይሳተፋሉ።ከዚህ አንፃር የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎችን በመጠቀም ሐሰተኛ ድምጽ፣ ምስል እና ቪዲዮ ማቀናበር በትንሽ የቴክኖሎጂ እውቀት ኢንተርኔት ባለበት ሁሉ ማንኛውም ሰው መፍጠር እና ማሰራጨት የሚችል መሆኑ ሌላው ስጋት ነው። ይህንን ችግር ለመቋቋም በቴክኒክ፣ ተመራማሪዎች የማሽን-ትምህርትን በመጠቀም ጥልቅ ሀሰተኛ ይዘቶችን ለመለየት የማያስችሉ የምርመራ ስርዓቶችን እየገነቡ ቢሆንም፤ ይህ ግንዛቤ በስልጠና የሚገኝ እንጅ እንዲሁ የሚመጣ አይደለም። ስለሆነም ችግሩን ያገናዘበ መፍትሄ ከመንግሥታት እና ከቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንደሚጠበቅ ባለሙያው ያስረዳል።



የጄኔሬቲቭ ኤ አይ ጥቅሞች



ምንም እንኳ ጄኔሬቲቭ ኤአይ አሉታዊ ጎኖች ቢኖሩትም፤ ጊዜን እና ጥረትን ይቆጥባል ፈጠራንም ይጨምራል። የጥበብ ሰዎች፣ ጸሐፊዎች እና ንድፍ አውጭዎች አዳዲስ ሀሳቦችን ለማፍቅረብ ይህንን ቴክኖሎጂ መጠቀም ይችላሉ። መረጃ በመሰብሰብ ተጠቃሚዎች የሚፈልጓቸውን ይዘቶች ለምሳሌ እንደ ፊልም ወይም ሙዚቃ ያሉ ይዘቶችን በመለየት በተጠቃሚው ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ይዘት ለማቅረብ ሊያግዝ ይችላል። ይህም ግላዊነትን በማላበስ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚ ምቹ በማድረግ የደንበኞችን እርካታ ያሻሽላል።



ምርምርን ያቀላጥፋል



እንደ መድኃኒት ማምረት ባሉ የህክምና መስኮች ጀነሬቲቭ ኤአይ አዳዲስ መድኃኒቶችን ወይም የህክምና ዘዴዎችን የመፍጠር ሂደትን ሊያፋጥን ይችላል። ይህ ቴክኖሎጂ የተለያዩ ንጥረውህዶች እንዴት እንደሚገናኙ በሚያቀርበው መረጃም ሳይንቲስቶች አዳዲስ መድኃኒቶችን በፍጥነት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። እንዲሁም ሌሎች AI ሞዴሎችን በማሰልጠን ሰው ሠራሽ መረጃዎችን መፍጠር ይችላል፣ ይህም በገሃዱ ዓለም መረጃ ለመሰብሰብ የሚጠፋውን ጊዜን እና ወጪን ይቀንሳል። ምርምርን የበለጠ ቀልጣፋ ያደርጋል ፣ለአዳዲስ ፈጠራዎችም በር ይከፍታል።



የንግድ ሥራዎችን ያሻሽላል



ይህ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ወይም ጀነሬቲብ ኤአይ /Generative AI /የንግድ ሥራን ለማሻሻል ሊረዳ ይችላል። መረጃን ከመተንተን ጀምሮ እስከ ትንበያ ድረስ፣ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔዎችን ለማድረግ ይረዳል። ለምሳሌ አዝማሚያዎችን በመገምገም የደንበኞችን መረጃ መተንተን ወይም ኩባንያዎች ለወደፊቱ እቅድ ለማውጣት እንዲረዳቸው ትንበያዎችን መስጠት ይችላል። በዚህም ምርታማነትን ለማሳደግ እና የተሻሉ የንግድ ውሳኔዎችን ለማድረግ ጠንካራ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል።በመሆኑም አደጋውን በመቀነስ በቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ለመሆን መንግሥታት እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ቴክኖሎጂው የሚተዳደርባቸውን ፖሊሲዎች መመሪያዎች እና ደንቦችን ማውጣት እንዲሁም የተጠቃሚዎችን የዲጅታል ግንዛቤን ማሳደግ እንደሚገባቸው የሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ አባት የሚባሉትን ጀፈሪ ሂንተንንጨምሮ በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች በመጠየቅ ላይ ናቸው። ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ በበኩሉ መገናኛ ብዙሃን እና ባለድርሻ አካላትም ለኅብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ መስጠት እንዳለባቸው ይገልፃል። መንግስታትም በጀት መድበው ለዜቻቸውን የዲጅታል ግንዛቤ መስጠት እንደሚገባቸው አስምሮበታል።





ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።





ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሰ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

በሰውሰራሽ አስተውሎት የሚሰሩ ሀሰተኛ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን እንዴት እንለይ?

በሰውሰራሽ አስተውሎት የሚሰሩ ሀሰተኛ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን እንዴት እንለይ?